የፌደራል ጠቅላይ አቃቢ ህግ የ114 ተከሳሾች ክስ እንዲቋረጥለት ለፍርድ ቤት በጽሁፍ አቀረበ
በሽብር ወንጀል ተከስሰው በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት የሚገኙትን ሁለት የዋልድባ መነኮሳት ጨምሮ የ114 ተከሳሾች ክስ እንዲቋረጥለት ለፍርድ ቤት ውሳኔ ማስተላለፉን የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ አስታወቀ፡፡ የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ የጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ማዕረጉ አሰፋ የሁለቱ መነኮሳት ክሱ መቋረጡን ለዶይቼ ቬለ አረጋግጠዋል። “ክሳቸው እንዲቋረጥ ውሳኔ መሰጠቱ እውነት ነው። በፍርድ ቤት በኩል ስለሆነ የሚለቀቁት፤ መለቀቅ አለመለቀቃቸውን ማረጋገጥ አልቻልንም፡፡
ዞሮ ዞሮ አቃቤ ህግ ክሱን ካነሳ ፍርድ ቤቱ የሚቀጥልበት ሁኔታ አይኖርም” ብለዋል፡፡ ክሳቸው ተቋርጦላቸዋል ከተባሉት ውስጥ ሁለቱ የዋልድባ መነኮሳት የሽብር ክስ የቀረበባቸው በጎንደር ተከስቶ ከነበረው ተቃውሞ ጋር በተያያዘ እንደነበር አይዘነጋም፡፡
መነኮሳቱ “ከግንቦት ሰባት ጋር ግኙነት አላችሁ፤ ጫካ ውስጥ የሚገኙ ታጣቂዎችን ትረዳላችሁ” በሚል የቀረበባቸውን ክስ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሲከታተሉ ቆይተዋል፡፡ ከዓመት በላይ በእስር የቆዩት መነኮሳቱ ለፊታችን ሚያዝያ 18 የፍርድ ቤት ቀጠሮ ተሰጥቷቸው ነበር፡፡
Share your thoughts on this post