fbpx
AMHARIC

የኢትዮ ጅቡቲ የባቡር መስመር በቀን 1 ሺህ ተሳፋሪዎችንና 53 ኮንቴይነሮችን እያጓጓዘ ነው

 (ኤፍ.ቢ.ሲ) – የኢትዮ ጅቡቲ የባቡር መስመር በቀን በርካታ ተሳፋሪዎችን እና ኮንቴነሮችን እያጓጓዘ መሆኑ ተነግሯል።

የባቡር መስመሩ ከሞጆ ደረቅ ወደብ ጋር ተገናኝቶ አገልግሎት መስጠት ከጀመረ ወዲህ በቀን 53 ኮንቴይነሮችን ከውጭ ወደ ደረቅ ወደቡ አመላልሷል፤ ይህም 53 ተሽከርሪዎች ከሚያነሱት ጋር እኩል ነው።

ከጥቂት ወራት በፊት ስራ የጀመረው የባቡር መስመሩ በቀን እስከ 1 ሺህ መንገደኞችንም እያጓጓዘ ይገኛል።

የኢትዮ ጅቡቲ የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት አክሲዮን ማህበር ዋና ዳይሬክተር ኢንጅነር ጥላሁን ሳርካ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ፥ የባቡር መስመሩ 73 ቀናትን መስራቱን ተናግረዋል።

ኢንጅነር ጥላሁን ባቡሩ በቀን እያነሳ ካለው በላይ ኮንቴይነሮችን የማንሳት አቅም ቢኖረውም፤ አሁን ባለው ደረጃ ግን አላማውን ማሳካት ችሏል ማለት ይቻላል ብለዋል።

መንገደኞችን ከማጓጓዝ ጋር በተያያዘም በአሁኑ ጊዜ በቀን እስከ 1 ሺህ ተሳፋሪዎችን ከለቡ ጣቢያ እስከ ጂቡቲ እያጓጓዘ መሆኑን ኢንጅነር ጥላሁን ተናግረዋል።

የባቡር መስመሩ በቀን እስከ 2 ሺህ መንገደኞችን የማጓጓዝ አቅም እንዳለው የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፥ ይሁን እንጂ ከባቡር ጣቢያዎች ጋር የሚያገናኙ እንደ መንገድ ያሉ መሰረት ልማቶች አለመጠናቀቅን በተግዳሮትነት አንስተዋል።

ታሪፍን አስመልክቶ ለሚነሳው ቅሬታም፤ የባቡር መስመሩ ተሳራፊዎችን በአንድ ኪሎ ሜትር 65 ሳንቲም ብቻ ነው የሚያስከፍለው ይህም ከሌሎች ሀገራት ጋር ስናነፃፀር ዝቅተኛ ታሪፍ ነው ብለዋል።

ሆኖም ግን ከቤታቸው እስከ ባቡር ጣቢያው ለመድረስ ሌላ ትራንስፖርት መጠቀማቸው ዋጋው የተወደደ እንዲመስል አድርጎታል ብለዋል።

አሁን ያለው ታሪፍ በጥናት ላይ ተመስርቶ መወሰኑን የገለጹት ኢንጅነር ጥላሁን፤ አስፈላጊ ከሆነ ግን ዳግም ጥናት ተደርጎበት ለሁለቱ መንግስታት ከቀረበ በኋላ ክለሳ ሊደረግበት እንደሚችልም ጠቁመዋል።

በአሁኑ ወቅት ከባቡር መስመሩ ጋር ተያይዞ የሚነሳው ዋነኛው ችግር ግጭት መሆኑን ተናግረዋል።

ይህንን ለመቅረፍም አጥር የማጠር እና ህብረተሰቡ ዘንድ ግንዛቤ የመፍጠር ስራዎች እየተሰሩ መሆኑንም አንስተዋል።

Share your thoughts on this post
%d bloggers like this:
Visit Us On TwitterVisit Us On YoutubeVisit Us On Instagram