fbpx
AMHARIC

የከፍተኛ ሹማምንቱ ጡረታ ሀገርን ዳግም የመውለድ ያህል ውለታ ነው

ኢትዮጵያ የአዲሱ ትውልድ ናት፤ ያን ትውልድ ጦረን በክብር ልንሸኘው እንጂ ያረገዘውን ቂም እላያችን ላይ ሲገላገለው ማርያም ማርያም ብለን ልናርሰው ዝግጁ አይደለንም፡፡

ዶክተር አብይ እንኳን ሹመኛውን ፓርቲውም ወጣት ሆኖ ካልሰራ በጡረታ እንደሚያሰናብቱት አልጠራጠርም፡፡ ***** | ስናፍቅሽ አዲስ  በድሬቲዩብ

ሸኘናቸው፡፡ እያለቀስን አለመሆኑ ይገርመኛል፡፡ አራት አስርት ዓመት ያገለገለን ሰው በእልልታ እንደመሸኘት ከባድ ልዩነት የለም፡፡

የአንድ ተቋም የህይወት ዘመን ዘብ እንኳን ሲሸኝ ብዙ ተብሎለት ብዙ ተወድሶ ነው፡፡ ዶክተር አብይ መንገዱን ዘግተው የነበሩ ታላላቅ ሹምምንትን በጡረታ አሰናብተዋል፡፡

ሀገርን ዳግም የመውለድ ያህል የሚቆጠር ውለታ ነው፡፡ ሞቶ ሰው ሀገር በሚመራባት ሀገር እያለ በጡረታ ሲሰናበት ማየት አዲስ ምዕራፍ ነው፡፡

ያ ትውልድ ለእኛ ታግሎ ለራሱ ኖሯል፡፡ ያ ትውልድ በእኛ ስም እርስ በርሱ ተጫርሷል፡፡ ያ ትውልድ ለእኛ እኔ አውቅላችኋለሁ ብሎ በዚህ ዓለም ጨረቃ ላይ ቤት ልስራ ባለበት ዘመን ቤትም ሀገርም አልባ አድርጎናል፡፡ ያ ትውልድ ሰላሳ ስም ይዞ አንድ እኩይ ባህሪ ያለው ፍጥረት ነበር፡፡

እነኚህ በጡረታ የተሰናበቱ ሰዎች የሁለት ትውልድ ድርሻ እና ዘመን ቀርጥፈው የበሉ ናቸው፡፡ ውለታቸውን አናውቀውም፤ ይልቁንም መንገዱን ዘግተው አላሳልፍ በማለት ትውልድ ባለበት እንዲቆም ያደረጉ ናቸው፡፡

ኖሩ ሞቱ ግድ የማይሰጠውን ትውልድ አገልግለንሃል ቢሉትም የመሰናበታቸውን ዜና እንደሙዚቃ እየደነሰ ያዳመጠ ነው፡፡

ልጅ ከሚጦር አባት ቢጦር ይሻላል፡፡ በዘመናችን እና በጊዜያችን በእነርሱ ድርጎ ከመኖር እንዲህ አድርጎ መገላገል ይበጃል፡፡

አሁን ደግ ዘመን በራፍ ላይ ነን፤ ወይ እንገባለን ወይ እንመለሳለን፡፡ መግባት ነው የሚበጀን፡፡ ዶክተሩ ወሳኝ ሰው እንደሆኑ እያሳዩ ነው፡፡

ከዚህ በኋላ መድኃኒት ከኤርትራ በርሃ አንጠብቅም፡፡ ከአራት ኪሎ በሽታ አራት ኪሎ መዳሃኒት ተገኝቶለታል፡፡ ዝም ብዬ ሳስበው እንኳን ሹማምንቱ ኢህአዴግም ቢሆን በእርጅናዬ እቀጥላለሁ ካለ ዶክተር አብይ በጡረታ እንደሚሸኙት አልጠራጠርም፡፡

ከዚህ በኋላ ኢትዮጵያ የማይበጇትን እየጦረች ከሚበጇት ጋር ትጓዛለች፡፡ እኔ እበጃታለሁ ብሎ ድርቅና ደግሞ ስፍራ የለውም፤ ያን ህዝብ ይወስናል፡፡ የህዝብን ውሳኔ ጠቅላያችን ይተገብሩታል፡፡ አሜሪካ ምን ፍለጋ እንሄዳለን? DireTube

Share your thoughts on this post
%d bloggers like this:
Visit Us On TwitterVisit Us On YoutubeVisit Us On Instagram