fbpx
AMHARIC

የኢትዮጵያ ኤሌትሪክ አገልግሎት ከ10 ዓመት በላይ የተወዘፈ ከ133 ሚሊየን ብር በላይ ገቢ አልሰበሰበም

የኢትዮጵያ ኤሌትሪክ አገልግሎት ከ10 ዓመት በላይ የሆነው እና ከ133 ሚሊየን ብር በላይ ሀብት እንዳልሰበሰበ የኦዲት ግኝት ያሳያል።

የፌዴራል ዋና ኦዲት መስሪያ ቤት በጥር ወር አጋማሽ አካባቢ በድረ ገጹ ባሰፈረው መሰረት አገልግሎቱ ከተለያዩ መንግስታዊና መንግሥታዊ ካልሆኑ ተቋማት እንዲሁም ግለሰብ ደንበኞች ነው ገንዘቡን ያልሰበሰበው።

97 የተለያዩ የአገልግሎቱ ደንበኞች ከ1999 እስከ 2008 በጀት ዓመት ለተጠቀሙበት የኤሌክትሪክ አገልግሎት 81 ሚሊየን ብር ለመክፈል ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተው በተቋሙ ምንም ዓይነት እርምጃ እንዳልተወሰደባቸው በኦዲቱ ተመልክቷል፡፡

አዳዲስ የሀይል ፈላጊ ደንበኞች ክፍያ በፈፀሙበት ቀን ቅደም ተከተል ተራቸው ተጠብቆ የማይስተናገዱበት፣ የደንበኞች ዝርዝር መረጃ አያያዝ እና በአገልግሎት አሰጣጥ ቀልጣፋ አለመሆን እንዳለ ነው የኦዲት ግኝቱ የሚያሳየው።

የሀብት ብክነቱም ሆነ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሩ ለምን ተከሰተ ሲል ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የጠየቀው የኢትዮጵያ ኤሌትሪክ አገልግሎት ችግሩ ከደንበኞች ጋር የሚደረገው ውል እጅግ የቆየ እና በአንድ ቤት ወይም ድርጅት በርካታ ተገልጋዮች ተቀያይረው በመጠቀማቸው ተጠያቂ ለማድረግ አስቸጋሪ ሁኔታ በመፈጠሩ ነው ይላል።

በኢትዮጵያ ኤሌትሪክ አገልግሎት የፋይናንስ ስራ አስፈጻሚ አቶ ጌታቸው ወልደሰንበት፥ ተቋሙ ከኦዲት ግኝቱ በኋላ በሰራው ሰፊ ስራ ወደ 56 ሚሊየን የሚጠጋ ብር መሰብሰብ መቻሉን ይናገራሉ።

በህግ አግባብ መታየት ያለባቸውንም የመለየት ስራ መሰራቱን አቶ ጌታቸው አስረድተዋል።

በኢትዮጵያ ኤሌትሪክ አገልግሎት የሪቴል ቢዝነስ ሀላፊ ወይዘሮ ይደነቁ ሌዩ፥ የልየታ ስራውን ተከትሎ እርምጃ ሊወሰድባቸው የሚገቡ ተቋማትም ሆነ ግለሰቦች ላይ እየተወሰደ መሆኑን ተናግረዋል።

ነገር ግን ክፍያ በተቋማት ላይ እርምጃ ለመውሰድ በሚደረገው ሂደት ለህብረተሰቡ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት መገኘታቸው ለአሰራር አስቸጋሪ እንደሆነባቸው ገልፀዋል።

ለህብረተሰቡ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት መካከልም ለአብነት የአዲስ አበባ ወሀ እና ፍሳሽ አገልግሎትን አንስተዋል ሀላፊዋ።

ወይዘሮ ይደነቁ አያይዘውም ለኢትዮያ ኤሌትሪክ አገልግሎት የተጠቀሙበትን ክፍያ ያልፈጸሙ ቁጥራቸው በተለያየ ጊዜ ዝቅም ከፍም የማለት ሁኔታ አለ ያሉ ሲሆን፥ አሁን ባለው ቁጥር ክፍያ ያልፈጸሙ 75 የሚሆኑ ተቋማት አሉ ብለዋል።

ከነዚህም መካከል የሀገር መከላከያ ሚኒስቴር ስልጠና ዋና መምሪያ፣ የኢትዮጵያ ውሀ ስራዎች ኮርፖሬኝን እና የብረታብረት እና ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን የሚገኙበት ሲሆን፥ ኢንዱስትሪዎችም እንደሚገኙበት ሀላፊዋ ተናገረዋል።

አገልግሎቱ ሊከፈሉ የማይችሉ ወደ 131 ሚሊዮን ብር መመሪያው በሚፈቅደው መሰረት ለመሰረዝ የማጣራት ስራ እየተሰራ መሆኑን ለፋና ብሮድ ካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግሯል ፡፡

በቀጣይም ይህን መሰል ችግር ለመቅረፍ የመረጃ አያያዝ ስርአቱን በማዘመን እና የደንበኛች ውል በየሁለት አመቱ የማደስ ስራ ይሰራል ነው የተባለው፡፡

በሰርካለም ጌታቸው

Share your thoughts on this post
%d bloggers like this:
Visit Us On TwitterVisit Us On YoutubeVisit Us On Instagram