fbpx
AMHARIC

የአሰብ ወደብን ለመጠቀም ፈጣን እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው

የአሰብ ወደብን ለመጠቀም ፈጣን እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ መለስ ዓለም በዛሬው እለት በሰጡት መግለጫ፥ የአሰብ ወደብ አገልግሎት በአፋጣኝ የሚጀምሩበት ሁኔታ እንዲመቻች የሁለቱ ሀገራት መሪዎች መመሪያ መስጠታቸውን አስታውቀዋል።

በዚህም መሰረት በኢትዮጵያ እና ቤርትራ በኩል ዝግጅት መጀመሩንም ገልፀዋል።

ከትራንስፖርት ሚኒስቴር፣ ከኢትዮጵያ ማሪታይም አገልግሎት ባለስልጣን፣ ከኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክ አገልግሎት ድርጅት እንዲሁም ከተለያዩ ተቋማት የተውጣጡ አካላት ያሉበት ግብረ ሀይል ተቋቁሞ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።

የአሰብ ወደብን ለመጠቀም በአሁኑ ወቅት የመንገድ ጥገና ስራም እየተካሄ ይገኛል ያሉት አቶ መለስ፥ በኤርትራ በኩልም ተመሳሳይ ስራ መጀመሩን ነው የገለፁት።

አቶ መለስ አክለውም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ አስመራ የሚያደርገውን መደበኛ በረራም በነገው እለት በይፋ እንደሚጀምር ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የትኬት ቢሮውን በአስመራ ከፍቷል ያሉት አቶ መለስ፥ በቀጣይም የበረራ ቁጥሮቹን ከፍ እያደረገ እንደሚሄድ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ አስመራ በረራ ሲጀምርም ኤርትራ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ካሉት 115 ዓለም አቀፍ መዳረኛዎች ጋር ትገናኛለችም ብለዋል።

ከዚህ በተጨማሪም የኢትዮጵያ አየር መንገድ የኤርትራ አየር ክልልን በመጠቀሙ በአማካኝ ያጣው የነበረውን 100 ሺህ ዶላር ያስቀርለታል ሲሉም ተናግረወዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የኤርትራ አየር መንገድን 20 በመቶ ድርሻ እንደሚኖረውም አቶ መለስ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በነገው እለት በሚጀምረው በረራም 465 ሰዎች ወደ አስመራ ይጓዛሉ እንደሚጓዙም አቶ መለስ በመግለጫቸው አስታውቀዋል።

ከእነዚህም ውስጥ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት፣ ባለሀብቶች እና ለዓመታት ከቤተሰቦቻቸው ተለያይተው የቆዩ ኤርትራውያን ይገኙበታል ነው ያሉት።

በስላባት ማናዬ – ኤፍ.ቢ.ሲ

Share your thoughts on this post
%d bloggers like this:
Visit Us On TwitterVisit Us On YoutubeVisit Us On Instagram