<<ወደ ኢትዮጵያ መምጣት ያስፈለገበት አንዱ ጉዳይ ተተኪ ጠቅላይ ሚኒስትር የሚሰየምበትን የሽግግር ሒደት ለማየት ነው''>>
አምባሳደር ዶናልድ (ዶን) ያማማቶ፣ በአሜሪካ የአፍሪካ ዲፕሎማሲ ውስጥ በተለይም በምሥራቅ አፍሪካ ትልቅ ቦታ ያላቸው ዲፕሎማት ናቸው፡፡ በፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት፣ ለአፍሪካ ጉዳዮች ተጠባባቂ ረዳት ሚኒስትር ተብለው ከተሾሙ ስድስት ወራት አስቆጥረዋል፡፡ ቀድሞውንም በአፍሪካ የካበተ የዲፕሎማሲ ልምድ ያላቸው ጎምቱ በመሆናቸው ወደ ሥራ ለመግባት ጊዜ አልፈጀባቸውም፡፡ በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር በመሆን አራት ለዓመታት ማለትም እ.ኤ.አ. ከ2006 እስከ 2009 ማገልገላቸው አይዘነጋም፡፡ ከዚያም በፊት በጂቡቲ፣ ቆይቶም በአፍጋኒስታን፣ በቅርቡም በሶማሊያ የአሜሪካ መንግሥት ተወካይ በመሆን ከሁለት ዓመት በፊት አገልግለዋል፡፡ በዚህ ሳምንት ኢትዮጵያን ጨምሮ በኬንያ፣ በናይጄሪያና በቻድ ጉብኝት በማድረግ ላይ ስለሚገኙት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሬክስ ቲለርሰን ጉብኝት በማስመልከት ከጉብኝቱ መጀመር፣ ቀደም ብለው ከአፍሪካ ጋዘጠኞች ጋር በስልክ ቃለ ምልልስ አካሂደው ነው፡፡ ኢትዮጵያን ጨምሮ በበርካታ የአፍሪካ ጉዳዮች ላይ ለአምባሳደር ያማማቶ ከቀረቡ ጥያቄዎችና ምላሾቻቸው መካከል የተመረጡትን በማውጣት ብርሃኑ ፈቃደ የሚከተለውን አጠናቅሯል፡፡
ጥያቄ፡- የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በተለይ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር በተያያዘ አሜሪካ በቅርቡ ካወጣችው መግለጫ አኳያ የኢትዮጵያ ጉብኝታቸው ዓላማ ምንድን ነው? ከኢትዮጵያ ባለሥልጣናትስ ጋር በምን ጉዳዮች ላይ አተኩረው ይነጋገራሉ?
አምባሳደር ያማማቶ፡- በኢትዮጵያ የሚደረገው ጉብኝት በጣም ጠቃሚ ነው፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጵያ የአፍሪካ ኅብረት መቀመጫ በመሆኗ ጭምር ጉብኝቱ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነው፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቲለርሰን ከአፍሪካ ኅብረት ሊቀመንበር ሙሳ ፋቂ፣ እንዲሁም ከሌሎች ኮሚሽነሮች ጋር በአፍሪካ መሠረታዊና ፈታኝ ሁኔታዎች ላይ ይመክራሉ፡፡ የደቡብ ሱዳን፣ የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ የሶማሊያ እንዲሁም ጂ5 እየተባሉ በሚጠሩት እንደ ቻድ ባሉት አገሮች ጉዳይ ላይ፣ ለፀጥታ በሚደረገው ድጋፍና በሌሎችም በርካታ ጠቃሚ ነጥቦች ላይ ይነጋገራሉ፡፡ የኢኮኖሚ ዕድገትን በተመለከተም ውይይት ይደረጋል፡፡ የአፍሪካ ኅብረትን የምንመለከተው በመላው አፍሪካ ሥልጣን ያለው ትልቅ ተቋም እንደሆነ ነው፡፡ ወደ ኢትዮጵያ መምጣት ያስፈለገበት ሌላው ጉዳይ ግን ተተኪ ጠቅላይ ሚኒስትር የሚሰየምበትን የሽግግር ሒደት ጭምር ለማየት ነው፡፡ ምን ሊፈጠር ይችላል? የሚለውን እያየን ነው፡፡
ኢትዮጵያ በሰላም ማስከበር ሒደት በርካታ ወታደሮችን በማዋጣት ቀዳሚ በመሆኗ ብቻም ሳይሆን፣ በአፍሪካ ወሳኝ ሚና የምትጫወት አገር ነች፡፡ አፍሪካ የራሷን ፀጥታ በማስከበር ረገድ ከሌላው ዓለም በተለየ ከፍተኛ ድርሻ እንዲሁም የበላይነት ያላት አኅጉር ነች፡፡ ሁሌም መጥቀስ የምፈልገው ነገር 53 በመቶ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኦፕሬሽን ሥራዎች በአፍሪካ እንደሚከናወኑ ነው፡፡ በዓለም ካሉት የተመድ ወታደሮች ውስጥ 87 በመቶው በአፍሪካ ይገኛሉ፡፡ 50 በመቶው ሁሉም ሰላም አስከባሪ ወታደሮች የአፍሪካ ኅብረት ሲታከልበት 70 በመቶ ይደርሳል፣ እነዚህ ወታደሮች በአፍሪካ ይገኛሉ፡፡ አብዛኛው የዓለም ሰላም አስከባሪ ወታደሮችም አፍሪካውያን ናቸው፡፡ በመሆኑም አፍሪካ መስዋዕትነት በመክፈልና በቁርጠኝነት ጭምር የድርሻዋን እየተወጣች ትገኛለች፡፡ ስለኢትዮጵያ ጉዳይ ስናነሳ፣ በኢትዮጵያ ተተኪ ጠቅላይ ሚኒስትር ጉዳይ ላይ ብቻም ሳይሆን፣ ተቋሙንና ተቋሙን የማጠናከር ሥራዎችም ላይ ያተኮረ ጉብኝት ነው ማለት እንችላለን፡፡ በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች የተፈጠሩትን ችግሮች እያየን ነው፡፡ ምናልባትም ከአንድ ሚሊዮን ያላነሱ ሰዎች ስለተፈናቀሉበት ጉዳይም እናያለን፡፡ ጉዳዩ ከተከሰተ ወዲህ በእኛ በኩል ችግሩን ለመፍታትና ውጥረቱን ለማርገብ እንዴት ድጋፍ ማድረግ አለብን? እያልን ነው፡፡
እንደሚታወቀው ይህ ጉዳይ በኢትዮጵያ ብቻ የተከሰተ አይደለም፡፡ በመላው አፍሪካ ስንመለከት በርካታ አካባቢዎች ውስጥ ከመሬት ልማት፣ ከመሬት ባለመብትነት፣ ከውኃ አጠቃቀም መብት፣ ከብሔር፣ ከጎሳና ከድንበር ጉዳይ ጋር በተያያዘ በርካታ ችግሮችና ውጥረቶች ይከሰታሉ፡፡ በመሆኑም በአትዮጵያ የሚታየው ችግር የተለየ አይደለም፡፡ ስለዚህ አሜሪካ በምን መልኩ ድጋፍ መስጠት እንደምትችል፣ በምን መልኩ ውጥረቶቹና ችግሮቹ እንደሚቀረፉ፣ እንዲሁም ሌሎችም ኢትዮጵያ ውስጥ የሚታዩ ችግሮችን እንዴት መፍታት እንደሚቻልና የእኛ ሚናስ ምን መሆን እንዳለበት ማወቅ እንፈልጋለን፡፡ ሌላው ጉዳይ የሰብዓዊ መብት ነው፡፡ በዚህ ረገድ በኢትዮጵያ ጠንካራ አስተዋጽኦ የሚያደርግ የተቋም ግንባታ እንዲኖር፣ ኢትዮጵያ በቀጣናውም በአፍሪካ በአኅጉር ደረጃና ለኢትዮጵያ ሕዝብ ጭምር የምትጫወተውን አዎንታዊ ሚና እንድትቀጥልበት በማሰብ ነው ጉብኝቱ የሚደረገው፡፡
ጥያቄ፡- የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቲለርሰን ጉብኝት የመጣው ኢትዮጵያ አሳሳቢ የፖለቲካ ቀውስ ውስጥ በምትገኝበት ወቅት መሆኑ አንዱ ሲሆን፣ ጉብኝታቸው ግን ከሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ ጋር መገጣጠሙ የአጋጣሚ ነው? ወይስ ሁለቱ አገሮች በኢትዮጵያ ላይ እንዲያተኩሩ ያደረጋቸው ሌላ ነገር አለ? ከመጋረጃ ጀርባ የሚካሄድ በአገሪቱም ሆነ በምሥራቅ አፍሪካ ፖለቲካዊ ሁኔታ ላይ የሚደረግ ውይይት ይኖራል?
አምባሳደር ያማማቶ፡- የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቲለርሰን ጉብኝት የሚገጣጠመው ከሩሲያ አቻቸው ጉብኝት ጋር ብቻም ሳይሆን፣ ከተባበሩት ዓረብ የኤምሬትስ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጉብኝት ጭምር ነው፡፡ የቲለርሰን ጉብኝት ትኩረት ያለምንም ጥርጥር በአፍሪካ ኅብረትና በኢትዮጵያ ላይ ያነጣጠረ ነው፡፡ እነዚህ ዋና የትኩረት ነጥቦች ናቸው፡፡ ሁሉም ውይይቶችና ስብሰባዎችም ከአፍሪካና በኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ላይ በማተኮር የሚደረጉ ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ በድጋሚ ለመናገር የምችለው ኢትዮጵያውያን በሚደረገው ሽግግር ላይ ያላቸውን ምልከታ ማየት እንደምንፈልግ ጭምር ነው፡፡ ይህ ትኩረት የሚስብ ጉዳይ ይመስለኛል፡፡ ቀጣዩ መንግሥት ምን ሊመስል ይችላል? የሚለውን ነጥብ ይዘን አሜሪካስ አዲሱን አስተዳደር በምን መልኩ ልትደግፍ ትችላለች? የሚለውም ትኩረት ይሰጠዋል፡፡
በድጋሚ ለመናገር ያህል ተተኪ ጠቅላይ ሚኒስትር ለመሰየም ኢትዮጵያ እየሄደችበት ያለችው የሽግግር ሒደት በኢትዮጵያ ብቻ የሚታይ አዲስ ክስተት አይደለም፡፡ ሽግግሩ መልካም ነገር ነው፡፡ የሽግግር ሒደቱ ተቋማትን ለማጠናከር የሚያስችል የመሻሻልና የለውጥ አመላካች ሒደት ነው፡፡ ኬንያንም ብናይ ራይላ ኦዲንጋና ኡሁሩ ኬንያታን የሚመለከት ጉዳይ አለ፡፡ በናይጄሪያ በመጪው ዓመት ምርጫ ይካሄዳል፡፡ ምናልባትም በመጪዎቹ 18 ወራት ውስጥ በአፍሪካ የሚደረግ ወሳኙ ምርጫ ይመስለኛል፡፡ ወደ ኢትዮጵያ ስንመጣም የፖለቲካ ሽግግር ሒደት እንዳለ እናያለን፡፡ ይህ አዲስ ነገር አይደለም፡፡ ነገር ግን ለአገሪቱም ሆነ ለቀጣናው መረጋጋት ወሳኝ ሒደት ነው፡፡ በመሆኑም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትራችን ጉብኝት ትኩረት የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ስለሚሠሩት ወይም የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ የውጭ ጉዳይ ወደ ኢትዮጵያ ስለመጡበት ጉዳይ አይደለም፡፡ ይልቁንም ኢትዮጵያውያን ስለወቅቱ ሁኔታ ምን እንደሚያደርጉ፣ እንዲሁም በአፍሪካ ኅብረት ጉዳይ ላይ ያተኮረ ጉብኝት ነው፡፡
ጥያቄ፡- በመግቢያዎ ሲጠቅሱ በኢትዮጵያ የተተኪ ጠቅላይ ሚኒስትር ጉዳይ ትኩረት ይሰጥበታል ብለዋል፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቲለርሰን በኢትዮጵያ ጉብኝታቸው እነማንን እንደሚያነጋግሩ ሊጠቅሱልን ይችላሉ? በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች ስለነበረው ግጭትና ስለተፈናቃዮች ጉዳይም ጠቅሰዋል፡፡ ሚኒስትሩ የእነዚህን ክልሎች አመራሮች ያነጋግራሉ?
አምባሳድ ያማማቶ፡- አያነጋግሩም፡፡ እንደምታውቁት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጉብኝት በጣም አጭር ነው፡፡ ረዘም ላለ ጊዜ ብንቆይ ደስ ባለን ነበር፡፡ ነገር ግን እዚህ ዋሽንግተን ያለው ሥራ፣ በአፍሪካ መሥራት የምንፈልጋቸው ሌሎችም ጉዳዮች በመኖራቸው ያለን ፕሮግራም በጣም የተጣበበ ነው፡፡ ሚኒስትሩ አመራሩን ማለትም ጠቅላይ ሚኒስትሩን፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩን፣ ሌሎች የመንግሥት አካላትና የአሜሪካ ኤምባሲ ኃላፊዎችን፣ እንዲሁም ሌሎችንም ያነጋግራሉ፡፡ የክልል አመራሮችን ያነጋግራሉ ወይ? ለሚለው ጊዜ የሚኖራቸው አይመስለኝም፡፡ የኦሮሚያና የሶማሌ ክልሎችን ብቻም ሳይሆን፣ ሌሎችም ጉዳዮች የአኅጉሪቱን ወቅታዊ ጉዳዮች በተመለከተ እኛ ገለጻ እናደርግላቸዋለን፡፡ የኬንያ፣ የሱዳን፣ የዴሞክራቲክ ኮንጎ፣ የናይጄሪያና የሌሎችም አገሮች ጉዳዮችና ጥያቄዎች አሉ፡፡ ከኢትዮጵያ ጋር በምናደርገው ውይይት የደቡብ ሱዳን ጉዳይም ይነሳል፡፡ 2.5 ሚሊዮን የደቡብ ሱዳን ስደተኞች በኡጋንዳና በኢትዮጵያ ተጠልለዋል፡፡ ሌሎች ሁለት ሚሊዮኖችም በአገር ውስጥ ተፈናቅለዋል፡፡
ምናልባትም ከ25 እስከ 30 በመቶው ተፈናቃይ የአፍሪካ ስደተኞች ደቡብ ሱዳኖች በመሆናቸው ከባድ ችግር ነው፡፡ ከዴሞክራቲክ ኮንጎ አኳያም ሲታይ ከፍተኛ ስደተኛና በገዛ አገሩ የተፈናቀለ ሕዝብ በብዛት የሚታይባት አገር ነች፡፡ ኢትዮጵያ እንዲህ ባለው ጉዳይ ውስጥ ቁልፍ ሚና ስለምትጫወት እነዚህ ጉዳዮች የመወያያ ርዕስ መሆናቸው አይቀርም፡፡ የሶማሊያ ሰላምና መረጋጋትም ይነሳል፡፡ በኢትዮጵያ ሕዝብና ማኅበረሰብ ልማት ውስጥ፣ በኢትዮጵያ የተቋም ግንባታ ሥራ ውስጥ ይበልጥ ማድረግ ስለሚገባን ድጋፍ ውይይት ይደረጋል፡፡ ኢትዮጵያ በየዓመቱ የምታስመዘግበው የስምንት ወይም የዘጠኝ በመቶ የኢኮኖሚ ዕድገት በአፍሪካ ለሚፈለገው የኢኮኖሚ መረጋጋት ተምሳሌትና መሪ እንድትሆን የሚያደርጋት ነው፡፡ ኢትዮጵያ እንደ ኬንያና ናይጄሪያ ሁሉ ውስብስብ አገር ብትሆንም በርካታ ምቹ አጋጣሚዎችም አሏት፡፡ ከመንግሥት፣ ከሕዝቡና ከተቃዋሚዎች፣ ከአካባቢ መሪዎችና፣ ከክልልና ከማኅበረሰብ ቡድኖች ጋር መሥራት እንፈልጋለን፡፡
ጥያቄ፡- የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ቲለርሰን በኬንያ በሚያደርጉት ጉብኝት ወቅት ተቀናቃኙን ራይላ ኦዲንጋን ያነጋግራሉ ወይ? በኬንያ ፖለቲካዊ ጉዳይ ላይ የአሜሪካ አቋምስ ምንድነው? በፕሬዚዳንት ኬንያታ መንግሥት ላይ፣ እንዲሁም በሲቪል መብቶች ላይ ስለሚታየው ጉዳይ አስተያየት ቢሰጡበት?
አምባሳደር ያማማቶ፡- በኬንያ የሚገኘው ኤምባሲያችን በአፍሪካ ከፍተኛው ነው፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያት አለው፡፡ ኬንያ በጣም ቁልፍና ወሳኝ የቀጣናው እምብርት አገር ነች፡፡ ለኢኮኖሚ ልማትና ለተቋማት ጉዳይ ብቻም ሳይሆን፣ ለአፍሪካ ኅብረት፣ ለተመድ ከምታደርገው አስተዋጽኦ አኳያ፣ እንዲሁም የበርካታ ዓለም አቀፍ ተቋማት መገኛ ከመሆኗ አንፃር ኬንያ ወሳኝ አገር ነች፡፡ በመሆኑም ከኬንያ ፕሬዚዳንትም ሆነ ከመንግሥታቸው ጋር የፖለቲካና የኢኮኖሚ ሪፎርም አስፈላጊነት ላይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ውይይት ያደርጋሉ፡፡ ምክንያቱም በተቃዋሚውና በኬንያታ መንግሥት መካከል ያለው ጉዳይም ይኸው በመሆኑ ነው፡፡ ተቃዋሚውን አካል ማግኘትን በተመለከተ፣ ካለን የመርሐ ግብር መጣበብ አኳያ የሚሆን አይመስለኝም፡፡ የትኛውም አገር ውስጥ በሚደረገው ጉብኝት ወቅት የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ ፕሬዚዳንቶችንና ጠቅላይ ሚኒስትሮችን፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችን፣ የማኅበረሰብ አመራር አካላትን ማነጋገር፣ ተቋሞቻቸው እንዴት ይጠናከሩ? እንዲሁም ተቃዋሚዎችን በምን አግባብ በማሳተፍ ገንቢ ውይይቶችን በፖለቲካና ኢኮኖሚ ሪፎርሞች ላይ ያካሂዱ? የሚሉት ላይ ትኩረት ይደረጋል፡፡ ይህም የሁሉም አካላትና የኬንያ ሕዝብ ፍላጎት በመሆኑ ጭምር ነው እነዚህ ነጥቦች ላይ እናተኩራለን፡፡ በመሆኑም በኬንያ ጉብኝታችን ወቅት በምን ጉዳዮች ላይ እንደምናተኩር ይበልጥ ግልጽ ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን አሁን ባለው ሁኔታ በኬንያ ጠንካራ የተቋም ግንባታ ላይ ያተኮረ ውይይት እንደሚደረግ ይጠበቃል፡፡
ጥያቄ፡- ባለፈው ኅዳር በመፈንቅለ መንግሥት ሥልጣን ላይ የወጣውን የዚምባብዌ መንግሥት ዕውቅና ትሰጣላችሁ? ከጥቂት ሳምንታት በፊት አሜሪካ በዚምባብዌ ላይ የጣለችውን ማዕቀብ በማሻሻሏ፣ ስለዚህ ጉዳይ፣ እንዲሁም አዲሱ ፕሬዚዳንት ምናንጋዋ አዲስ ምርጫ ቢያካሂዱ ከተጣለባቸው ማዕቀብ ነፃ ልታደርጓቸው ትችላላችሁ?
አምባሳደር ያማማቶ፡- በሙጋቤና በምናንጋዋ መካከል የሥልጣን ሽግግር ሲደረግ፣ የደቡባዊ አፍሪካ የልማት ማኅበረሰብ (ሳዲክ) አገሮች እንዲሁም የአፍሪካ ኅብረት ለውጡ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ሪፎርሞችን እንደሚያመጣ ትልቅ ተስፋ ሰንቀው ነበር፡፡ የፕሬዚዳንት ምናንጋዋ ዓብይ ትኩረት የኢኮኖሚ ሪፎርም እንደሆነ ይታወቃል፡፡ የዕውቅናው ጉዳይ ለአገሮች ከምንሰጠው ዕውቅና ጋር የሚገናኝ ነው፡፡ በዚምባብዌ ያሉን አምባሳደር የአሜሪካን ብቻም ሳይሆኑ የሌሎችንም ወዳጅ አገሮችና አጋሮቻችን ጉዳይ በማስተባበር እየመሩ በመሆናቸው፣ ከዚምባብዌ ጋር እንዴት መሥራት እንዳለብን እያየን ነው፡፡ አምባሳደራችን ሃሪ ቶማስ ከፕሬዚዳንት ምናንጋዋ ጋር ተነጋግረው መሥራት በምንችልባቸው በርካታ ጉዳዮች ላይ ሐሳብ ተለዋውጠዋል፡፡ የዚምባብዌ መፃዒ ጉዳይ ላይ ብቻም ሳይሆን፣ ዚምባብዌ ስለሚኖራት ሚናም ተነጋግረዋል፡፡ በአሜሪካ ከሚገኙት የዚምባብዌ አምባሳደር ጋርም እየተጋገርን ነው፡፡ ዚምባብዌ በቀጣናው ጠቃሚ እንደመሆኗ መጠን ወደ ፊት ትልቅ ተስፋ አለን፡፡ የአገሪቱ ኢኮኖሚ በአንድ ወቅት በጣም ጠንካራ ነበር፡፡ በአሜሪካ ዶላር ላይ የተመሠረተ ኢኮኖሚ ግን ሊኖራት አይገባም፡፡ የራሷ መገበያያ ገንዘብ ላይ የተመሠረተ ኢኮኖሚ መፍጠር አለባት፡፡ ዚምባብዌ በቀጣናው የዳቦ ቅርጫት ስትባል የኖረች አገር ነች፡፡ ይህ በድጋሚ እንዲሆን እንፈልጋለን፡፡ ከፍተኛ አቅምና ዕድሉ አላት፡፡ ሕዝቧም በፈጠራና በችሎታ የተካነ በመሆኑ ይህንን ተጠቅሞ ለአገሪቱ ተቋማዊ ግንባታ የሚኖረውን ሚናም ማገዝ እንፈልጋለን፡፡ ከሳዲክ አገሮችና ከአፍሪካ ኅብረት ጋር በመሆን ይህን ለውጥ ለማምጣት እየሠራን ነው፡፡ ረዥምና ጊዜ የሚጠይቅ ሒደት ቢሆንም፣ አሜሪካ በዚምባብዌ መጪው ጊዜ ላይ ቁርጠኛ አቋም እንዳላት መግለጽ እፈልጋለሁ፡፡
ጥያቄ፡- አሜሪካ በቅርቡ ይፋ ያደረገችው የዕርዳታ በጀት ቅነሳ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ የኬንያ ጉብኝት ከሚነሱ ነጥቦች አንዱ ሊሆን ይችላል?
አምባሳደር ያማማቶ፡- በጉብኝታቸው ወቅት የዕርዳታ መቀነስ ሳይሆን ለውጭ አገሮች የምንሰጠው ድጋፍ እንዴት መስተናገድ እንዳለበት የሚያተኩር ጉዳይ ሊነሳ ይችላል፡፡ የምንሰጠውን ድጋፍ እንደ ኢንቨስትመንት እናየዋለን፡፡ በአፍሪካ የወደፊት የልማት ጉዞ ውስጥ ቁልፍና ወሳኝ በሆኑ ዘርፎች ላይ የሚደረግ ኢንቨስትመንት ነው፡፡ ከዚህ ባሻገር ግን ግንኙነታችንን የምናዳብርበትም ነው፡፡ ከኬንያ በቀር በአፍሪካ የመሠረተ ልማት አውታሮች ዝርጋታ ላይ አንሳተፍም፡፡ ሞምባሳን ከናይሮቢ የሚያገናኝ የመንገድ ግንባታ ሥራ ላይ መሳተፋችን ምናልባትም ትልቁ የአሜሪካ የመሠረተ ልማት ግንባታ ተሳትፎ ሊባል የሚችል ነው፡፡ ትኩረታችን ተቋማት ግንባታና ሰዎችን ማገዝ ላይ ነው፡፡ የሴቶች ትምህርት፣ የሥራ ፈጠራ ፕሮግራሞችና የወጣቶች ልማት ፕሮግራም የሆነው የ‹‹ያሊ›› ፕሮግራም ይጠቀሳሉ፡፡
ሌላው ጉዳይ ትምህርትን ለማስፋፋት የምናደርገው ትኩረት ነው፡፡ ጠንካራ የባንክ ተቋማት ለልማት ወሳኝ ግብዓት በመሆናቸው፣ እነዚህም ላይ ትኩረት እናደርጋለን፡፡ በየጊዜው እያደገ የመጣው የአፍሪካ የብድር ዕዳ ጫና ትኩረት የሚሻ ነው፡፡ ይህ ፈተና ነው፡፡ አፍሪካ ከግብርና የፍጆታ ዕቃዎች ምርት ላይ ወደ ተመሠረተ ኢንዱስትሪ እያደገች በመሆኗ፣ እኛም የዚህን ጉዞ ስኬት እንዲታይ እንፈልጋለን፡፡ በርካታ መስኮች ላይ ድጋፍ በማድረግ ኢንቨስት እያደረግን ቢሆንም፣ እውነቱን ለመናገር አንዳንዶቹ ፕሮግራሞች ትርጉም የማይሰጡ በመሆናቸው መወገድ እንዳለባቸው እናምናለን፡፡ መስፋፋት አለባቸው በምትሏቸው መስኮች ላይ ሐሳብና ጥቆማ ካላችሁ ለመስማት ዝግጁ ነን፡፡ ከማኅበረሰብና ከመንግሥት አመራሮች ጋር ሰፊ ውይይት ማድረግ ይኖርብናል፡፡ ለብቻችን የምናደርገው አይሆንም፡፡ ፕሮግራሞችና ፕሮጀክቶች የሚዋቀሩትና የሚተገበሩት በአጋርነት ሲሆን ትርጉም ይሰጣል፡፡ ይህም ሲሆን የኬንያንም ሆነ የአፍሪካ ሕዝቦችን ፍላጎት ማሳካት ይችላል፡፡
ጥያቄ፡- አሜሪካ በቻድና በጂቡቲ የፀጥታ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ፍላጎት እንዳላት ይታወቃል፡፡ በርካታ አሜሪካውያንን ይህ ጉዳይ አስገርሟል፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ የፀጥታ ጉዳይ ላይ ያላቸው ዕቅድ፣ ምናልባትም የአሜሪካ ዕቅድ ምን እንደሆነ ቢነግሩን?
አምባሳደር ያማማቶ፡- ‹‹ካምፕ ለሞኒዬ›› የተባለውን ወታደራዊ ሠፈር በምንመሠርትበት ወቅት የጂቡቲ አምባሳደር ነበርኩ፡፡ ይህ የአሜሪካ ወታደራዊ ተልዕኮ ዋናው መገኛ አካባቢ እንደመሆኑ፣ የሥልጠናና የፀጥታ ድጋፍ የሚሰጥበት ከመሆኑም ባሻገር 150 እና 151 የተባሉትን ግብረ ኃይል አባላት ያስጠለለ ሠፈር ነው፡፡ ዓላማው በአካባቢው አገሮች ድንበር ፀጥታ ማስፈንና የባህር ላይ ውንብድንና መዋጋት፣ ወደ አፍሪካ የሚገባውንና የሚወጣውን ሕገወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውርም መግታት ነው፡፡ ከፀጥታ አኳያ ጂቡቲን በምን መልኩ መርዳት እንደሚያስፈልግም የምንሠራበት ነው፡፡ ጂቡቲ የሰላም አስከባሪ ወታደሮችን ከሚያዋጡ አገሮች አንዷ ነች፡፡ ወይም የአፍሪካ ኅብረት በሶማሊያ ላለው ተልዕኮ (አሚሶም) አካል ነች፡፡ በጂቡቲ የጦር ሠፈር ላለው የፈረንሣይ ጦርም ድጋፍ እናደርጋለን፡፡ ይህንን ሁሉ የምናስተባብርበት ነው፡፡ ሌላው ጉዳይ ቻይናም የጦር ሠፈሯን መመሥረቷ ነው፡፡ በሌሎች አገሮች ውስጥም የጦር ሠፈሮች አሉን፡፡ በመጪው ፀደይ ወቅት በዋሽንግተን ዲሲ በምናካሂደው ውይይት ወቅት ቻይና በአፍሪካ ያላት ተልዕኮና ኦፕሬሽን ምን እንደሆነ ለማወቅ እንሞከራለን፡፡ ከቻይና ጋር በመነጋገር በጁቡቲ ብቻም ሳይሆን፣ በሌሎች አገሮች ውስጥም ስለምታደርጋቸው እንቅስቃሴዎች መነጋገር እንፈልጋለን፡፡ በተለይም በምትሰጣቸው የዝቅተኛ ወለድ ብድሮች ሳቢያ በርካታ አገሮች ከፍተኛ የዕዳ ጫና ውስጥ እየወደቁ ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የመሠረተ ልማት እንዲስፋፋ ቻይና ድጋፍ እያደረገች ነው፡፡ የተመድ የሱዳን ተልዕኮ ውስጥ አዎንታዊ ሚና ተጫውታለች፡፡ ይሁንና በጣም ውስብስብ ግንኙነት ነው ያለው ቢሆንም፣ በፀጥታ ጉዳይ ላይ ከልብ በመነጨ መንፈስ እንዴት መተባበር አለብን? በሚለው ላይ እናተኩራለን፡፡ በፀጥታ ጉዳይ ላይ ከአፍሪካ ኅብረት፣ ከምሥራቅ አፍሪካ አገሮች የትብብር ማዕቀፍ፣ እንዲሁም ከምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት (ኢጋድ) እና ከሌሎች ጋር ስላለው የፀጥታ ጉዳይ ላይ በትብብር መሥራት እንፈልጋለን፡፡
ጥያቄ፡- ቻይና በጂቡቲ፣ በዚምባብዌም ሆነ በሌሎች አገሮች ውስጥ ያላትን የኢኮኖሚና የኢንቨስትመንት ፍላጎት አሜሪካ እንዴት ትመለከተዋለች?
አምባሳደር ያማማቶ፡- ቀደም ብዬ ለመጥቀስ እንደሞከርኩት፣ በዋሽንግተን ከቻይና ባለሥልጣናት ጋር ወደፊት የምንመክርበት ነው፡፡ ከተቻለ በሌሎች ሰፊ ጉዳዮች ላይ ለመነጋገር እንፈልጋለን፡፡ ሥጋቶቻችን ከሆኑት ውስጥ ቻይና በአፍሪካ ያላት ኢኮኖሚያዊ ዓላማ ምን እንደሆነ ማወቅ ነው፡፡ የታይዋን ደጋፊ ከሆኑት በቀር በሁሉም አገሮች ውስጥ ማለት ይቻላል ሚሲዮኖች አሏቸው፡፡ ይመለከቱናል በምንላቸው ጉዳዮች ላይ ለመተባበርና አብሮ ለመሥራት እንችል እንደሆነ ማየት እንፈልጋለን፡፡ አንደኛው ማየት የምንፈልገው ጉዳይ በርካታ አገሮች ዳግመኛ ወደ ከፍተኛ የፀዳ አዘቅት ውስጥ እየገቡ መሆናቸውን ነው፡፡ ይህ ያሳስበናል፡፡ ከዚህ ቀደም ከፍተኛ የብድር ጫና ውስጥ የገቡ ደሃ አገሮችን ለማገዝ በተደረገው ጥረት፣ አብዛኞቹ ዕዳቸው ተሰርዞላቸው የኢኮኖሚ ልማት ማስመዝገቡ የሚችሉበት ዕድል ተመቻችቶላቸዋል፡፡ ሆኖም እነዚህ አገሮች ዳግመኛ ዕዳ ውስጥ እንዲዘፈቁ አንሻም፡፡ አንዳንድ አገሮች ከኢኮኖሚያቸው እስከ 50 በመቶ፣ 100 በመቶ አንዳንዴም እስከ 200 በመቶ ከቻይና መንግሥት በዝቅተኛ ወለድ በሚሰጥ ብድር ሳቢያ ዕዳ ውስጥ ሲወድቁ እያየን ነው፡፡ ከሌሎች አገሮችና ተቋማት እየተበደሩም ለዚህ ዕዳ መጠን እየተዳረጉ ነው፡፡ በመሆኑም አገሮች በብድር ጫና ውስጥ ሳይወድቁ ነገር ግን የልማት ፍላጎታቸውን ማሟላት የሚችሉበትን ፋይናንስ እንዴት ሊያገኙ ይችላሉ? የሚለው ጉዳይ ላይ ምን መሥራት እንደሚገባን ማየት አለብን፡፡
ሌላው ተገቢ ያልሆነ የሀብት አጠቃቀምና ሽሚያ ላይ የሚታየው አካሄድ ነው፡፡ ሀብቱ ያላቸው አገሮችና ሕዝቦቻቸው በተገቢው መንገድ ተጠቃሚ መሆን በሚያስቻላቸው አኳኋን ያላቸውን ሀብት እንዲጠቀሙበት እንፈልጋለን፡፡ እዚህ ላይ ኮንጎ ብቻም ሳይሆን ሌሎችም የምዕራብ አፍሪካ፣ የደቡባዊ አፍሪካ፣ የምሥራቅ አፍሪካ አገሮችና ሕዝቦች ባላቸው የተፈጥሮ ሀብት ተጠቅመው የአፍሪካ ሕዝቦችን መሠረታዊ የኢኮኖሚ ልማት ተጠቃሚ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ሌላው ከፀጥታ አኳያ ለተመድ ኦፕሬሽኖች ቻይና ደጋፊና አጋዥ በመሆኗ ይህ እንዲስፋፋ ማድረግ ይገባል፡፡ በጤና አጠባበቅና ክብካቤም ቻይና በጣም ገንቢ ሚና እንዳላት ምሳሌ መጥቀስ እፈልጋለሁ፡፡ የእኛን ያየን እንደሆነ 81 በመቶው ለአፍሪካ የምንሰጠው ድጋፍ በጤና ክብካቤ ላይ የሚደረግ ኢንቨስትመንት ነው፡፡ ምንም እንኳ በቻይና አገር ውስጥ ፈታኝ የጤና ክብካቤ ሁኔታዎች እንዳሉ ሆኖ፣ ለአፍሪካ በምንሰጠው የጤና ክብካቤ ድጋፍ ላይ ማሻሻል ስለሚገቡን ጉዳዮች ጠቃሚ ሐሳቦችን ከቻይና አግኝተናል፡፡ ለውይይት የሚጋብዙ ጉዳዮች የመኖራቸውን ያህል በማንስማማባቸው ጉዳዮች ላይ ያለንን አቋምም የምናሳይበት ዕድል ይኖረናል፡፡
ጥያቄ፡- ሶማሊያን በደንብ የሚያውቋትና በቅርቡም እንደ ጎበኟት ይታወቃልና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ፖሊሲን መሠረት በማድረግ፣ ከኢትዮጵያና ከሶማሊያ እንዲሁም ከሌሎች አጋሮቿ ጋር ያደረጉት ውይይትን መነሻ በማድረግ፣ እየጨመረ ከመጣው በሰው አልባ አውሮፕላኖች የታገዘ ጥቃትና በሶማሊያ የአሜሪካ አምባሳደር መልቀቅ ጋር በተያያዘ ወታደራዊ አካሄድ እየታየ በመሆኑ፣ አሜሪካ በሶማሊያ ላይ ያስቀመጠችው ግብ ምን እንደሆነ ቢገልጹልን?
አምባሳደር ያማማቶ፡- ለሶማሊያ ጉዳይ ወታደራዊ ተልዕኮ መፍትሔ አይደለም፡፡ የአሜሪካ የአፍሪካ ኮማንድ (አፍሪኮም) ኮማንደር የሆኑት ጄኔራል ዋልደሆዘርና እኔ በብሔራዊ የጦር ኮሌጅ የድኅረ ምረቃ ትምህርታችንን ተከታትለናል፡፡ ሁለታችንም በሶማሊያ ጉዳይ ላይ መሠረታዊ የሆነ የአመላካከት አንድነት አለን፡፡ በሶማሊያ ከ20 ዓመታት በላይ ሠርቻለሁ፡፡ የአሜሪካ ኤምባሲ በዚያች አገር እንዲቋቋም የበኩሌን ጥረት አድርጌያለሁ፡፡ እ.ኤ.አ. በ2016/17 በሞቃዲሾ አዲሱ ኤምባሲ ተመሥርቷል፡፡ ለሶማሊያ በፖለቲካ ፍላጎት ላይ የተመሠረተ ፖለቲካዊ መፍትሔ እንዲኖር እንፈልጋለን፡፡ ፕሬዚዳንት ፋርማጆንና ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ ሌሎችንም ባነጋርንበት ወቅት እንዳነሳነው፣ ባለፈው ዓመት በለንደን በተደረገው ስምምነት መሠረት የሶማሊያ ፌዴራል መንግሥት ከጋሙዶግ እስከ ባይዶዋ ያሉትን የማኅበረሰቡን መሪዎች ማሳተፍ እንዳለበት የተደረሰው ስምምነት ትኩረት እንዲሰጡበት እንፈልጋለን፡፡
ከዚያም በላይ እስከ ሶማሌላንድና ፑንትላንድ ያለው ማኅበረሰብ የሚሳተፍበት እንዲሆን እንፈልጋለን፡፡ ተቋማትን መፍጠር ብቻም ሳይሆን፣ የሶማሊያ ብሔራዊ ጦር እንዲኖር የራሳቸውንም ወታደሮች በማሰማራት ፀጥታቸውን እንዲያስከብሩ፣ የፖሊስ ኃይላቸውን እንዲገነቡና ጠንካራ የፋይናንስ ተቋማትን እንዲመሠርቱ እንፈልጋለን፡፡ በፖለቲካው መስክም አንድ ሰው አንድ ድምፅ በሚለው መርህ መሠረት የምርጫ ሒደት እንዲኖራቸውና መሪ ሲሾሙም ከጎሳ የመምረጥ ሒደት እንዲወጡ፣ ይህም ለመልካም አስተዳደር እንደሚያግዛቸውና ሕዝቡም የራሱን መሪ መምረጥ እንዲችል ለማድረግ እየሠራን ነው፡፡ በመሆኑም በሶማሊያ ያለው ትኩረት ፖለቲካዊ ነው፡፡ በመሆኑም ፌዴራል መንግሥቱ ወደ ሁሉንም የፌዴራል ክልሎች የሚያቅፍ ጠንካራ መንግሥትና ጠንካራ የፌዴራል ጉዳዮች ላይ የተመሠረተ እንዲሆን ያስፈልጋል፡፡ በሰው አልባ አውሮፕላኖች በመታገዝ የሚካሄዱ ጥቃቶች ለፌዴራል መንግሥቱ የፀጥታ ድጋፍ ለመስጠት ታስበው ነው፡፡ ዋናው መሠረታዊ ነጥብ ግን ለሶማሊያ ያለው መፍትሔ ፖለቲካዊ በመሆኑ፣ ሶማሊያን አንድ ለማድረግ ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት ነው አማራጩ፡፡