fbpx
AMHARIC

“አፄ ቴዎድሮስ ሌትም ቀንም የሚያስቡት ስልጣኔንና ዘመናዊነትን ለማምጣት ነበር”

ለኢትዮጵያ አንድነት፣ ስልጣኔና ዘመናዊነት እንዲሰፍን መሠረት የጣሉና ታላቅ ራዕይ የነበራቸው መሪ ናቸው፤ አፄ ቴዎድሮስ:: አፄ ቴዎድሮስ ኢትዮጵያን ከምንም በላይ አስበልጠው ይወዱ ነበር:: እናም ከእንግሊዞች ጋር በተፈጠረ አለመግባባት ጦርነት ውስጥ በገቡ ጊዜ የሠራዊታቸውን መሸነፍ ሲመለከቱ ኢትዮጵያ በባዕዳን እጅ ገብታ ማየትን ፈፅሞ አልተቀበሉትም:: ስለሆነም መቅደላ አምባ ላይ ራሳቸውን አጠፉ::
እነሆ አፄ ቴዎድሮስ በመቅደላ አምባ ላይ በክብር ከወደቁ 150ኛ ዓመት ሆናቸው:: እኛም ታዲያ ይህን የ150ኛ የሰማዕትነት ዓመታቸውን ምክንያት በማድረግ ስለ አፄ ቴዎድሮስ መጠነኛ ግንዛቤ ይሰጡን ዘንድ እንግዳ ጋብዘናል:: እንግዳችን ዶ/ር ፋንታሁን አየለ ሲሆኑ በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የታሪክ አስተማሪና ተመራማሪ ናቸው:: በሙያቸው ደግሞ ረዳት ፕሮፌሰር ደረጃ ላይ ይገኛሉ:: መልካም ንባብ!

የአፄ ቴዎድሮስ ትውልድ እና እድገት የት እና እንዴት ነበር?

የፊቱ ካሣ ኃይሉ ወልደ ጊዬርጊስ የተወለዱት ቋራ ውስጥ ነው:: አባታቸው ደጃች ሀይሉ የቋራ አካባቢ አስተዳዳሪ ነበሩ:: እናታቸው ደግሞ ወ/ሮ አትጠገብ ይባላሉ:: በእርግጥ አንዳንድ ሰዎች የአፄ ቴዎድሮስን የትውልድ እና ዕድገት ሁኔታ በተመለከተ የተለያዩ ነገሮችን ሊሉ ይችላሉ:: ይሁን እንጅ በትክክል የተወለዱት ቋራ እንደሆነ በርካታ የታሪክ መረጃዎች ያመለክታሉ::
አፄ ቴዎድሮስ በልጀነታቸው የቤተ ክህነት ትምህርት እንዲማሩ ወደ ገዳም ተልከው የጠበቀ ዕውቀት እንደያዙም በእጃችን የሚገኙ በርካታ የታሪክ መረጃዎች ያመላክታሉ:: የነበሩበት ገዳም በመጀመሪያው የዘመነ መሣፍንት ጦርነት በመቃጠሉ እና ጓደኞቻቸውም በመገደላቸው እርሣቸው ተርፈው ስለነበር በቀጥታ ወደ ወታደርነት እንደገቡም መረጃዎች ያመለክታሉ::
በወታደርነት ከደጃች ክንፉ ዘንድ ሄደው በመግባት የኢትዮጵያን ድንበር ሲከላከሉ ከመቆየት ባለፈ ወታደራዊ ዕውቀትንም ቀስመዋል::

ለትግል እንዴት ተነሱ? ከህብረተሰቡ ዘንድ የነበራቸው አቀባበልስ ምን ይመስል ነበር?

አፄ ቴዎድሮስ የደጃች ክንፉን መሞት ተከትሎ ቋራን ማለትም አባታቸው ያሥተዳድሩት የነበረውን አካባቢ የማስተዳደር ፍላጐት ነበራቸው፤ ያ ግን ሊሆን አልቻለም:: ምክንያቱም በወቅቱ ራስ አሊና እቴጌ መነን አካባቢውን ወስደውት ነበር:: ይህን ተከትሎም እርሳቸው ወደ በረሃ ገብተው በሽፍትነት ትግሉን ጀመሩ::
አፄ ቴዎድሮስ ከሽፍትነታቸው ጀምሮ የተለየ ባህሪ ነበራቸው:: ይኸውም ለድሆችና አቅመ ደካሞች በጣም ያዝኑ ነበር:: በጦርነት አሸንፈው የሚያገኙትን ምርኮም ለነዚሁ የህብረተሠብ ክፍሎች እና ለወታደሮችም ያከፋፍሉ ነበር:: በመሆኑም በአካባቢው ማህበረሰቦች ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት እና ድጋፍ ማግኘት ችለው ነበር:: ይህ ሁኔታ ደግሞ በኋላ ላይ ድል በድል እያስመዘገቡ እንዲሄዱ አግዟቸዋል::

ኢትዮጵያን አንድ የማድረግ ትግላቸውን እንዴት ጀመሩት?

አፄ ቴዎድሮስ የኢትዮጵያን ታሪክ በደንብ ያውቃሉ:: ኢትዮጵያ በመካከለኛው ክፍለ ዘመን በእነ አምደ ፅዮን፣ በእነዘረ ያዕቆብ ጊዜ የነበራትን ገናናነትም በደንብ ያውቃሉ:: በተጨማሪም አገር ከመበታተን ይልቅ አንድ ከሆነች ጠንካራና ገናና እንደምትሆንም ያምናሉ:: ከዚህም ባሻገር የሚነገር ትንቢትም ነበር:: ይሄም ትምቢት ከኢትዮጵያ ቴዎድሮስ የሚባል ንጉስ ይነሣል:: እርሱም ኢትዮጵያን አንድ ከማድረግ ባለፈ በአገሪቱ እኩልነት፣ ነፃነት፣ ፍትህ እና ሠላም ያሰፍናል የሚል ነበር::
እርሣቸው ደግሞ እኔ ኢትዮጵያን አንድ ለማድረግ እና ህዝቦቿን ለመጥቀም እግዚ አብሄር የመረጠኝ ሠው ነኝ የሚል እምነት ነበራቸው:: ከዚህም በመነሣት ነው በኋላ ሲነግሱ የንግሥና ሥማቸውን ቴዎድሮስ ያስባሉት:: ንጉስ ነገስት ከሆኑ በኋላም ታዲያ ይሄን ትንቢት ለማሣካት እና ኢትዮጵያን አንደ ለማድረግ እንቅስቃሴያቸውን አጠናከረው ቀጠሉ::
ሌላው ደግሞ የዘመነ መሣፍንት ወቅት ህዝቡ ላይ ከፍተኛ መከራ እና ጫና ይደርሰበት የነበረበት ወቅት በመሆኑ ህዝቡም በትንቢት ይነገርለት የነበረው ንጉስ እንዲመጣ በተስፋ ይጠብቅ ነበር:: በመሆኑም አፄ ቴዎድሮስ ይህን ሁሉ ተገንዝበው ስለ ነበር ትንቢቱን እውን ለማድረግ ኢትዮጵያን አንድ የማድረጉን ትግል ገፉበት:: በኋላ ግን በተለያዩ ምክንያቶች የጀመሩትን ሣይጨርሱ መቅደላ ላይ ህይወታቸው አልፋለች::

ኢትዮጵያ ውስጥ ሥልጣኔንና ዘመነናዊነትን ለማምጣትሥ ለምን እና እንዴት ተነሱ? ምንስ አከናወኑ?

አፄ ቴዎድሮስ በኢትዮጵያ ሥልጣኔን እና ዘመናዊነትን ለማምጣት በመጀመሪያ እንዲያስቡ እና እንዲነሱ ያደረጋቸው ከግብፅ ጋር ያካሄዱት ጦርነት ነበር:: አፄ ቴዎድሮስ ከግብፆች ጋር ደበርቅ በምትባል ቦታ ላይ ባደረጉት ጦርነት በርካታ ወታደሮቻቸው ከመሞታቸው ባሻገር እርሣቸውን ጨምሮ ሌሎች በርካቶችም ቆስለው የመጀመሪያ ሽንፈታቸውን ተጐንጭተዋል:: በወቅቱ የአፄ ቴዎድሮስ ሰራዊት ጦር እና ጋሻ ታጥቆ የነበረ ሲሆን የግብፅ ጦር ደግሞ አውሮፓ ሰራሽ ጠብመንጃ ታጥቆ ነበር:: በመሆኑም የአፄ ቴዎድሮስን ሰራዊት ከእርቀት በጠብመንጃ እየተኮሰ ከፍተኛ ጉዳት አድርሶበት ነበር:: ይህ የተፈጠረው ኢትዮጵያ የሰለጠነች ባለመሆኗ ጠመንጃ መሥራት ባለመቻሏ እንደነበር አፄ ቴዎድሮስ ተገነዘቡ::
አፄ ቴዎድሮስ ታዲያ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ሌትም ቀንም የሚያሥቡት በኢትዮጵያ ሥልጣኔን እና ዘመናዊነትን ለማምጣት ነበር::
ማሠብ ብቻም ሳይሆን ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴም ገብተዋል:: ከእነዚህ መካከል ጋፋት ላይ መሣሪያ ማምረቻ እንዲሰራ አድርገዋል::
በወቅቱ በአውሮፓ ከፍተኛ የሥልጣኔ ደረጃ ላይ ከነበረችው እንግሊዝ ጋር የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በመጀመር ሥልጣኔ እና ዘመናዊነት በኢትዮጵያ እንዲመጣ እንዲያግዟቸው መወትወት ጀመሩ:: በወቅቱም ከእንግሊዝ በመጡ አማካሪዎች በመታገዝ እንደ መንገድ ያሉ ነገሮችን ለመክፈት ጥረት አድርገዋል:: ሠራዊታቸውን ደሞዝ ተከፋይ እንዲሆን አድርገዋል:: በቤተክርስቲያን ውስጥ ለውጥ እንዲመጣም ጥረት አድርገዋል:: ከእነዚህም ባሻገር ሌሎች ተግባራትንም ማከናወን ችለው እንደነበረም የተለያዩ የታሪክ ማሥረጃዎች ያመላክታሉ::

አፄ ቴዎድሮስ የተለያዩ ጦርነቶችን አድርገዋል:: ወደ ጦርነቶች የሚገቡባቸው ሁኔታዎች ምን ነበሩ?

አፄ ቴዎድሮስ በተለይ ከግብፆች ጋር ጦርነት ውስጥ የሚገቡት የኢትዮጵያን ዳር ድንበር ለማሥከበር ነው:: በሌላ በኩል ደግሞ አገራቸው ውስጥ ሥልጣኔ እና ዘመናዊነት እንዲመጣ ለማድረግ በሚሰሩት ሥራ ላይ እንቅፋት ሲገጥማቸው ወይም አላግዛቸው ከሏቸው ሀይሎች ጋርም ጦርነት ውስጥ ገብተዋል::
ለምሣሌ እንግሊዝ በኢትዮጵያ ሥልጣኔ እና ዘመናዊነት እንዲመጣ እንድታግዛቸው በተደጋጋሚ በመጠየቃቸው እና ከእንግሊዝ ሁለት አማካሪዎች በመላካቸው ውጥናቸው እንደሚሳካ ከፍተኛ እምነት ነበራቸው:: ይሁን እንጅ ያሰቡትን ድጋፍ ከእንግሊዝ ማግኘት አልቻሉም:: በመሆኑም እንግሊዛውያንን እና ሌሎችን የውጭ አገር ሰዎች ወደ እስር ከተቷቸው:: በዚህም የተነሣ ከእንግሊዝ ጋር ጦርነት ውስጥ ሊገቡ እና የእርሣቸው መጨረሻ ሊሆን ችሏል::
በሌላ በኩል ደግሞ በአገር ውስጥ የነበሩ የተለያዩ መሳፍንት የየራሣቸውን አካባቢ እንደፈለጉ ለማድረግ እንዲመቻቸው የአፄ ቴዎድሮሥን የአንድነት የሥልጣኔ እና ዘመናዊነት እንቅስቃሴ በመቃወም በተለያየ ጊዜ ወደ ጦርነት ይገባሉ:: በመሆኑም አፄ ቴዎድሮሥ ንጉስ ነገሠት ከሆኑ በኋላም ይሁን በፊት የማያቋርጥ ጦርነት ውስጥ አሳልፈዋል:: የሚያሳዝነው ግን ያሰቡትን ቢጀምሩም ሳይጨርሱት ማለፋቸው ነው::

በመቅደላው ጦርነት ወቅት ህዝቡ እስከ መጨረሻው ከጐናቸው ያለመቆሙ ለህልፈታቸው አንዱ ምክንያት ነው ይባላል:: ይሄን እንዴት ያዩታል? ይሄስ አንዴት ነው?

አፄ ቴዎድሮስ በትክክልም በመቅደላው ጦርነት በዋናነትም በእሮጌ ላይ ከእንግሊዝ ጋር ባደረጉት ጦርነት እንደ በፊቱ በርካታ ህዝብ ከጐናቸው አልነበረም:: ለዚህ ምክንያቶች ናቸው የሚባሉት ደግሞ ከሁለት ወገኖች ጠንካራ ተቃውሞ ገጥሟቸው ሥለነበር ነው:: አንደኛው በዘመነ መሣፍንት ወቅት እንደነበረው ሁሉ መሣፍንቱ የየራሣቸውን ግዛቶች በተናጠል ማሥተዳደር ባለመቻላቸው ከፍተኛ ተቋውሞ አሥነሥተዋል::
ሌላው ደግሞ ከቤተክህነት የገጠማቸው ተቃውሞ ነው:: በወቅቱ ቤተ ክህነት ሰፊ መሬት ነበራት:: ይህን ሰፊ መሬት ግን መሬት ለሌላቸው አርሶ አደሮች የማከፋፈል (የመሬት ሥሪት የማድረግ) ዕቅድ ነበራቸው:: በዚህም የተነሣ ከቤተክህነት ከፓትሪያርኩ ጀምሮ ከቀሣውስቱ እና ዲያቆናቱ ከፍተኛ ተቋውሞ ገጥሟቸው ነበር:: በዚህም ምክንያት ህዝቡ ከተቃውሞው ጐራ መሰለፍ ጀመረ::
በሌላ በኩል ደግሞ በእርሣቸው ጊዜ የነበሩ ዓመታትን በሙሉ ያሳለፉት በጦርነት ነበር:: በዚህ ሁኔታ እየተማረረ አብዛኛው ሰራዊታቸው ይወጣ ነበር:: በመጨረሻም ከነበራቸው ከ60 እስከ 70 ሺህ የሚደርስ ወታደር ውስጥ በእሮጌው ጦርነት ወቅት ከአምስት ሺህ የማይበልጥ ወታደር ብቻ ነበር የቀራቸው:: በዚህ ሁኔታ እንግሊዞች ሲመጡ ከፍተኛ የሆነ የሀይል መዳከም የነበረ በመሆኑ ሊመጣጠኑ አልቻሉም:: በመሆኑም የሽንፈታቸው አንድ ምክንያት ሊሆን ችሏል::

ከእርሣቸው በኋላ ኢትዮጵያን አንድ ያደረጓት እና ለማድረግ የጣሩት ነገስታት ከርሣቸው የተማሩት ነገር አለ?

አፄ ዮሀንስም ሆኑ አፄ ምኒልክ ኢትዮጵያን አንድ ለማድረግም ሆነ ሥልጣኔ እና ዘመናዊነትን ለማምጣት ከአፄ ቴዎድሮስ ትልቅ ትምህርት ተምረዋል:: አፄ ምኒልክ በተለይ ከእርሣቸው ቤት በግዞት ለበርካታ ዓመታት የቆዩ ከመሆናቸው ባለፈ በቅርበት ይከታተሏቸው እና ስለ ጥንቷ ኢትዮጵያ ታላቅነት፣ ሥለ ሥልጣኔ እና ዘመናዊነት አስፈላጊነት ያሥተምሯቸው ነበር:: በጣም እንደ ልጅ ከማየታቸውም ሌላ ልጃቸውን ሳይቀር ድረውላቸዋል::
በመሆኑም የአፄ ቴዎድሮሥ ራዕይ በአፄ ምኒልክ አዕምሮ ውስጥ ሰርፆ እንዲገባ ሆኗል:: ስለሆነም አፄ ምኒልክ ንጉሰ ነገስት ከሆኑ በኋላ አፄ ቴዎድሮስ ካስተማሯቸው ባሻገር ሀሣባቸው ያልተሣካባቸውን ድክመቶቻቸውንም ተረድተው ነበር:: በመሆኑም ኢትዮጵያን አንድ የማድረጉን እና ሥልጣኔ እና ዘመናዊነትን የማምጣቱን ጉዳይ በብልሃት እና በአስተዋይነት በማከናወናቸው ሊሳካላቸው ችሏል::

አፄ ቴዎድሮስ በአንድ በኩል አዛኝ፣ ሚዛናዊና ፍትሃዊ መሆናቸው ሲነገር በሌላ በኩል ደግሞ በተቃራኒው ጨካኝ እና ስሜታዊ ናቸው ይባላል:: ይሄ ከምን መጣ?

አፄ ቴዎድሮስ ለድሆች እና ለተበደሉት አዛኝ ፍትህ የሚሰጡ እና ሚዛናዊ እንደነበሩ በርካታ የታሪክ ማሥረጃዎች ይጠቁማሉ:: ከዚህ በተቃራኒው ደግሞ ጨካኝ እና ስሜታዊ እንደሆኑም ይነገራል:: በእርግጥ አፄ ቴዎድሮስ ጨካኝ እና ስሜታዊም ነበሩ:: ለዚህ ደግሞ በዋናነት የሚገፋፋቸው ያሰቡትን ኢትዮጵያን አንድ የማድረግ እና ሥልጣኔ እና ዘመናዊነትን የማምጣት ዕቅዳቸውን የሚያደናቅፉ ነገሮች እየገጠሟቸው ሥለ ነበር ነው::
በመሆኑም እርሣቸው ሠው እንደመሆናቸው መጠን ዕቅዳቸውን ለማደናቀፍ ጐንበሥ ቀና በሚሉት ላይ የጭካኔ እና ስሜታዊነት እርምጃ ይወስዱ ነበር:: በመሆኑም ሁለት ገፅታዎች እንደነበሯቸው መረጀዎች ያሥረዳሉ::

ልክ እንደ ትውልድ ቦታቸው ሁሉ ስለቀብር ቦታቸውም የተለያዩ ፀሀፍት የተለያየ ቦታዎችን ይጠቅሣሉ:: የቀብር ቦታቸው በትክክል የት ነው?

አፄ ቴዎድሮስ ህይወታቸው ባለፈበት የእሮጌው ጦርነት ወቅት በርካታ የውጭ ሀገር ፀሀፍት እና ጋዜጠኖች ተገኝተው ነበር:: እነሱ እንደፃፉት አፄ ቴዎድሮስን ሞተው ወድቀው የእንግሊዝ ወታደሮች እንዳገኟቸው እና በኋላም የእንግሊዝ የጦር አዛዥ ቆመው አስከሬናቸው በመቅደላ መድሃኒዓለም ቤተክርስቲያን እንዲቀበር እንዳደረጉም ፅፈዋል:: የታሪክ ማሥረጃዎች የሚያሳዩት እና እኔም የማውቀው መቅደላ መቀበራቸውን ነው::
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን አንዳንድ ሰዎች አስከሬናቸው ከመቅደላ ወጥቶ ወደ ትውልድ አካባቢያቸው መወሰዱን ይጠቅሣሉ:: ይህ ግን መሠረት የለውም:: ምክንያቱም መቼ እና ማን ቆፍሮ አውጥቶ እንደ ወሰደው ማሥረጃ የለም::

ለነበረን ቆየታ አመስግናለሁ!
እኔም እንግዳ አድርጋችሁ ስለጋበዛችሁኝ አመሰግናለሁ!
በኩር ጋዜጣ በአዲሱ አያሌው
ሚያዝያ 22/2010 ዓ/ም ዕትም

Share your thoughts on this post
%d bloggers like this:
Visit Us On TwitterVisit Us On YoutubeVisit Us On Instagram