የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ልዑል አልጋወራሽ ሼክ መሀመድ ቢን ዛይድ አል ነኸን በኢትዮጵያ ጉብኝት ሊያደርጉ ነው
የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ልዑል አልጋወራሽ ሼክ መሀመድ ቢን ዛይድ አል ነኸን ከነገ ጀምሮ በኢትዮጵያ ይፋዊ የስራ ጉብኝት ሊያደርጉ ነው።
ሼክ መሀመድ ቢን ዛይድ አል ነኸን ይፋዊ የስራ ጉብኝት ለማድረግም ነገ አዲስ አበባ እንደሚገቡ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ሼክ መሀመድ ቢን ዛይድ አል ነኸን በኢትዮጵያ በሚኖራቸው የሁለት ቀናት ቆይታም ከኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ እና ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ተገናኝተው እንደሚወያዩም ተገልጿል።
የሁለትዮሽ ጉዳዮች እና አካባቢያዊ ሁኔታዎችም የውይይታቸው አካል መሆኑ ተነግሯል።
ሼክ መሀመድ ቢን ዛይድ አል ነኸን በቆይታቸው የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳፋኪ ጋር ይወያያሉ ተብሎም ይጠበቃል።
ከዚህ በተጨማሪም ልዑል አልጋ ወራሹ በኢትዮጵያ በሚኖራቸው የሁለት ቀናት ቆይታ የመስክ ጉብኝትም ያደርጋሉ ነው የተባለው።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በቅርቡ በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ጉብኝት ማድረጋቸው ይታወሳል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በቆይታቸውም ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ልዑል አልጋ ወራሽ ሼክ መሀመድ ቢን አል ነኸን ጋር በአቡ ዳቢ ተወያይተዋል።
በዚህም ወቅት ሁለቱ ሀገራት ወዳኝነታቸውን እና ትብብራቸውን የበለጠ ማጠናከር በሚችሉበት ሁኔታ እንዲሁም በወቅታዊ አካባቢያዊ እና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ መምከራቸውም ይታወሳል።