fbpx
AMHARIC

የፍትህ ህግና ስርዓት ማሻሻያ ምክር ቤት ሊቋቋም ነው

የፍትህ ህግና ስርዓት ማሻሻያ ምክር ቤት ሊቋቋም መሆኑን የፌደራል ጠቅላይ አቃቢ ህግ አስታወቀ።

የፍትህ ስርዓቱ በርካታ ለውጦች ቢመዘገቡበትም የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር ዜጎችን ለእንግልት የፍትህ ስርዓቱን ደግሞ ለጥራት ችግር አጋልጦት መቆየቱን በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የተጠናው ጥናት ያመላክታል።

ቀልጣፋ የፍትህ አገልግሎት አለማግኘት እና መጉላላት፣ የፍርድ ውሳኔ ለማግኘት ለበርካታ አመታት መመላለስና መጉላላት፣ በወንጀል የተከሰሱ ሰዎች ከፖሊስ ምርመራ ጀምሮ ነጻ የህግ አገልግሎት አለማግኘት እንዲሁም ስልጣንን መከታ በማድረግ ሰዎችን ማንገላታት በጥናቱ ጎልተው የተለዩ ችግሮች መሆናቸውም ተጠቅሷል።

የሚስተዋሉትን ችግሮች በመቅረፍ የፍትህ ህግና ስርዓት አሰራሩን ለማሻሻልም የፍትህ ህግና ስርዓት ማሻሻያ ምክር ቤት ሊቋቋም መሆኑን የፌደራል ጠቅላይ አቃቢ ህግ አቶ ብርሃኑ ፀጋዬ ተናግረዋል።

ምክር ቤቱ ዜጎች በፍትህ ስርዓቱ ላይ የሚያነሱትን የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር፣ መጉላላትና የፍትህ ጥራት ችግርን መቅረፍ እንደሚያስችልም ነው የተናገሩት።

ከነጻነትና ከገለልተኝነት ጋር ተያይዞ የሚስተዋሉ ችግሮችን በመዳደስስም በአጭር ጊዜ ውስጥ ከምርመራ ጀምሮ በፍትህ አሰጣጡ ላይ የሚሻሻሉ ህጎችንም ይመለከታል ነው ያሉት።

ከዚህ ባለፈም ምክር ቤቱ በዋናነት በዳኝነት ስርዓት፣ የህግ ማመንጨት፣ ማውጣትና ማሻሻልን መሰረት በማድረግ፥ በዴሞክራሲ ተቋማት አሰራር እና በሌሎችም የህግ ስርዓቱ ላይ ምክረ ሃሳብን ለመንግስት ያቀርባል ብለዋል ጠቅላይ አቃቢ ህጉ።

የሚቋቋመው ምክር ቤት ከ9 እስከ 12 አባላት የሚይዝ ሲሆን በስሩ ስምንት ንዑስ ቡድኖች ይቋቋማሉ።

ምክር ቤቱ ከውጭና ከሃገር ውስጥ እንዲሁም ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና ከሌሎች የግል የህግ ባለሙያዎች በነጻነት ሙያዊ ሃሳብ የሚሰጡበት ይሆናል ብለዋል።

ይህ ደግሞ ወሳኝ በሆኑና መሻሻል ባለባቸው ህጎች ላይ በሙያ በማገዝ ዜጎች የሚፈልጉትን የፍትህ ስርዓት ለመዘርጋትና ለማጠናከር እንዲሁም የባለሙያዎችን ተሳትፎ ለማሳደግ ያግዛል።

ከዚህ ባለፈም በምክር ቤቱ ሁሉም ባለሙያ በሃገሩ ህግና ስርዓት ላይ በእኔነት ስሜትና በሃላፊነት እንዲሰራ ያስችለዋል ተብሎ ታምኖበታል።

ምክር ቤቱም ከሶስት ሳምንታት በኋላ ይቋቋማል ተብሎም ይጠበቃል።

 

በታሪክ አዱኛ – ኤፍ ቢ ሲ

Share your thoughts on this post
%d bloggers like this:
Visit Us On TwitterVisit Us On YoutubeVisit Us On Instagram