fbpx
AMHARIC

የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክን ጎበኙ

የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክን ጎበኙ፡፡

ፕሬዚደንቱ ወደ ሐዋሳ ከተማ ሲገቡ የአካባቢው ህዝብ ደማቅ አቀባበል አድርጎላቸዋል፡፡

በፕሬዚዳንት ኢሳያስ የሚመራው የኤርትራው ልኡክ የሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ የማምረቻ ፋብሪካዎችን የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጋር በጋራ ጎብኝተዋል።

በፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የተመራው የኤርትራ ልኡክ በኢትዮጵያ የሶስት ቀናት ይፋዊ የስራ ጉብኝት ለማድረግ ዛሬ ነው ረፋድ ላይ አዲስ አበባ የገባው፡፡

ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱም፥ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድን ጨምሮ የክልል ርዕሳነ መስተዳድራን፣ ሚኒስትሮች፣ የኃይማኖት አባቶች፣ ታዋቂ ግለሰቦች እና የጥበብ ሰዎች ተገኝተው ደማቅ አቀባበል አርጎላቸዋል።

ፕሬዚዳንቱ በብሄራዊ ቤተመንግስት በተደረገላቸው የምሳ ግብዣ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር፥ የኢትዮጵያና ኤርትራ ህዝብ ለሰላም ያለው ፍላጎት እና ምኞች መግለፁን አንስተዋል።

በዚህም “የኢትዮጵያና ኤርትራ ህዝቦች ከእንግዲህ ሁለት ህዝቦች ናቸው ብለው የሚገልፁ አካላት ካሉ ሀቁን የማያውቁ ናቸው” ብለዋል።

የፊታችን እሁድ ዕለት ደግሞ በሚሊኒየም አዳራሽ 25 ሺህ ህዝብ የሚገኝበት “የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ሰላም ማብሰሪያ” መድረክ ይካሄዳል።
መድረኩ ላይም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ እና ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ተገኝተው ንግግር ያደርጋሉ ተብሏል።

በተጨማሪም የኪነ ጥበብ ባለሙያዎችም የሁለቱን ሀገራት ሰላም የሚያንፀባርቁ የተለያዩ ስራዎችን በመድረኩ ላይ እንደሚያቀርቡም ይጠበቃል።

Share your thoughts on this post
%d bloggers like this:
Visit Us On TwitterVisit Us On YoutubeVisit Us On Instagram