fbpx
AMHARIC

የኤምኤች 370 የመሰወር እንቆቅልሽ ሳይፈታ ፍለጋው በሚቀጥለው ሳምንት በይፋ ያበቃል ተብሏል

ንብረትነቱ የማሌዢያ አውሮፕላን የነበረውን የኤምኤች 370 ፍለጋ በሚቀጥለው ሳምንት በይፋ እንደሚያበቃ ኃላፊዎቹ አስታውቀዋል፡፡

ኤምኤች 370 ከአራት ዓመት በፊት ከማሌዢያ ኳላላፑር ተነስቶ ወደ ቻይና ቤጂንግ ሲበር ነበር የተሰወረው፡፡

የኤምኤች 370 አውሮፕላን መሰወር በዘመናዊው የሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ እንቆቅልሽ የሆነ ጉዳይ ነው፡፡

ከዚህ ቀደም ትንንሽ ስብርባሪዎች በማዳጋስካርና ህንድ ውቅያኖስ ውስጥ በምትገኘው ሪዩኒየን ደሴት ውስጥ ተገኝተዋል፡፡

ሆኖም ለአራት ዓመታት ሙሉ የማሌዢያ መንግስት እና ሌሎች ሀገራት ተሳትፈውበታል፤ በመጨረሻም አንድ የአሜሪካ ድርጅትም ፍለጋው ውስጥ ተሳትፏል፤ ነገር ግን ሁሉም ፍሬ ማፍራት አልቻሉም፡፡

ለዚህ እንቆቅልሹ ላልተፈታው አውሮፕላን ፍለጋ እስከአሁን ድረስ ከ160 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር በላይ የወጣ ሲሆን፥ አብዛኛውን ወጪ ማሌዢያ እንደሸፈነች ተገልጿል፡፡

ከአውሮፕላኑ መሰወር ጋር ተያያዞ ከተሰነዘሩት መላምቶች መካከል ምናልባት ፓይለቱ እራሱን አጥፍቶ ሊሆን ይችላል፣ ነዳጅ ጨርሶ ይሆናል፣ ያልታወቀ አደጋ ደርሶበት ነው የሚሉና ሌሎች ሐሳቦችም ተነስተዋል፡፡

በቅርቡ ታዲያ የአውስትራሊያ ትራንስፖርት ቢሮ ፒተር ፎሊይና ግሬግ ሁድ ለአውስትራሊያ ፓርላማ እንደገለጹት ከሆነ አውሮፕላኑ ምናልባትም ነዳጅ ጨርሶ በህንድ ውቅያኖስ የመከስከሱ ነገር ያመዝናል ብለዋል፡፡

አውሮፕላኑ የተሰወረው እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2014 ሲሆን፥ 239 ሰዎችን ይዞ እንደነበር ይታወሳል፡፡

 

ምንጭ፦ታይምና ሌሎች

በአብርሃም ፈቀደ ወደ አማርኛ ተመለሰ

Share your thoughts on this post
%d bloggers like this:
Visit Us On TwitterVisit Us On YoutubeVisit Us On Instagram