fbpx
AMHARIC

በጃንጥላ ተከልሎ ቀዶ ህክምና? በችግር የተተበተበው ፈለገ ህይወት ሆስፒታል

በቅርቡ የባሕር ዳር ፈለገ ህይወት ሪፈራል ሆስፒታል የቀዶ ህክምና ክፍል ፎቶግራፍን በማህበራዊ ድረ ገጾች ያዪ ሰዎች ጥያቄ ነው። የቀዶ ህክምና ክፍሉ ጣሪያ ቀዳዳ ኖሯል። በጣሪያው ሽንቁርም ዝናብ ይገባል።

ሀኪሞች ቀዶ ህክምና ሲያደርጉ ዝናብ እንዳያውካቸው በጃንጥላ ይከላከላሉ። ነፍሳቸውን በሀኪሞቹ እጅ ጥለው አልጋው ላይ ያሉ ታካሚዎችም በጥላው ይጋረዳሉ።

ነገሩን በፎቶግራፍ መመልከትና ቦታው ሆኖ የሁነቱ አካል መሆን ይለያያሉ። በጃንጥላ ስር ቀዶ ህክምና ማድረግ ምን አይነት ስሜት ይኖረው ይሆን?

ስሜ አይጠቀስ ብሎ አስተያየቱን የሰጠን የህክምና ባለሙያ በቀዶ ህክምና ክፍሉ ጃንጥላ ተይዞለት ህክምና የሰጠው ከአንዴም ሁለቴ መሆኑን ይናገራል።

ባለሙያው እንደሚለው የቀዶ ህክምናውን ሂደት የሚያስተባብሩ ነርሶች ሁለት ወይም ሦስት ጥላ ይዘረጋሉ። ከቤታቸው እስከ ሆስፒታሉ የተጠለሉበት ጃንጥላ ሁለተኛ ዙር አገልግሎት እየሰጠ ይመስላል። ሁኔታው ለህክምና ባለሙያዎች ብቻ ሳይሆን ለህሙማንም ምቾት አይሰጥም።

“በእንደዚህ አይነት ሁኔታ ቀዶ ህክምና ከሚደረግልን ቢቀርብንስ? የሚሉም አሉ። ደህንነት አይሰማቸውም” ይላል ሀኪሙ።

ያነጋገርናቸው የሆስፒታሉ ሰራተኞች ጣሪያው ማፍሰስ ከጀመረ ሁለት ወር እንደሆነውና ቅሬታቸውን ደጋግመው ቢያቀርቡም መፍትሄ እንዳላገኙ ይናገራሉ።

“ዝናብ ጠብ ባለ ቁጥር ሁለት ወይም ሦስት ጥላ ተይዞ ነው የሚሰራው። ዝናብ በመጣ ቁጥር ለእኛ ሰቀቀን ይሆንብናል። ለታካሚዎችም አስቸጋሪ ነው። የቀዶ ህክምና ክፍል በጣም የፀዳ መሆን አለበት። ህሙማንን እናድናለን ሲሉ ሁለት ሰዎች ለኢንፌክሽን ተጋልጠዋል። ሞትም ሊከሰት ይችላል። ስለ ችግሩ ብንናገርም ከጤና ቢሮ ጀምሮ የሚመለከታቸው ሰዎች መፍትሄ አልሰጡንም” ይላሉ።

ሆስፒታሉ በዘርፈ ብዙ ችግሮች የተበተበ መሆኑን የሚገልጹት ባለሙያው ማህበረሰቡን ለማገልገል ከመፈለግ በመነጨ ፍላጎት ቢሰሩም በሆስፒታሉ ደስተኛ አለመሆናቸውን ያመለክታሉ።

ስለ ጉዳዩ ያነጋገርናቸው የፈለገ ህይወት ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር ዶ/ር መልካሙ ባዬ እንደሚሉት የቀዶ ህክምና ክፍል ዝናብ ያፈሰሰው ያሳለፍነው ሰኞ ብቻ ነው። ችግሩን በጊዜያዊነት ለመቅረፍ ያፈሰሰውን ቦታ መርጠው እንደጠገኑና በዘላቂነት መፍትሄ ለመስጠት ሙሉ እድሳት እንደሚያስፈልግ ይናገራሉ።

ሆስፒታሉ እድሜ ጠገብ መሆኑ ለችግሩ መንስኤ መሆኑን ተናግረው “በጤና ቢሮ የሚሰራው አዲስ ህንጻ ሲጠናቀቅ መፍትሄ ይሰጠናል” ይላሉ።

የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር አበባው ገበየ በበኩላቸው “በሆስፒታሉ ጥላ ተይዞ ቀዶ ህክምና አልተካሄደም። በማህበራዊ ድረ ገጽ የሚወራው ውሸት ነው” ባይ ናቸው። በእርግጥ የሀኪሞቹና የዳይሬክተሩ ምላሽ የዶ/ር አበባውን ይቃረናል።

ጥላ ተይዞ ቀዶ ህክምና ሲካሄድ የሚያሳዩ ፎቶግራፎችን ብዙዎች ከማክሰኞ አንስቶ በማህበራዊ ድረ ገጽ እየተቀባበሏቸው ነው።

ቀዶ ህክምና በጃንጥላ ስር

አርብ እለት ያነጋገርናቸው ስማቸውን ያልጠቀሱት ሀኪምና አንድ እጩ ሀኪም “ችግሩ ሁለት ወራት አስቆጥሯል” ይላሉ። ሜዲካል ዳይሬክተሩ የአንድ ቀን አጋጣሚ ነበር ተፈቷል ሲሉ፤ የጤና ቢሮ ኃላፊው ሀሙስ በፈለገ ህይወት ሆስፒታል ተገኝቼ እንዳየሁት የቀዶ ህክምና ክፍሉ አንድ ቀን ቢያንጠባጥብም ተጠግኗል።

“የቀዶ ህክምና ክፍሉ እንደሚያፈስና በወቅቱ እየሰሩ የነበሩ ሃኪሞች ጣሪያው ሲያፈስባቸው የወሰዱት አማራጭ ጥላ መዘርጋት እንደሆነ ሰምቻለሁ” ያለን የስድስተኛ ዓመት የህክምና ተማሪና በፈለገ ህይወት ሆስፒታል በቀዶ ህክምና ክፍል ልምምድ የሚያደርግ እጩ ሃኪም ነው።

ሆስፒታሉ አራት የቀዶ ህክምና ክፍሎች ሲኖሩት ጣሪያው ያፈሳል የሚባለው ሁለተኛው ክፍል ነው። ክፍሉ ጠባብ በመሆኑ ልምምድ የሚያደርጉ የህክምና ተማሪዎች ክፍሉ ውስጥ ገብተው ለመመልከት የሚቆሙበት ቦታ እንኳን አያገኙም።

“ይህም የወደፊቶቹ ሃኪሞች በቂ የልምምድ እውቀት እንዳያገኙ ፈታኝ አድርጎባቸዋል” ሲል ያክላል።

የጣሪያው ማፍሰስ እንደጊዜያዊ ችግር ተቆጥሮ እንደቆየ የገለፀልን ተማሪው “በክልል ደረጃ እንደሚገኝ አንድ ትልቅ ሪፈራል ሆስፒታል በርካታ ህሙማንን የሚያስተናግድ ቢሆንም ያለበት ችግር ተዘርዝሮ የሚያልቅ አይደለም” ሲል ይጨምራል።

የኦክስጅን እጥረት

ከዚህ ቀደም ሆስፒታሉ የኦክስጅን እጥረት ገጥሞት ነበር። ከአራት ወር በፊት በኦክስጅን እጥረት ስምንት ህጻናት መሞታቸውን ዳይሬክተሩ ዶ/ር መልካሙ ይናገራሉ።

ታካሚዎች ኦክስጅን ገዝተው ይጠቀሙ መባሉ አነጋጋሪ ነበረ። “ለኦክስጅን የሚወጣው ገንዘብ ከፍተኛ በመሆኑ በሽያጭ አድርገነዋል ማለታቸው፤ ገንዘብ ያላቸው ብቻ እንዲጠቀሙ የሌለው አማራጩ ሞት ብቻ እንዲሆን አስገድዷል” ሲል ተማሪው ይናገራል።

በሀገሪቷ የነበረው አለመረጋጋት ያስከተለው የመንገድ መዘጋት በሆስፒታሉ የኦክስጅን እጥረት ማስከተሉን ዳይሬክተሩ ጠቁመው፤ ሲያነጋግር የቆየው የኦክስጅን ችግር በቅርቡ እልባት አግኝቷል ይላሉ።

“ከአራት ወር በኋላ ሆስፒታሉ የራሱ ኦክስጅን ማዘጋጃ ይኖረዋል” ብለውም ተስፋ ሰጥተዋል።

የኦክስጅን እጥረት በእጅጉ ከጎዳቸው አንዱ የህጻናት ክፍል ነው። ክፍሉ በእንቅርት ላይ… እንዲሉ የማሞቂያ እጥረትም አለበት። ስማቸውን የማንጠቅሰው ዶክተር፤ የህጻናት ህክምና ክፍል ውስጥ ጨቅላ ህጻናት የሚሞቁበት ኢንኩቤተር ቁጥር ከሚወለዱ ህጻናት ጋር እንደማይመጣጠን ያስረዳሉ።

“በአንድ ግዜ ሙቀት የሚያገኙት አምስት ህጻናት ናቸው። አንድ ማሞቂያ ለአንድ ህጻን ብቻ መሆን ነበረበት” ይላሉ።

አልጋ ያላገኙ ታካሚዎች ኮሪደር ላይ

ድንገተኛን በቀጠሮ

የጤና እክል አጋጥሟቸው ወደ ሆስፒታሉ የሚሄዱ ታካሚዎች ለሳምንት ወይም ለወራት ቀጠሮ ይሰጣቸዋል። ባለቤታቸው ታማባቸው ከፍኖተ-ሰላም ወደ ሆስፒታሉ ያመሩ አስታማሚ እንደነገሩን ችግሩ አገልግሎት ለማግኘት ሳምንታት መጠበቃቸው ብቻ አይደለም።

“ላብራቶሪ ለማሰራት ሳምንት ሆነኝ። እንኳን አገልግሎት ሊሰጡን ወደ ላብራቶሪው ስንጠጋ እየገፈተሩ ነው የሚያባርሩን” ሲሉ ያማርራሉ።

በርካታ ታካሚዎችን በሚያስተናግደው ሆስፒታል አልጋ እንኳን የማያገኙ አሉ። መሬት ላይ ሆነው መድሃኒት የሚወስዱ ህሙማንን ማየት የተለመደ ነው።

ልጅ ወልደው ብዙም ሳይቆዩ ወለል ላይ የሚተኙ እናቶች ጥቂት አይደሉም። እናቶች ወልደው የሚጠብቃቸው እንክብካቤ ሳይሆን ቀዝቃዛና ጎርባጣ ወለል መሆኑን ማሰብ ያሰቅቃል ይላሉ ተገልጋዮች።

የቀዶ ህክምና የተደረገላቸው ህሙማንም ከቀዶ ህክምና ክፍል ከወጡ በኋላ ለማገገም የሚተኙበት ክፍል ባለመኖሩ አብዛኞቹ በረንዳ ላይና በየኮሪደሩ ለመተኛት ይገደዳሉ።

በሆስፒታሉ ሁለት ዓመት ተኩል የሰራው የአጥንት ህክምና ክፍል ነርስ አዳነ ከበደ* “አንድ ሰው በድንገት አጥንቱ ተሰብሮ ቢመጣ ህክምና የሚያገኘው ከሦስት ወራት በኋላ ነው” ይላል።

በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የመኪና አደጋ ደርሶባቸው የሚያክሙበት ቦታ ያጡበትን ወቅትም ያስታውሳል። በወቅቱ ተጎጂዎቹን ኮሪደር ላይ አስተኝቶ ለማከም እንኳን ቦታ ታጥቶ ነበር።

ያነጋገርነው ተማሪ እንደሚለው ሆስፒታሉ የቦታ ጥበት ችግርን ለመቅረፍ ሰፋፊ ክፍሎችን በማጥበብና ለሁለት በመክፈል እንዲሁም በረንዳን ወደ ክፍል መቀየር ሞክሯል። ሆኖም ይህም መፍትሄ ሊሆን አልቻለም።

‘ካልተከፈለን ራ እናቆማለን’

ነርሱ አዳነ ከበደ* እንደሚለው የህክምና ባለሙያዎች የትርፍ ሰዓት ክፍያ ከየካቲት ጀምሮ ለአራት ወራት አልተሰጣቸውም ነበር። በዚህ ምክንያትም በተለያየ እርከን ያሉ የህክምና ባለሙያዎች የሥራ ማቆም አድማ ለመምታት የፊርማ ማሰባሰብ ዘመቻ ሲያደርጉ ሆስፒታሉ የአንድ ወር ክፍያ ለመስጠት ወሰነ።

ባለሙያዎቹ የሚያማርሩት በክፍያ ጉዳይ ብቻ አይደለም፤ አስፈላጊ የህክምና መሳሪያዎች ባለመሟላታቸውም ጭምር ነው። ህክምና መስጫ መሳሪያዎች ሲበላሹ ለመጠገን የሚወስደው ጊዜም ሌላ የራስ ምታት ሆኖብናል ይላሉ።

በተለያየ ክፍሎች የሚገኙ ሀኪሞች የሚያነሷቸው ጥያቄዎች እንዲመለሱ ‘አድማ እንመታለን’ ሲሉ ማስፈራራትን እንደ አማራጭ እየወሰዱ ነው። ይህንን ለማድረግ የተገደዱትም ለጥያቄዎቻቸው አፋጠኝ ምላሽ ስለማያገኙ መሆኑን ያመለክታሉ።

“ጥያቄ ተጠይቆ መልስ ስለማይሰጥ እጩ ሀኪሞች፣ ነርሶች፣ ሬዚደንት ሀኪሞች በየተራ አምጸዋል። ለእዚህ የበቃነው ሰሚ ስለሌለን ነው” ይላል አዳነ።

ፈለገ ህይወት የአማራ ክልል ሪፈራል ሆስፒታል ቢሆንም ጥቃቅን የሚመስሉ ነገር ግን የሚያውኩ ክፍተቶችም ይስተዋሉበታል። እንደ ምሳሌ አቅጣጫ ጠቋሚ ምልክቶች አለመኖራቸው ይጠቀሳል።

ከባህር ዳርና ከአቅራቢያዋ ወደ ሆስፒታሉ የሚያቀኑ ታካሚዎች አንድ የህክምና ክፍልን ለማግኘት ለደቂቃዎች መንከራተትት ግድ ይላቸዋል።

ያነጋገርናቸው በተለያዩ ክፍሎች ያሉ የሆስፒታሉ ሰራተኞች አብዛኞቹን ችግሮች የሆስፒታሉ አስተዳዳሪዎችና የክልሉ ጤና ቢሮ በቀላሉ ሊፈቷቸው ቢችሉም ቸል ብለዋል ይላሉ።

ህሙማን በረንዳ ላይ
ህሙማን በረንዳ ላይ

የዘገየው የማስፋፊያ ህንጻ ግንባታ

የሆስፒታሉ ሜዲካል ዳይሬክተርና የጤና ቢሮ ኃላፊው ከቢቢሲ ለቀረቡላቸው አብዛኞቹ ጥያቄዎች እየተገነባ ያለው የሆስፒታሉ ማስፋፊያ ህንጻ ለችግሮቹ መፍትሄ ይሰጣል የሚል ምላሽ አላቸው።

ሆኖም ማስፋፊያ ግንባታው ይጠናቀቃል ከተባለበት በአራት ዓመት ዘግይቷል። ግንባታው መሀል ላይ ተቋርጦ ዳግም የተጀመረውም በቅርብ ነው።

“ችግሩ ከጨረታ ጋር የተያያዘ ነበር። ለግንባታው በቂ ገንዘብ ተመድቧል። የተቋራጩ ፍጥነት ህንጻው የሚያልቅበትን ግዜ ይወስነዋል” ይላሉ የጤና ቢሮ ኃላፊው።

በሌላ በኩል ዶ/ር መልካሙ ሆስፒታሉ ወደ ሰባት ሚሊየን ህዝብ ከማስተናገዱ አንጻር የሚመደብለት በጀት በቂ እንዳልሆነ ይናገራሉ።

ለችግሮቹ መንስኤ የሚሉትም የክልሉ ጤና ቢሮ ለሆስፒታሉ ትኩረት መንፈጉን ነው። በስድስት ወር ውስጥ 127ሺህ ተመላላሽ ታካሚዎች ህክምና ተሰጥቷቸዋል፤ 5ሺህ ከፍተኛ ቀዶ ህክምናም ተደርጓል።

ዳይሬክተሩ ፈለገ ህይወት እንደ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታልነቱ መስጠት የሚጠበቅበትን አገልግሎት እየሰጠ ስላለመሆኑ በጀት ያስከተለው የግብአት እጥረትን በምክንያትነት ያነሳሉ። የሰራተኞች ክፍያ ለሦስት ወራት የዘገየውም በጀት ስላልነበረ ነው ይላሉ።

“ለ2010 ዓ.ም ያስፈልጋል ብለን የያዝነው 316 ሚሊዮን ብር ቢሆንም የጤና ቢሮ መስጠት ከሚችለው በላይ ነው” የሚሉት ዳይሬክተሩ አፈጻጸማቸውን ሲመዝኑ ከእቅዳቸው ወደ ኋላ መቅረታቸውን ያክላሉ።

የጤና ቢሮ ኃላፊው ዶ/ር አበባው በአንጻሩ “በከፍተኛ የክልሉ ካቢኔ ጥናት ተሰርቶ የሆስፒታሉ ችግሮች ተለይተው ታውቀዋል። ለአገልግሎት ጥራት ማነስና የሰው ኃይል እጥረት መፍትሄ የሚሆን ሰነድ እየተገበርን ነው” የሚል ምላሽ አላቸው።

“ለሆስፒታሉ የሀገሪቷንና የክልሉን ስሌት መሰረት ያደረገ በጀት እንሰጣለን” ቢሉም ፈለገ ህይወት ከሚያስተናግደው ሰው አንጻር በጀቱን መከለስ ሊያስፈልግ ይችላል ይላሉ።

ኃላፊው “ስለ ክፍያ መቋረጥ ሪፖርት አልደረሰንም። የሰራተኞች ዲውቲ አንድም ቀን አልተቋረጠም” ይላሉ። የሰራተኞቹና የዳይሬክተሩ ምላሽ ግን ይህን ይቃረናል።

*ስም የተቀየረ

BBC Amharic

Share your thoughts on this post
%d bloggers like this:
Visit Us On TwitterVisit Us On YoutubeVisit Us On Instagram