fbpx
AMHARIC

የኤርትራና ሶማሊያ ማዕቀብ ክትትል ኮሚቴ በኢትዮጵያ ጉብኝት እያደረገ ነው

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት በኤርትራ እና ሶማሊያ ላይ የጣለውን ማዕቀብ ተፈፃሚነት እንዲከታተል የተቋቋመው ኮሚቴ በኢትዮጵያ ጉብኝት በማድረግ ላይ ይገኛል።

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የካዛኪስታን አምባሳደር እና የኮሚቴው ሊቀመንበር ኬይራት ኩማሮቭ የተመራው ኮሚቴ በሃገራቱ ላይ የተጣለው ማዕቀብ እንዴት መሄድ እንዳለበት ለመምከር በአካባቢው ሀገራት የሚያደርገውን ጉብኝት ቀጥሎ በአዲስ አበባ ይግኛል።

የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዳስታወቀው ይህ ኮሚቴ ዛሬ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ሂሩት ዘመነ ጋር ተገናኝቶ ውይይት አድርጓል።

ቀደም ሲል ቡድኑ በኬንያ፣ ጅቡቲና ሶማሊያ ተመሳሳይ ጉብኝት ያደረገ ሲሆን፥ በኤርትራ ጉብኝት ለማድረግ ያቀረበው ጥያቄ በሀገሪቱ መንግሰት ተቀባይነት አላገኘም።

ከቡድኑ ጋር ውይይት ያደረጉት ወ/ሮ ሂሩት የኤርትራ መንግስት አካባቢውን ከማተራመስ እንዳልታቀበና የባህሪ ለውጥ እንዳላሳየ በመግለፅ የማዕቀቡ መነሳት ሁኔታ መሬት ላይ ባለው ተጨባጭ ሁኔታ መወሰን እንዳለበት ነው የተናገሩት።

የኮሚቴው ሊቀመንበር ኢትዮጵያ ለምታደርገው ትብብር ምስጋናቸውን በማቅረብ ወደፊትም ተቀናጅቶ ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን ገልፀዋል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኤርትራ መንግስት በሶማሊያ ለሚንቀሳቀሱ ታጣቂ ሀይሎች ድጋፍ በማድረግ ለአካባቢው ሰላም ጠንቅ መሆኑ መረጋገጡን ተከትሎ ነው በሀገሪቱ ላይ ማእቀብ የጣለው።

የኤርትራ መንግስት ከዚህ ተግባሩ አልታቀበም የሚለው የፀጥታው ምክር ቤት በሀገሪቱ ላይ የተጣለውን ማእቀብ በተደጋጋሚ ሲያራዝምም ቆይቷል።

ኢትዮጵያም የዚህ ማእቀብ አፈፃፀም ላይ አስፈላጊው ምርመራ እንዲደረግ ስታነሳ የነበረው ጥያቄ ተቀባይነት አግኝቶ ወደ ተግባር ተገብቷል።

ኤፍ ቢ ሲ

Share your thoughts on this post
%d bloggers like this:
Visit Us On TwitterVisit Us On YoutubeVisit Us On Instagram