fbpx
AMHARIC

እስራኤል አፍሪካውያን ስደተኞችን የማስወጣት እቅዷን ሰረዘች

እስራኤል በሕገ-ወጥ መንገድ አገሬ ገብተዋል ያለቻቸውን ከአስር ሺ በላይ የሚቆጠሩ አፍሪካውያን ስደተኞችን የማስወጣት መርሃ-ግብሯን ሰረዘች።

የእስራኤል መንግሥት ለሀገሪቱ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በፃፈውም ምላሽ ስደተኞችን በኃይል ከሀገር የማስወጣት እቅድ የሀገሪቱ አጀንዳ አይደለም ብለዋል።

ነገር ግን አሁንም ቢሆን የኢሚግሬሽን ባለስልጣናት በፈቃዳቸው መመለስ የሚፈልጉ ስደተኞችን ለመመለስ መንገዶችን እየፈለጉ ነው።

በሕገ-ወጥ መንገድ ገቡ የሚባሉ ከ30 ሺ በላይ አፍሪካውያን ስደተኞች እጣ ፈንታ አሁንም ያልለየለት ሆኗል።

ከዚህ ቀደም የእሥራኤል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በአብዛኛው ከኤርትራና ከሱዳን የመጡ ስደኞችን በፈቃዳቸው ገንዘብና ወደ አገራቸው መመለሻ ቲኬት ተሰጥቷቸው የሚመለሱ ካሉ እንዲሄዱ ካልሆነ በኃይል ከሀገር እንዳይወጡ እገዳ መጣሉ ይታወሳል።

በተባበሩት መንግሥታት ቀርቦ የነበረው ስደተኞችን ወደ ምዕራባውያን ሀገራት መልሶ የማስፈር እቅድንም እስራኤል ከዚህ ቀደም ተስማምታ የነበረ ቢሆንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቤንያሚን ናታንያሁ ስምምነቱን እንደሰረዙም ታውቋል።

በዚህም ስምምነት መሰረት እስራኤል ለስደተኞቹ በሌላ ሀገር መልሰው እስኪሰፍሩ ድረስ ጊዜያዊ መጠለያን ትሰጣለች የሚል ነው።

ሰኞ እለትም ከአሜሪካ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተውጣጡ 18 የዲሞክራቲክ ፓርቲ አባላት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ቤንያሚን ናታንያሁ በፃፉት ደብዳቤ የተባበሩት መንግሥታት ለስደተኞቹ ያወጣውን እቅድ መሰረዛቸውን እንዳሳዘናቸው ገልፀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስደተኞቹን ግራ ያጋባና ቀጣዩ እርምጃንም በግልፅ የማያሳይ በሚል ምክንያት እቅዱን እንደሰረዙት ተገልጿል።

ብዙዎቹ አፍሪካውያን ስደተኞች ከኤርትራ እንዲሁም በጦርነት ከታመሰችው ሱዳን የመጡ ናቸው።

ስደተኞቹ ለህይወታቸው ፈርተው እንደመጡና መመለስ እንደማይችሉ ቢገልፁም የእስራኤል መንግሥት ብዙዎቹን የአፍሪካ ጥገኝነት ጠያቂዎችን እንደ ኢኮኖሚ ስደተኛ ያያቸዋል።

ስደተኞቹ በበረሃማው ድንበር በኩል አጥር ከመስራቱ በፊት በግብፅ በኩል የገቡ ናቸው።

BBC Amharic

Share your thoughts on this post
%d bloggers like this:
Visit Us On TwitterVisit Us On YoutubeVisit Us On Instagram