fbpx
AMHARIC

የአሜሪካ የሰብዓዊ መብት ሪፖርት ኢትዮጵያን በእጅጉ ተቸ

ብሩክ አብዱ – ሪፖርተር

የአሜሪካ የዴሞክራሲ፣ የሰብዓዊ መብቶችና የሠራተኞች ጉዳይ ቢሮ እ.ኤ.አ. በ2017 በኢትዮጵያ የነበረውን የሰብዓዊ አያያዝ በእጅጉ ተቸ፡፡

ቢሮው ቅዳሜ ሚያዚያ 13 ቀን 2010 ዓ.ም. ባወጣው ሪፖርት በተጠቀሰው ዓመት ኢትዮጵያውያን ሰብዓዊ መብቶቻቸው በአግባቡ እንዳይከበሩላቸው፣ ከፍተኛ ፈተና ገጥሞአቸው እንደነበረ አስታውቋል፡፡

ሪፖርቱ በተለይ እ.ኤ.አ. በጥቅምት 2016 የታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በእስረኞች አያያዝና በግለሰቦች ሕይወት መጥፋት የሰብዓዊ መብት አያያዙን በእጅጉ እንዳባባሰውና የመናገር መብት፣ የፕሬስ ነፃነት፣ ኢንተርኔት የመጠቀም፣ የመሰብሰብ፣ የመደራጀትና የመንቀሳቀስ መብቶችን የገደበ አዋጅ እንደነበረ ገልጿል፡፡

እ.ኤ.አ. ግንቦት 28 ቀን 2016 መንግሥታዊ ባልሆነው በሰብዓዊ መብት ጉባዔ ባደረገው ዳሰሳ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ በኦሮሚያ፣ በአማራና በደቡብ ክልሎችና በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር 19 ግለሰቦች በፀጥታ ኃይሎች መገደላቸው ተረጋግጧል ብሏል፡፡ በመጋቢት ወር የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ያወጣውን ሪፖርት ጠቅሶ በኦሮሚያ፣ በአማራና በደቡብ ክልሎች በነበሩ ግጭቶች በአጠቃላይ 669 ሰዎች መገደላቸውን ያትታል፡፡

ከሶማሌ ክልል በፀጥታ አስከባሪዎች በተደረገ ዘመቻ፣ በኦሮሚያ ክልል በምሥራቅና በምዕራብ ሐረርጌ፣ በባሌና በጉጂ ዞኖች ከ100 በላይ ሰዎች መሞታቸውን ጠቁሟል፡፡

በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ወቅት ያለ ፍርድ ቤት ማዘዣ ማሰር በመቻሉ በርካታ ግለሰቦች የታሰሩ መሆናቸውን፣ እስረኞቹም መደበኛና መደበኛ ባልሆኑ እስር ቤቶች ታጉረው መቆየታቸውን ገልጿል፡፡ ትምህርት ቤቶች፣ ኮሌጆች፣ ማሠልጠኛ ተቋማትና የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በመላው አገሪቱ እንደ እስር ቤት ሲያገለግሉ መቆየታቸውንም ሪፖርቱ አመልክቷል፡፡

በዚህ ዓይነቱ የእስረኞች አያያዝ ምክንያት፣ የታሳሪዎች ቤተሰቦች በእስር ላይ የነበሩ ዘመዶቻቸው መጥፋታቸውንና ሊያገኟቸው እንዳልቻሉ ሪፖርቱ ያስረዳል፡፡

እስረኞችም በተጣበቡ ማቆያዎች እንደነበሩ፣ የምግብ፣ የመጠጥ ውኃ፣ የመፀዳጃና የንፅህና መጠበቂያዎች እንዳልነበራቸው ከተለያዩ ምንጮች አሰባሰብኳቸው ያላቸውን መረጃዎች አጠናቅሮ ማቅረቡን አስታውቋል፡፡

እስረኞች ቁልቁል በእግራቸው እንደሚሰቀሉና ወንጀላቸውን እንዲናዘዙ በማለት በኤሌክትሪክ ንዝረት እንደሚሰቃዩ፣ ብሎም እንደሚገረፉ ሪፖርቱ አመላክቷል፡፡

ሪፖርቱ በአሰላ የሚገኝ 400 ሰዎችን ብቻ መያዝ የሚችል እስር ቤት ውስጥ ከ3,000 ሰዎች በላይ ታጉረውበት እንደነበረም በምሳሌነት አቅርቧል፡፡ በቂሊንጦ ታስሮ ሕክምና በመከልከሉ ለሞት የተዳረገ አየለ በየነ የሚባል ግለሰብም እንደነበረ፣ አብረውት የተከሰሱ ሰዎች ለእስር ቤቱ አስተዳደር መታመሙን በተደጋጋሚ ቢያሳውቁም በቸልታ መታለፉን ለፍርድ ቤት ማስረዳታቸውን አባሪ አድርጓል፡፡

ብዙዎቹ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ሊከሰቱ የቻሉት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ የፀጥታ አካላት በራሳቸው ዕዝ በመንቀሳቀሳቸው፣ በየትኛውም የሲቪል ባለሥልጣን ቁጥጥር ሲደረግባቸው እንዳልነበረ መሆኑን በአፅንኦት ገልጿል፡፡

ይሁንና የሪፖርቱን መውጣት ተከትሎ መግለጫ ያወጣው በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲ፣ በሺዎች የሚቆጠሩ እስረኞች መፈታታቸው፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በንግግሮቻቸው ማሻሻያዎች መደረግ እንዳለባቸው መግለጻቸውን በማስታወስ እ.ኤ.አ. በ2018 የሚወጣው ሪፖርት የተሻለ ይዘት ይኖረዋል ብሎ እንደሚያምን አስታውቋል፡፡

ኤምባሲው አክሎም የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር ወደ ተግባር እንዲለወጥ ድጋፍ እንደሚያደርግ፣ በቀጣይ የሚወጡ ሪፖርቶች የተሻለ ይዘት እንዲኖራቸው የሚደረገውን ጥረት እንደሚያግዝ ጠቁሟል፡፡

የአሜሪካ ኮንግረስ ከሳምንታት በፊት የኢትዮጵያን የሰብዓዊ መብት አያያዝ የሚተችና የአሜሪካ መንግሥት ጠንካራ አቋም እንዲይዝ የውሳኔ ሐሳብ (ኤች አር 128) በሙሉ ድምፅ ማፅደቁ ይታወሳል፡፡

Share your thoughts on this post
%d bloggers like this:
Visit Us On TwitterVisit Us On YoutubeVisit Us On Instagram