fbpx
AMHARIC

የግንቦት 20 ድል 27ኛ ዓመት በመላው ሀገሪቱ እየተከበረ ነው

የግንቦት 20 ድል 27ኛ ዓመት በመላው ሀገሪቱ በመከበር ላይ ይገኛል።

ግንቦት 20 የደርግ ስርዓት በህዝባዊ ጥያቄዎች በተመሰረተ የትጥቅ ትግል የወደቀበት እለት ነው።

በዓሉን አስመልክቶ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ ባስተላለፉት የመልካም ምኞት መግለጫ፥ አሁን ላይ መንግስት ከህዝቡ እያገኘ ያለው ድጋፍ የግንቦት 20 ድሎችን ለማስፋፋት ተጨማሪ አቅም መሆኑን ገልፀዋል።

በሀገሪቱ የተገኘውን የህዝብ ድጋፍና የታየውን መነቃቃት በመጠቀም የግንቦት 20 ድሎችን ለማስፋፋት መንግስት ትኩረት ሰጥቶ ይሰራልም ነው ያሉት።

የተጀመረው የህዳሴ ጉዞ እንዲሳካና የሀገሪቱ መጪ ጊዜ የተሻለ እንዲሆን የሀገሪቱ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በጠንካራ የአንድነት መንፈስ መስራት እንዳለባቸውም ፕሬዚዳንቱ አሳስበዋል።

የግንቦት 20 ድል የኢትዮጵያ ፖለቲካና ኢኮኖሚ መስተጋብር መሰረታዊ በሆነ መልኩ የተለወጠበትና አጠቃላይ የሀገሪቱ ገጽታ አወንታዊ ባህሪያትን እንዲላበስ መንገድ የተጠረገበት እንደሆነም በመግለጫቸው አመላክተዋል።

የዘንድሮው የግንቦት 20 ድል በዓል የሚከበረው ባለፉት 2 አመታት ሀገሪቱ ከገባችበት ቀወስ ተላቃ ሰላምና መረጋጋት በአስተማማኝ መልኩ ተረጋግጦ መንግስትና ህዝብም በአዲስ መንፈስ አዲስ ምዕራፍ በጀመሩበት  ወቅት ነው ብለዋል።

ባለፉት 27 ዓመታት የተመዘገቡ በርካታ የግንቦት 20 የድል ፍሬዎች መኖራቸውን የገለጹት ፕሬዚዳንቱ እነዚህን ውጤቶች የሚፈታተኑ በርካታ ችግሮችም የነበሩ መሆናቸውንም አስታውሰዋል።

አሁን ላይ መንግስትና ህዝብ እጅ ለእጅ ተያይዘው በጋራ ችግሮችን በመቀልበስ የላቀ የለውጥ ጉዞ ላይ ሲሆኑ፥ ለበለጠ ውጤትም መስራት እንዳለባቸውም ነው የገለጹት።

የህዝብን መሰረታዊ ጥያቄ መመለስና የዴሞክራሲ ምህዳሩን ማስፋት ቀጣይ የመንግስት የትኩረት አቅጣጫ እንደሚሆነም አስረድተዋል።

የግንቦት 20 ድል ፌዴራላዊ ስርዓት እንዲገነባና የሀገሪቱ ህዝቦች በማንነታቸው አንገታቸውን ቀና አድርገው ለሀገራቸው እድገት እንዲረባረቡ እድል መፍጠሩን ነው ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙላቱ የተናገሩት።

ኤፍ.ቢ.ሲ

Share your thoughts on this post
%d bloggers like this:
Visit Us On TwitterVisit Us On YoutubeVisit Us On Instagram