fbpx
AMHARIC

የመዲናዋን የመብራት መቆራረጥ ለማስቀረት የተጀመረው የማስፋፊያ ፕሮጀክት በተያዘለት ጊዜ ማጠናቀቅ አልተቻለም

የአዲስ አበባን የመብራት መቆራረጥ ያስቀራል ተብሎ የተጀመረው የማስፋፊያ ፕሮጀክት እስካሁን አልተጠናቀቀም።

ይህ ፕሮጀክት የተዳከሙትን መስመሮች በአዲስ የመተካትና ነዋሪው የሚፈልገውን ሀይል ማስተላለፍ የሚችል አቅምን መፍጠር የሚያስችል ነው።

ይሁን እንጂ ፕሮጀክቱ ባለፈው ጥቅምት ወር ይጠናቀቃል ተብሎ የነበረ ቢሆንም፤ የተለያዩ ምክንያቶች ተፈጥረው መጠናቀቂያ ጊዜው ወደ ሚያዚያ ወር መገፋቱ ነው አቶ ጎሳዬ የሚያነሱት።

ነገር ግን ይህ የብዙዎችን የመብራት ችግር ይፈታል የተባለው ፕሮጀክት አሁንም ማጠናቀቅ አልተቻለም።

ለዚህ ደግሞ ከባለፈው ክረምት ጀምሮ የወሰን ማስከበር ችግሮች ፈታኝ ሆነው መቀጠላቸው እና አንዳንድ ቦታዎች በዚሁ የወሰን ማስከበር ምክንያት ስራ እስከማቆም የሚያስገድዱ ሁኔታዎች መፈጠራቸው እንደሆነ ዋና ስራ አስፈፃሚው ተናግረዋል።

እንዲሁም ለስራው ተብሎ መብራት ሲጠፋ ከህብረተሰቡ የሚመጡ ጥያቄዎች በመብዛታቸው በየቀኑ ስራዎችን ማከናወን እንዳልተቻለ እና በተያዘለት ጊዜ እንዳይጠናቀቅ እንቅፋት እንደሆነ ገልፀዋል።

እንደ ዋና ስራ አስፈፃሚው ገለፃ አሁን ላይ የፕሮጀክቱ አፈፃፀም ከ82 በመቶ በላይ መጠናቀቁን ነው የተናገሩት።

ለዚህም የመሬት ውስጥ ኬብል የመቅበር ስራ ከሚያስፈልገው 146 ኪሎ ሜትር ውስጥ 126 ኪሎ ሜትር ስራው ተጠናቋል።

ሌላው ዝቅተኛ መስመር የሚሸከሙ ወይም ወደየቤቱ የሚተላለፉ መስመሮች የሚሸከሙ፣ ዛፉ የሚባሉት ከአራቱም ማዕዘን ወደ ዋናው መስመር የሚገቡ መስመሮችን የሚሸከሙ እንዲሁም መካከለኛ የሚባሉ ወይም ከ10 ሜትር በላይ ከፍታ ያላቸው ፖሎችም ተከላዎች እየተከናወኑ ነው ተብሏል።

በአጠቃላይ ለፕሮጀክቱ መጠናቀቅ ከሚያስፈልገው 30 ሺህ የኮንክሪት ፖሎች 20 ሺህ የሚሆኑት እንደተጠናቀቁ አቶ ጎሳዬ ተናግረዋል።

ፕሮጀክቱንም ክረምት ከመግባቱ በፊት ለማጠናቀቅ እየተሰራም ነው ተብሏል።

ይህ ፕሮጀክት ከ162 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር በላይ በሆነ ወጭ እየተከናወነ የሚገኝ ሲሆን፥ 137 ሚሊየን ዶላሩ ከቻይና ባንክ በብድር የተገኘ መሆኑን የተቋሙ መረጃ ያመለክታል።

የፕሮጀክቱ መጠናቀቅ የከተማዋን የመብራት ችግር ለመቅረፍ ጉልህ ሚና ይጫወታል ተብሎ የታመነበት በመሆኑ ባለድርሻ አካላት በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባ ተነግሯል።

በዙፋን ካሳሁን

Share your thoughts on this post
%d bloggers like this:
Visit Us On TwitterVisit Us On YoutubeVisit Us On Instagram