fbpx
AMHARIC

በደቡብ ሱዳን ባለው የሰላም ችግር በቅርቡ 14 ሺህ የሚጠጉ የሀገሪቱ ዜጎች ወደ ጋምቤላ ክልል ገብተዋል

በደቡብ ሱዳን ባለው የሰላም ችግር ባለፉት ሁለት ወራት 14 ሺህ የሚጠጉ የሀገሪቱ ዜጎች ወደ ኢትዮጵያ ጋምቤላ ክልል መግባታቸውን የስደትና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ አስተዳደር አስታወቀ።

ስደተኞቹ በበኩላቸው ሀገራቸውን ጥለው ወደ ኢትዮጵያ የመጡት በሁለቱ ተቀናቃኞች መከካል በተደጋጋሚ እየተከሰተ ባለው የፀጥታ ችግርና በምግብ እጥርት ምክንያት መሆኑን ገልጸዋል።

በአስተዳደሩ የጋምቤላ ክልል የስደተኞች ፕሮግራም ማስተባበሪያ ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ለገሰ ድሪባ እንደገለጹት፥ በደቡብ ስዳን ባለው የሰላም ችግር ወደ ጋምቤላ ክልል የሚገቡት ስደተኞች ቁጥር እየጨመረ ነው።

በአውሮፓውያኑ ዘመን ቀመር ካለፈው ጥር ወር 2018 ጀምሮ እስካሁን 14 ሺህ የሚጠጉ የደቡብ ሱዳን ስደተኞች ወደ ክልሉ ገብተው በጉኘየል የስደተኛ መጠለያ ጣቢያ እንዲጠለሉ ተደርጓል።

በደቡብ ሱዳን ያለው የጸጥታና የምግብ እጥረት ችግር ካልተቃለለ የስደተኞች ቁጥር ሊጨምር እንደሚችልም ስጋታቸውን ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅትም በፓምዶንግ ጊዜያዊ የስደተኛ መጠለያ ከ2 ሺህ በላይ ስደተኞች ተመዝግበው ወደ ጉኘየል የስደተኛ መጠለያ ጣቢያ የማጓጓዝ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

“ለስደተኞቹ ጽህፈት ቤቱ ከሌሎች ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር በመቀናጀት የምግብ፣ የንጽህ መጠጥ ውሃ፣ የጤናና ሌሎች ሰብዓዊ አገልግሎቶች እየቀረቡላቸው ነው” ብለዋል።

ቀደም ሲል የመጡትን ጨምሮ ወደ ክልል እየገቡ ያሉት የስደተኞች ቁጥር ከፍተኛ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የተሟላ ሰብአዊ አገልግሎት ለማቀረብ አስቸጋሪ ስለሆነ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ድጋፍ ሊጠናከር እንደሚገባ ጠይቀዋል።

ኢዜአ ከፅህፈት ቤቱ ያገኘው መረጃ ዋቢ በማድረግ እንደዘገበው በቅርቡ የገቡትን ጨምሮ በሰባት የስደተኛ መጠለያ ጣቢያዎች ከ413 ሺህ በላይ የደቡብ ሱዳን ስደተኞች በጋምቤላ ክልል ተጠልለው ይገኛሉ።

ኤፍ. ቢ. ሲ

Share your thoughts on this post
%d bloggers like this:
Visit Us On TwitterVisit Us On YoutubeVisit Us On Instagram