fbpx
AMHARIC

በኡጋንዳ ‹ጥንቆላን ያበረታቱ › 23 የሬዲዮ ጣቢያዎች ተዘጉ

በኡጋንዳ የመገናኛ ብዙሃን መስፈርቶችን ባለማሟላታቸው እና ከህግ ውጭ በመስራታቸው ምክንያት 23 የሬዲዮ ጣቢያዎች ከስራ እንዲታገዱ መደረጋቸውን ቢቢሲ ዘገበ ፡፡

የኡጋንዳ ኮሚዩኒኬሽን ኮሚሽነር ለምስራቅ አፍሪካ የዜና ወኪል እንደተናገሩት 23 የሃገሪቱ የሬዲዮ ጣቢያዎች የጥንቆላ ማስታወቂያዎችን በማስተናገዳቸው ምክንያት እንዲዘጉ ተደርገዋል ብለዋል፡፡

የሬዲዮ ጣቢያዎቹ ዝቅተኛ የስርጭት መስፈርቶችን እንዳላሟሉ የተናገረው ኮሚሽኑ በ 2014 ከጥንቆላ ማስተዋወቅ ጋር ተያይዞ ማስጠንቀቂዎች ቢሰጣቸውም ትዕዛዙን ችላ ማለታቸው ታውቋል ፡፡

ኮሚሽነሩ አያይዘው እንዳሉት ጣቢያዎቹ በሬዲዮ ድራማ እያዋዙ ድርጊቱን በይበልጥ ለማስፋፋት ጥረት ማድረጋቸው በመረጋገጡ እና ህዝቡን ለአጭበርባሪዎች በማጋለጣቸው መንግስት እርምጃውን ለመውሰድ ተገዷል ብለዋል፡፡

የኮሚሽኑ ቃል አቀባይ የሆኑት ፓሜላ አንኩንዳ ለምስራቅ-አፍሪካን የዜና ወኪል እንደተናገሩት የሬዲዮ ጣቢያዎቹ የሚጠበቁባቸውን መስፈርቶች ለማሟላት ከተስማሙ ወደ ስራ ይመለሳሉ ፡፡

በኡጋንዳ 270 የሬዲዮ ጣቢያዎች የተቋቋሙ ሲሆን ማስታወቂያ ለመሳብ ሲባል በሚያደርጉት ያልተገባ ፉክክር መሠረታዊ መስፈርቶችን እየጣሱ መሆናቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

Share your thoughts on this post
%d bloggers like this:
Visit Us On TwitterVisit Us On YoutubeVisit Us On Instagram