fbpx
AMHARIC

ታሪክን በጨረፍታ – የግሽ ዓባይ የባህል ቡድን በሰሜን ኮርያ ፒዮንግያንግ ከተማ!

የሁለተኛው የዓለም ጦርነት በአሜሪካ ሃያልነት አና በሩሲያ አሸናፊነት ሲጠናቀቅ ዓለም በሁለት ጎራ ተከፈለ፡፡

ምዕራቡ የአውሮፓ ክፍል እና አሜሪካ በካፒታሊዝም ስር ሲጠለሉ፣ምስራቅ አውሮፓ እና በብዛት የእስያ ሃገራት ሶሻሊስታዊ ስራዓትን ተቀበሉ፡፡ ካፒታሊስቱ በአሜሪካ እየተዘወረ፣ሶሻሊስቱ ደግሞ በታላቋ ሩሲያ እየተጠበቀ ቀዝቃዛው ጦርነት ዓለምን አመሰው፡፡ ካፒታሊስቷ ደቡብ ኮርያ ከኮሚኒስቷ ሰሜን ኮርያ ጦር ተማዘው የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ከደቡብ ኮርያ ጎን ሁኖ ተዋግቷል፡፡

ከ 1953 ዓ/ም ጀምረው ግጭት ውስጥ የነበሩት ሁለቱ ኮርያዎች ከ 60 ዓመት በኋላ ለእርቅ ተቀምጠዋል፡፡
የሰሜን ኮርያው ፕሬዝዳንት ኪም ጁን ኡን እና የደቡብ ኮርያው ሙን ጀኢን ተጨባብጠው ታሪካችን እናድሳለን እያሉ ነው፡፡
ወደ ቀደመ ነገራችን ስንመለስ ኢትዮጲያ እስከ ጃንሆይ ዘመን ድረስ ዲፕሎማሲዋ ከምዕራባያውኑ ጋር ነበር፡፡
ደርግ ሶሻሊስት ሲሆን ኢትዮጲያ ፊቷን ወደ ምስራቁ እና ወደ አረብ ሃገራት አዞረች፡፡

ከካፒታሊስቷ ደቡብ ኮርያ ይልቅ ኮሚኒስቷ ሰሜን ኮርያ ለኢትዮጵያ ወዳጅ ሆነች፡፡በፖለቲካ ዘላቂ ጥቅም እንጂ ዘላቂ ጠላት ወይም ወዳጅ የለም፡፡ በ 1979 በተለይም የሶሻሊስት ሃገራት የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ነበራቸው፡፡
13 ኛው የዓለም የወጣቶች ቀንም በሰሜን ኮርያ ርዕሰ መዲና ፒዮንግያንግ እየተከበረ ነው፡፡ አፍሪካን በመወከል ኢትዮጲያ ስትመረጥ ኢትዮጲያ ይዛው የሄደች የባህል ቡድን ደግሞ የግሽ ዓባይን ኪነት ቡድን ነበር፡፡

ኪነት ቡድን በነ ኪም ጁን ኡን ቅድመ አያት ለነ ኪም ቤተሰብ እና ለመላው ዓለም አጀብ ያሰኘ የባህል ትርኢት አሳየ፡፡
በግሽ ዓባይ የኪነት ቡድን ዙሪያ መጠነኛ ጥናት ያደረገው ጋዜጠኛ ደረጀ ጥበቡ በአዲስ አድማስ ጋዜጣ እንዳሰፈረው የግሽ ዓባይ የኪነት ቡድን በ 1979 የፒዮንግዮንግ ከተማን አድምቋል፡፡
በጎጃም ክፍለ ሃገር በህዝብ ገንዘብ የተመሰረተው የግሽ ዓባይ የኪነት ቡድን ከአስመራ እስከ ፒዮንጋንግ ሰሜን ኮርያ ባህላችን አሳይቷል፡፡ እነ ይሁኔ በላይ፣ሰማኸኝ በለው፣ሃብቱ ንጋቱ(አንሙቴ)፣ተዘራ ማንችሎ ወዘተ የግሽ ዓባይ የኪነት ቡድን ፍሬዎች ናቸው፡፡

ሐምሌ 5 ቀን 1972 በደብረማርቆስ አፄ ተክለሃይማኖት ቤተመንግስት የተመሰረተው የግሽ ዓባይ ኪነት ቡድን በርካቶችን አቅፎ ይዞ ነበር፡፡
የግሽ ዓባይ ኪነት ቡድን በሽግግር መንግስቱ ወቅት በባህርዳር ከተማ ማዘጋጃ እንዲሆን ሲወሰን የገንዘብ እጥረት ገጠመው፡፡ ከ 1984 በኃላም ዳግም የግሽ ቡድን ወደ ከፍታው መምጣት አልቻለም፡፡

ከ 2004 ዓ/ም ጀምሮ እንደ አዲስ ተዋቅሮ ስራ የጀመረ ቢሆንም የቀደመ ከፍታውን ለማምጣት ብዙ ይቀረዋል፡፡ እንደ ግሽ ዓባይ የኪነ ት ቡድን ሁሉ የጎንደሩ ፋሲለደስ እና የወሎው የወሎ ላሊበላ የኪነት ቡድኖች ገናና ነበሩ፡፡ሁሉም በአዲስ ተዋቅረዋል ፡፡
ወደ ቀደመ ገናነታቸው ለመመለስ ግን ብዙ ድጋፍ ይሻሉ፡፡

በየሺሀሳብ አበራ

Share your thoughts on this post
%d bloggers like this:
Visit Us On TwitterVisit Us On YoutubeVisit Us On Instagram