fbpx
AMHARIC

ኢትዮጵያ ላቀረበችው የሰላም ጥሪ የኤርትራ መንግስት በጎ ምላሽ ሊሰጥ ይገባል – ኤርትራውያን ስደተኞች

አዲሱ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የኢትዮ- ኤርትራ ጉዳይ በሰላም እንዲፈታ ላቀረቡት የሰላም ጥሪ የኤርትራ መንግስት በጎ ምላሽ መስጠት እንደሚጠበቅበት በኢትዮጵያ የሚኖሩ ኤርትራዊያን ስድተኞች ገለፁ።

በትግራይ ሰሜናዊ ምዕራብ ዞን በአዲ ሓሩሽ ስድተኞች መጠልያ ጣቢያ ከሚገኙ ኤርተራውያን መካከል አቶ ክብሮም ፍስሃፅዮ አንዱ ናቸው ።

አቶ ክብሮም ለኢዜአ እንደገለፁት የኤርትራ መንግስት በኢትዮጵያ በኩል ለቀረበለት የሰላም ጥሪ በጎ ምላሽ የመስጠት ኃላፊነት አለበት።

“የኤርትራ መንግስት የሰላምን ዋጋ በመረዳት የቀረበለትን የሰላም ጥሪ ሊቀበል ይገባል ” ያሉት ደሞ አቶ ተስፋልደት ግርማይ ናቸው ፡፡

የሀገሩ መንግስት በኢትዮጵያ በኩል የቀረበለትን የሰላም ጥሪ በመቀበል ከጎሮቤት አገራት ጋር ሰላም ለማስፈን ቢተጋ ተጠቃሚ የሚሆነው የራሱ ሀገርና ህዝብ መሆኑን ተናግረዋል ።

“የኤርትራ መንግስት የአገሩን ህዝብ የልብ ትርታ በሚገባ በማድመጥ ከኢትዮጵያ መንግስት የቀረበለትን የሰላም ጥሪ መቀበል አለበት “ያለው ደግሞ በማይ ዓይኒ የኤርትራ ስድተኞች ጣቢያ ነዋሪ ወጣት ኪሮስ ንርአ ነው።

በዞኑ ህፃፅ በተባለ የኤርትራዊያን ስድተኞች መጠለያ ጣቢያ የምትገኝ ወጣት አዲያም ካህሳይ በበኩልዋ “የምንወዳት አገራችን ጥለን ለስደት የተዳረግነው በአገሪቱ ባለው የሰላምና የዴሞክራሲ እጦት ነው” ብላለች፡፡

በኤርትራ ሰላምና ዴሞክራሲ እንዲሰፍን ህዝቡ ተፅእኖ መፈጠር እንዳለበት ገልፃለች።

አዲሱ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር በኢትዮ -ኤርትራ ያለውን ጉዳይ በሰላም ለመፍታት ያቀረቡትን ጥሪ የኤርትራ መንግስት ተቀብሎ በደም ለተሳሰረው የሁለቱ ህዝቦች ግንኙነት መጠናከር የድርሻውን እንዲወጣ ጠይቃለች፡፡

በትግራይ ሰሜናዊ ምዕራብ ዞን በሚገኙ አራት የኤርትራዊያን ስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎች ከ180 ሺህ በላይ ኤርትራዊያን ተጠልለው እንደሚገኙ ከዞኑ የስድተኞችና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ አስተዳደር የተገኘ መረጃ ያመለክታል።
ENA

Share your thoughts on this post
%d bloggers like this:
Visit Us On TwitterVisit Us On YoutubeVisit Us On Instagram