fbpx
AMHARIC

በዓለ ሆሣዕና – በመጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ ተጻፈ

ሆሣዕና ማለት የዕብራይስጥ ቃል ነው፤ “ሆሻአና” ሲባል ትርጒሙም “አቤቱ አኹን አድን” ማለት ነው፡፡

ይኽ በዓለ ሆሣዕና ከ9ኙ ዐበይት የጌታ በዓላት ውስጥ ሲኾን ኪሩቤል ሱራፌል በፍርሀት በረዐድ ኹነው ዘፋኑን የሚሸሙት ጌታ በትሕትና በአህያና በውርንጫይቱ በትሕትና ተቀምጦ እየተመሰገነ ወደ ቤተ መቅደስ የገባበት፣ የዘካርያስ ትንቢት የተፈጸመበት፣ ሕዝቡ ዘንባባ ይዘው የዘመሩበት፣ ሕፃናት በንጹሕ አንደበታቸው ሆሣዕና ብለው ያመሰገኑበት ታላቅ በዓል ነው፡፡

ይኽም ታሪክ በ4ቱ ወንጌላት ላይ ሲጻፍ በማቴ 21፡ 1 ላይ “ወደ ኢየሩሳሌምም ቀርበው ወደ ደብረ ዘይት ወደ ቤተ ፋጌ ሲደርሱ፥ ያንጊዜ ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ሁለት ላከ” ይላል፡፡

ቤተ ፋጌ ማለት የበለስ ቤት ማለት ሲኾን ከኢየሩሳሌም ወደ ኢያሪኮ በሚወስደው መንገድ አቅራቢያ ያለች ትንሽ መንደርናት፡፡

ኹሉን ዐዋቂ የኾነው ጌታም ጴጥሮስንና ዮሐንስን “በፊታችሁ ወዳለችው መንደር ሂዱ፥ በዚያን ጊዜም የታሰረችን አህያ ውርንጫም ከርሷ ጋር ታገኛላችሁ፤ ፈትታችሁ አምጡልኝ” በማለት እንደ ማዕምረ ኅቡአትነቱ (የተሰወረውን ዐዋቂነቱ) በመንደሯ ውስጥ ስለታሰሩት አህያና ውርንጫ አስቀድሞ ይነግራቸዋል፡፡

በተናቀች ግርግም በቤተልሔም በተወለደ ጊዜ ላምና አህያ ትንፋሻቸውን እንደገበሩለት፤ አኹንም በሰዎች በተናቀች አህያ በጌትነት ተቀምጦ እንዲመሰገንባት መርጧታል፡፡

ከዚያም “ማንም አንዳች ቢላችሁ ለጌታ ያስፈልጉታል በሉ፤ ወዲያውም ይሰዳቸዋል” በማለት የኹሉ ጌታ ርሱ መኾኑን አመለከታቸው፡፡

በተሰጣቸው ሥልጣነ ክህነት የሕዝቡንም የአሕዛቡን ኀጢአት የማሰር የመፍታት ሰማያዊ ሥልጣነ ክህነት የተሰጣቸው ሐዋርያትን የሕዝብ ምሳሌ የኾነችውን አህያይቱንና የአሕዛብ ምሳሌ የኾነችው ውርንጫዋንም እንዲያመጡ አዟቸዋልና።

አምጥተው “ልብሳቸውንም በእነርሱ ላይ ጫኑ”፤ በአህያዋና በውርንጫዋ ላይ ኮርቻ ሳይኾን ልብስ ማድረጋቸው ኮርቻ ይቈረቊራል ልብስ ግን አይቈረቊርምና የማትቈረቊር ሕግ ሠራኽልን ሲሉ፤

ዳግመኛም ልብስ በአካል ያለውን ኀፍረት እንዲሰውር አንተም በደላችንን የምትሰውርልን ይቅር ባይ ነኽ ሲሉ፡፡

ከኢየሩሳሌም እስከ ቤተ መቅደስ 16 ምዕራፍ ሲኾን መተርጒማነ ሐዲስ በትርጓሜ ወንጌል ላይ እንደሚገልጹት 14ቱን ጌታ በእግሩ ሲኼድ 2ቱን በአህያዋ፤ በውርንጫዋ 3 ጊዜ ቤተ መቅደሷን ዞሯል፡- 14ቱ በእግሩ መኼዱ የ10ሩ ቃላት 4ቱ የ4ቱ ኪዳናት ምሳሌ፡፡

2ቱ በአህያዋ መጓዙ የፍቅረ እግዚአብሔርና የፍቅረ ቢጽ፤ 3ቱን በውርንጫዋ ተቀምጦ ቤተ መቅደሱን መዞሩ የ3ትነቱ የአንድነቱ ምሳሌ ነበር፡፡

ጌታ ንጉሠ ነገሥት ሲኾን፤ ኪሩቤል ሱራፌል ዙፋኑን በፍርሀት በረአድ የሚሸከሙት 24ቱ ካህናተ ሰማይ ዙፋኑን በፍርሀት የሚያጥኑለት ርሱ በትሕትና የዋህ ኾኖ በተናቁት በአህያና በውርንጫይቱ ላይ ተቀመጠ፡፡

ይኽም የተናቁትን ሊያከብር እንደመጣና፤ በየዋሀን ምእመናን ልቡና እንደሚያድር ለማሳወቅ በነርሱ ተቀመጠ፤ በአህያ የተቀመጠ አባሮ እንደማይዝ ሸሽቶ እንደማያመልጥ ርሱም ካልፈለጉት እንደማይገኝ ከፈለጉት እንደማይታጣ በምስጢር አመለከታቸው፡፡

ቅ.ዮሐንስ አፈወርቅ፡- ስለዚኽ ነገር በትርሜ ወንጌሉ ላይ “እነዚኽ እንስሳት መላውን የሰው ልጅ ይወክላሉ፡፡
ኹለቱም አህያ መኾናቸውም የሰው ልጅ ክርስቶስ ከመምጣቱ በፊት የነበረውን አኳኋን የሚያስረዳ ነው፡፡

ምክንያቱም አህያ በኦሪቱ ዘንድ ንጹሕ እንስሳ አይደለችም፤ ብዙ ክብደት ያላት የማትወደድ እንስሳ ናት፤ ደካማ ናት፡፡

ሰውም እንደተናገርን ክርስቶስ ከመምጣቱ በፊት እንዲኽ ነበረ፡፡” በማለት አመስጥሯል፡፡

ሊቁ ቅ. ቄርሎስ ዘእስክንድርያም፡- “ፈጣሬ ኵሉ እግዚአብሔር ሰውን በምድር ላይ ጠቢብ አድርጐ ፈጥሮት ነበር፡፡

ማሰብና ማሰላሰል የሚችል ፍጥረት አድርጐ ፈጥሮት ነበር፡፡ ሰይጣን ግን አታለለው፡፡ ምንም እንኳን ሰው በሥላሴ አምሳል ቢፈጠርም መልኩን አበላሸው፡፡

ፈጣሬ ኵሉ እግዚአብሔርን ማወቅ ተሳነው፡፡ ክፉው ሰይጣን ሰውን እንስሳ እስኪመስል ድረስ ክብሩን አዋረደው፡፡ መዝሙረኛው ዳዊት፡- “ሰውስ ክብሩን አላወቀም፤ የሚጠፉ እስሳትን መሰለ” ያለውም ስለዚኹ ነው /መዝ.49፡12/፡፡

በመኾኑም አህያይቱ ክብራቸውን አጥተው ተዋርደው የነበሩትን እስራኤል ዘሥጋን ትመስላለች፡፡

እስራኤል ከሕጉ ጥቂት ነገርን ያውቃሉ፡፡  ከነቢያትና ከቅዱሳንም ትንሽ ያውቃሉ፡፡

ከኹሉም በላይ ደግሞ ወደ አሚን የሚጠራቸውን ክርስቶስን አልታዘዙትም፡፡ “እኔ የዓለም ብርሃን
ነኝ” ሲላቸውም እንደምን እንደ አህያይቱ በድንቁርና ተይዘው እንደነበረ ሲገልጥላቸው ነው፡፡ ውርንጫይቱ ደግሞ አሕዛብን ትወክላለች፡፡

ውርንጫ እኽልን ለመጫን እንደማታገለግል ኹሉ አሕዛብም ማኅደረ እግዚአብሔር ከመኾን ርቀው ነበርና፡፡” በማለት ገልጽዋል፡፡

ሊቁ ጀሮምም፡- “ደቀ መዛሙርቱ አህያይቱንና ውርንጫይቱን ለመፍታት ኹለት ኾነው መላካቸው ለሕዝብም ለአሕዛብም መላካቸው ያመለክታል፡፡”

ሊቁ አምብሮስ፡- “አህያየቱን ለመፍታት ማንም አይከለክላችኁም ብሎ መላኩ ጌታ ለደቀ መዛሙርቱ የሰጣቸው ሥልጣን ሰማያዊ መኾኑ ያመለክታል፡፡” በማለት ልዩ ምስጢርን አስተላፎበታል፡፡

ያን ጊዜ ከሕዝቡም እጅግ ብዙዎች ልብሳቸውን በመንገድ ላይ አነጠፉ ይኽንም ማድረጋቸው ስንኳን አንተ የተቀመጥኽባት አህያ መሬት መርገጥ አይገባኽም ሲሉ ነበር፤ ሌሎችም ከዛፍ ጫፍ ጫፉን እየቈረጡ በመንገድ ላይ ያነጥፉ ነበር፡፡

ይኽም ዘንባባ ብዙ ምሳሌ ያለው ነው፤ ይኸውም በእስራኤል ያለው ሰሌን፣ ተምር፣ ዘይት ነበርና ያነን ቈርጠው አመስግነውታል፤ ይኽም ምሳሌነት ያለው ነው፡፡

ይኽም ሰሌን እሾኻማ እንደኾነ ትእምርተ ኀይል ትእምርተ መዊእ አለኽ ሲሉ ነው፤ እሳት ለብልቦ ይተወዋል እንጂ እንደማያቃጥለው ባሕርይኽ አይመረመርም ሲሉ ነበር፡፡

ዳግመኛም ከሰሌን ዝንጣፊ ጋር ተመሳሳይ ተምር ይዘዋል ይኽም ተምር ልዑል ነው አንተም ልዑለ ባሕርይ ነኽ ሲሉ፤ ፍሬው አንድ እንደኾነ አንተም ዋሕደ ባሕርይ ነኽ ሲሉ፡፡

በእሾኽ የተከበበ ነው ባሕርይኽ አይመረመርም ሲሉ ነበር፡፡

የዘይት ዛፍ ነው ቢሉ ዘይት ጽኑዕ እንደኾነ ጽኑዐ ባሕርይ ነኽ ሲሉ፤ ብሩህ ነው ብሩሀ ባሕርይ ነኽ በትምህርትኽም የሰውን ልቡናን ታበራለኽ ሲሉ፤ ዘይት መሥዋዕት እንደሚኾን መሥዋዕት ትኾናለኽ ሲሉ ነበር፡፡

“የሚቀድሙትም ሕዝብ የሚከተሉትም ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው፤ ሆሣዕና በአርያም እያሉ ይጮኹ ነበር” በማለት በአርያም መድኀኒት እንደኾነና እግዚአብሔር አብ “የምወድደው ልጄ ይኽ ነው” ብሎ መስክሮለት የመጣው ኢየሱስ ክርስቶስ መርገመ ሥጋ መርገመ ነፍስን የሚያርቅ በረከተ ሥጋን በረከተ ነፍስን የሚያድል መኾኑን ኹሉም መሰከሩለት፡፡

በእጅጉ የሚደንቀው የ40 ቀን የ80 ቀን ሕጻናት የፈጠራቸው ጌታ በአህያና በውርንጫ ተቀምጦ ባዩት ጊዜ በንጹሕ አንደበታቸው አንደታቸው ረቶላቸው ጌታን ዘንባባ በመያዝ ሲያመሰግኑ በእጅጉ ይደንቅ ነበር፡፡

ነገር ግን ጸሐፍት ፈሪሳውያን ያደረገውን ድንቃ ድንቅ በመቅደስም ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ እያሉ የሚጮኹትን ልጆች ባዩ ጊዜ፥ ተቈጥተው እነዚህ የሚሉትን አትሰማምን? አሉት፤ ኢየሱስም፦ እሰማለሁ፡፡

ከሕፃናትና ከሚጠቡት አፍ ምስጋናን ለራስህ አዘጋጀህ የሚለውን ቃል ከቶ አላነበባችሁምን? በማለት በሕጻናት እንደሚመሰገን የነርሱም ጌታ መኾኑን ከዳዊት መዝሙር በመጥቀስ ነገራቸው፡፡

ሊቁ ያዕቆብ ዘሥሩግ ሰለዚኽ ምስጢር ሲገልጸው ፡- “ፍቅርኅ ከዘባነ ኪሩብ አውርዶ በአህያ ዠርባ ላይ እንድትቀመጥ አስገደደኽ፡፡ ብዙ ዐይንና ብዙ ገጽ ካላቸው ከሰራዊተ መላክእት ይልቅ በዲዳዋ አህያ ትመሰገን ዘንድ ወደደክ፡፡

በሰማይ ሰራዊት ሠረገላ ተቀምጠኅ ክብርኽን ማሳየት አልወደድክም፤ በውርንጫይቱ ላይ ተቀምጠኅ ወደ ሰማይ ሠራዊት መኼድን መረጥክ እንጂ፡፡ በአርያም እሳታውያን የሚኾኑ ኪሩቤል ያመሰግኑኻል፤ በምድርም ሕፃናት ይዘምሩልኻል፡፡

በአርያም ብርሃናውያን መላእክት በብርሃን ክንፋቸው መንገድኽን ያነጥፉልኻል፤ በምድርም ደቀ መዛሙትኽ ልብሳቸውን አንጥፈው መንገድኽን አስተካከሉ፡፡ ወዮ! አርያማዊ ሲኾን ምንም ሳይንቀን ይጐበኘን ዘንድ ከአባቱ መጣ፡፡

እርሱም በገዛ ፈቃዱ ሰው እስከ መኾን ደርሶ መጣ፡፡ በአህያ ላይ ተጭኖም ይጐበኘን ዘንድ መጣ፡፡ ነቢዩ ዘካርያስ የመንፈስ ቅዱስን እንዚራ ይዞ በደስታ ትንቢትን ለመናገር ይቻኰላል፡፡ እየደረደረም የጽዮንን ልጅ ይጠራታል፡፡” በማለት አስተምሯል፡፡

የምስጋና ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በአህያዋና በውርንጫዋ ላይ ተቀምጦ ሕፃናትን ጨምሮ ዘንባባ ሰሌን በያዙት ኹሉ “ሆሣዕና በአርያም” እየተባለ እየተመሰገነ ወደ ቤተ መቅደስ የገባበትን ታላቁን በዓል ከኹሉም ዓለም አስበልጣ በታላቅ ክብር የምታከብርና የምታስተምረው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡

ይኸውም ታላቁ የምስጋና ዕለት ሊደርስ ሲቃረብ ስንዱዋ እመቤት አስቀድማ በቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ የቊርባን ምስጋና “ቦአ ኀቤሃ እግዚአ አጋዕዝት ወመናፍስት እንዘ ይጼዐን ዕዋለ አድግ ትሑት…

” (የአጋዕዝትና የመናፍስት ጌታ በተዋረደ አህያ ግልገል ተቀምጦ ወደ ርሷ ገባ፤ በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ ብሩክ ነው፡፡

አንተም የአማልክት አምላክ የእስራኤልም ንጉሥ እግዚአብሔር ቡሩክ ነኽ እያሉ ለሚያመሰግኑ ሕፃናት ኹሉ ጌትነቱን አሳየ፤ የሆሳዕናን ዑደት ለነርሱ ለደቀ መዛሙርቱ አሳየ፤ ቡርክ ርሱ በታላቅ ቃል እየጮኻችኊ ሆሣዕና በአርያም በሉ አላቸው፡፡

ሆሣዕና በአርያም ሆሣዕና በአርያም ሆሳዕና በአርያም፤ ከመድኀኒትነቱ የተነሣ ከዚኽ አስቀድሞ ያልተደረገ ከዚኽም በኋላ የማይደረግ ተአምራትንና መንክራትን አሳየ፤ ሆሣዕና በአርያም ሆሣዕና በአርያም ሆሳዕና በአርያም… ) በማለት መድኀኒትነቱን ስትሰብክ ካህናትና ምእመናንም በአንድ ድምፅ በዚያ ዘመን የምስጋና ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በተመሰገነበት በዚኽ ልዩ ምስጋና “ሆሣዕና በአርያም ሆሣዕና በአርያም ሆሣዕና በአርያም” እያሉ በመዘመር፤ ፈጣሪያቸው ክርስቶስን ያመሰግናሉ፡፡

ከዚያም በዋዜማው “በዕምርት ዕለት በዓልነ ንፉሑ ቀርነ በጽዮን ወስብኩ በደብረ መቅደስየ እስመ ይቤ ዛቲ ዕለት በዓለ እግዚአብሔር ሆሣዕና በአርያም ቡሩክ አንተ ንጉሠ እስራኤል” (በታወቀች በበዓላችን ዕለት በጽዮን መለከትን ንፉ፤ በመቅደሴ ተራራም ስበኩ ይኽቺ ዕለት የእግዚአብሔር በዓል ናት፡፡

በአርያም መድኀኒት የተባልኽ የእስራኤል ንጉሥ አንተ ቡሩክ (መርገመ ሥጋ መርገመ ነፍስን የምታርቅ በረከተ ሥጋ በረከተ ነፍስን የምታድል) ነኽ) በማለት ልዩ ምስጋናዋን ዠምራ ሌሊቱ ድረስ በልዩ ምስጋና እየሰበከችው በኋላም ቤተ መቅደሱን በውርጫዋ ተቀምጦ እንደዞረ በአራቱ መኣዝን የጌትነቱ ወንጌል እየተነበበ፤ ካህናቱን ምእመናንም በእጃቸው የዘንባባ ዝንጣፊን ይዘው “ሆሣዕና በአርያም ሆሣዕና በአርያም ሆሣዕና በአርያም” እያሉ ያመሰግኑታል፡፡

Share your thoughts on this post
%d bloggers like this:
Visit Us On TwitterVisit Us On YoutubeVisit Us On Instagram