fbpx
AMHARIC

ጠቅላይ ሚንሰትሩ የዘነጓቸው መቶ ቀናት!

ጠቅላይ ሚንሰትሩ የዘነጓቸው መቶ ቀናት! | ሬሞንድ ሃይሉ በድሬቲዩብ

ጠቅላይ ሚንሰትሩ ምኒሊክ ቤተ-መንግሰት ከከተሙ መቶ ቀናት ሞልቷቸዋል፡፡ በእነዚህ ጊዜያት ከጅግጅጋ እሰከ መቐለ፣ከአሶሳ እሰከ ጎንድር በማቅናት በመፈረስ ላይ ለነበረችው ሀገር ካስማ ሁነዋል፡፡ በዚህ ሳያበቁም የሁለት አስርታት አዚምን ሰብረው ኤርትራ የሚሏትን የቅርብ ዕሩቅ ፍቅሯን እንድንሞቅ መንገድ ጠርገዋል፡፡ ወዲያ ማዶ ያሉትን ባላንጣዎች ማቸርና ኬርን አዲሰ አበባ ጠርተውም የፍቅር ጸበል ርጭተዋቸዋል፡፡

እንዲህ ያለው የጠቅላይ ሚንሰትሩ ተግባር የገረማቸው ዓለመ አቀፍ የመገናኛ ብዙሃንም አብይ አህመድ (ዶ/ር) የሚለውን ስም በየዕለቱ በማንሳት በማወደስ ላይ ተጠምደዋል፡፡ ከሮይተርስ እስከ ሽንዋ ፣ከቢቢሲ እስከ አልጀዚራ የዘለቀው የውዳሴ ዜማ በሀገር ውስጥ የመገናኛ ብዙሃንም የተደገፈ ሁኖ ኢቢሲም ኤፍ ቢ ሲም እኩል እየዘመሩ ነው፡፡

በርግጥ ጠቅላይ ሚንሰትሩ በአጭር ጊዜ ካሰመዘገቡት ስኬት አንጻር የመገናኛ ብዙሃኑ የሰጡት ሽፋን የሚያሰወቅስ ባይሆንም ጥዋትም ማታም አንድ አይነት ዜና ማነብነባቸው ግን አሁንም የምንናፍቀውን የሀሳብ ብዝሃነት እንዳያጠፋው መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡ የሀገራችን መገናኛ ብዙሃን ከመጣው ስርዓት ጋር ተለጥፈው እጅ ከመንሳት የዘለለ ሚና ይኑራቸው የሚል አስተያየት መስጠቱንም ሀገር አደጋ ውስጥ ሲገባ ብቻ ሳይሆን ከወዲሁ ልንለምደው ይገባል፡፡

ጠቅላይ ሚንሰትሩም የመገናኛ ብዙሃኑ የእሳቸው የፕሮፖጋንዳ መሳሪያ የሆኑ እንዳይመስል የተለያዩ አሰተሳሰቦችን ለህዝብ የሚቀርቡበትን ዕድል ሊያመቻቹ ይገባል፡፡ ሁሉም የሚባሉ የሀገሪቱ የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ሃላፊዎች በእሳቸው ይሁንታ ስልጣን ላይ ያሉ እንደመሆናቸው መጠን የሀሳብ ብዝሃነት ላይ ከወዲሁ ትኩረት ሰጥቶ መስራቱ ተገቢ ይመስላል፡፡ ስለ ጠቅላይ ሚንስትሩ መቶ ቀናት ስናወራም የሰሩልንን ይዘን ከመዘመር ባለፈ እንዲሰሩልን የምንመኘውንም በመጠቆም ቢሆን ስለሚመሩት ህዝብ መረጃ እንዲያገኙ ይረዳቸዋል፡፡

ከዚህ በመነሳትም በእሳቸው መቶ የአመራርነት ቀናት የተዘነጋውን ሌላ አንገብጋቢ ጉዳይ ለመመልከት እንሞክር፡፡ ኢህአዴግ የራሱን ማህበራዊ መሰረት የለየ የፖለቲካ ድርጅት ነው፡፡ አርሶ አደሩን ዋና ማህበራዊ ካፒታል ያደረገው የድርጅቱ ጎዳና በርካታ ውጣ ውረድ ቢኖረውም ቢያንስ የትጥቅ ትግሉን በድል እንዲያጠናቅቅ የራሱን ሚና ተጫውቷል፡፡

በትረ ስልጣኑን ከያዘ በኋላም ቢሆን አብዮታዊ የሚለውን ቃል ከድርጅቱ ስያሜ ላይ ላለመፋቁ ምክንያት አድረጎ የሚጠቅሰው ይኼው የማህበራዊ መሰረት አለመለወጥን ነው፡፡ በርግጥ ገዥው ፓርቲ ከ1997 ዓ.ም ምርጫ በኋላ ወደ ከተማ ፊቱን ቢያዞርም ስትራቴጅካሊ ግን ዛሬም የአርሶ አደር ድርጅት መሆኑን አይክድም፡፡ እንዲህ ያለው አለመካድ ሁለት ጥቅሞችን ለገዥው ፓርቲ ይቸረዋል፡፡

የመጀመሪያው የአደጋ ጊዜ በሩ አድርጎ የሚገለገልበት ነው፡፡ ኢህአዴግ ፈታኝ ተቃውሞ በከተሞች ሲገጥመው እኔ ዋና መሰረቴ የገጠር ህዝብ ነው የሚል የማምለጫ ሙግትን የሚያሰማውም ለዚህ ነው፡፡ ለእንዲህ አይነቱ ትርክት ማሳያነት ደግሞ ከምርጫ 97 የተሻለ ወቅት የለም፡፡

ሌላው የአለመካዱ ምክንያት ግን በጠንካራ መከራከሪያ ላይ ያረፈ መሆኑ አጠያያቂ አይደለም፡፡ ይህም ሲባል ኢህአዴግ አርሶ አደርን ማህበራዊ መሰረት ለማድረግ መወሰኑ ለሀገሪቱ የሚበጅ ወሳኝ ጉዳይ በመሆኑ ነው፡፡ በዛሬዋ ኢትዮጵያ ውስጥ 81 በመቶ ያህሉ ህዝብ አርሶ አደር መሆኑ እሙን ነው፡፡ ከዚህ ህዝብ መካካል ደግሞ ከ70 በመቶ በላይ የሚሆነው ወጣት መሆኑ አያከራክርም፡፡

ገዥው ፓርቲ እንደ አንድ ቅደመ ካፒታሊስት ሀገርርን እንደሚያስተዳድር ድርጅት አርሶ አደሩን ተገን አደርጋለሁ ማለቱ የውዴታ ግዴታ የሚሆነውም ለዚህ ይመስላል፡፡ ጠቅላይ ሚንሰትር አብይ አህመድ ግን ባለፉት መቶ ቀናት ስለዋናው ማህበራዊ መሰረታቸው ብዙ ሊሉን አልደፈሩም፡፡ የደቡብ ሱዳን ሰላም ያሳሰባቸውን ያህል የ81 ሚሊዮን ህዝብ የስራ ዘርፍ የሆነው አርሶ አደርነት ብዙ ያሳሰባቸው አይመስልም፡፡

እዚህ ላይ የኢኮኖሚው ማነቃቂያው አርሶ አደሩን ተጠቃሚ የሚያደርግ አይደለም ወይ? የሚል ጥያቄ ሊነሳ እንደሚችል መገመት ይቻላል፡፡ በርግጥ ፕራይቬታይዜሽን ለአርሶ አደሩ ይዞለት የሚመጣው ገፀ በረከት እንዳለ አይካድም፡፡ ይሁን እንጅ አይደለም ገና ዳዴ በሚል አምራች ዘርፍ ላይ ቀርቶ ስኬታማ ወደ ሚባል ኢንዱስትራሊያዜሽን በፍጥነት ብነሸጋገር 70 በመቶ ለሚሆው የገጠር አርሶ አደር በዛው በትውልድ ቅየው የስራ ዕድል መፍጠሩ የውዴታ ግዴታ ነው፡፡

ይህ ሀሳብ ሁለት መሰረታዊ መነሻዎች አሉት፡፡ የመጀመሪያው የሀገራችን ከተሞች የቱንም ያህል በፍጥነት ቢያድጉና ቢሰፉ የገጠር አርሶ አደሮችን ፍልሰት የሚቋቋሙ ካለመሆናቸው ይመነጫል፡፡ ሁለተኛው የገጠሩ አርሶ አደር የትምህርት ደረጃ ዝቅተኛ በመሆኑ ወደፊት የሚፈጠሩ ግዙፍ ከተሞችም ለሱ የሚሆን የስራ ዕድል ብዙ አይኖራቸውም፡፡

ይህ እውነት በመቶኛ ሲቀመጥም የሀገራችን ከተሞች ታዓምራዊ የሚባል ዕድገትን ቢያስመዘግቡ እንኳን ከ30 በመቶ በላይ የሚሆን ወጣት አርሶ አደርን የማሰተናግድ አቅም የላቸውም፡፡ ከዚህ በመነሳት ገዥው ፓርቲም ይሁን ጠቅላይ ሚንሰትሩም በግል ዋና ማህበራዊ መሰረታቸውን አርሶ አደር ማድረግ የህልውናቸው መሰረት መሆኑን የሚገነዘቡት ይመስላል፡፡

ያ ካልሆነ ግን ከገጠር እየፈለሰ ለሚመጣ ወጣት የስራ ዕድል መፍጠሩ አደጋና ለሀገሪቱ ህልውናም አሳሳቢ ደረጃ ወደ መሆን ይሸጋገራል፡፡ በመሆኑም የተከበሩ ጠቅላይ ሚንሰትር ሆይ የዘነጉትን መንገድ አለና ዘወር ብለው ይመልከቱ ብያለሁ፡፡ DireTube

Share your thoughts on this post
%d bloggers like this:
Visit Us On TwitterVisit Us On YoutubeVisit Us On Instagram