የተለያዩ ሀገራት የግንቦት 20 ድል በዓል የመልካም ምኞት መልዕክታቸውን እየላኩ ነው
ዛሬ እየተከበረ ያለውን የግንቦት 20 ድል በዓልን ምክንያት በማድረግ የተለያዩ ሀገራት መሪዎች የመልካም ምኞት መልዕክታቸውን ለኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት እየላኩ ይገኛሉ ።
የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፒዮ በፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና አሜሪካ ህዝብ ስም የግንቦት 20 ድል የመልካም ምኞት መልዕክታቸውን ልከዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው ኢትዮጵያ እና አሜሪካ የጠለቀ እና የረዥም ጊዜ ወዳጅነት እንዳላቸው አንስተዋል።
ይህ ወዳጅነታቸው ዘላቂ ልማት፣ ዴሞክራሲ፣ የሰብዓዊ መብት፣ ሰላም እና መልካም አስተዳደር ማምጣት ላይ የተመሰረተ መሆኑንም ነው የገለፁት።
ለኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ መልካም ምኞታቸውን ያስተላለፉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፥ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት እና በቅርብ ዓመታት ሀገሪቱ የተጎናፀፈችውን የምጣኔ ሀብት እድገት ለማስቀጠል ላላቸው ቁርጠኝነት የአሜሪካ ሙሉ ድጋፍ እንዳላቸውም ነው ያረጋገጡት።
የሁለቱ ሀገራት ወዳጅነት የበለጠ እንዲያድግም የዩናይትድ ስቴትስ ዝግጁነትንም ደግመው አረጋግጠዋል።
በተጨማሪም የሳዑዲ አረቢያው ንጉስ ሳልማን እና ልዑል አልጋ ወራሽ መሀመድ ቢን ሳልማን ለኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ በላኩት መልዕክት ነው መልካም ምኞታቸውን ያስተላለፉት።
የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ፕሬዚዳንት ሼክ ከሊፋ ቢን ዛይድ አል ነኸን የመልካም ምኞት መልዕክታቸውን ልከዋል።
እንደዚሁ የሰሜን ኮሪያ ብሄራዊ ሸንጎ ፕሬዚዳንት ኪም ዮንግ ናም በተመሳሳይ የግንቦት 20 ድል በዓል መልካም ምኞታቸውን ልከዋል።
ኤፍ.ቢ.ሲ