AMHARIC

በትግራይና አማራ ክልል የእግር ኳስ ክለቦች መካከል የሚደረጉ ውድድሮችን በሰላማዊ ሁኔታ ለማካሄድ የሚያስችል ቅድመ ዝግጅት ተደርጓል- ዶ/ር ደብረፅዮን

By Habesha Times

December 24, 2018

በትግራይና አማራ ክልል የእግር ኳስ ክለቦች መካከል የሚደረጉ ውድድሮችን በሰላማዊ ሁኔታ ለማካሄድ የሚያስችል በቂ ቅድመ ዝግጅት መደረጉን የትግራይ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት አስታወቀ።

ባለፈው ዓመት በስፖርታዊ ጨዋነት መጓደል ምክንያት በትግራይና አማራ ክልል የእግር ኳስ ክለቦች መካከል ሲካሄድ የነበረው ውድድር በገለልተኛ ሜዳ ሲስተናገድ መቆየቱ ይታወሳል።

ይሁን እንጅ የኢትዮጵያ የእግር ኳስ ፌዴሬሽን ከሁለቱ ክልሎች ርእሳነ መስተዳድሮች ጋር ባደረገው ውይይት መሰረት በ2011 ዓ.ም የሚካሄዱ ጨዋታዎች ክለበቹ በየሜዳቸው እንዲያደርጉ መወሰኑ ነው የተገለፀው።

በዚህም በሁለቱም ክልል የእግር ኳስ ክለቦች መካከል የሚደረጉ ውድድሮችን በሰላማዊ ሁኔታ ለማካሄድ የሚያስችል በቂ ቅድመ ዝግጅት መደረጉን የትግራይ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳድር ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቀዋል።

“ፖለቲካና ስፖረት መደባለቅ የለበትም” ያሉት ምክትል ርእሰ መስተዳድሩ፥ ስፖርት በራሱ ሕግና ስርዓት መሰረት መዳኘት እንዳለበት ገልፀዋል።

ስፖርታዊ ጨዋታዎችን ለፖለቲካ አላማ በማዋል ሰላም ለማደፍረስ የሚንቀሳቀሱ ሀይሎች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡም አሳስበዋል።

ክልሉ በአሁኑ ወቅት የተረጋጋ ሰላምን ከማስከበር ባለፈ በህዝብ የሚነሱ የልማትና የመልካም አስተዳድር ጥያቄዎች ለመመለስ ጥረት እያደረገ መሆኑንም ገልፀዋል።

ስለሆነም በስፖርታዊ ጨዋታዎች ወቅት በሚፈጠሩ ችግሮች ምክንያት በትግራይ ክልል የሚፈጠር የሰላም መደፍረስ የለም ነው ያሉት።

ጨዋታዎች በተያዘላቸው መርሃ ግበር መሰረት እንዲከናወኑም የፀጥታ ሃይሎች፣ የስፖርት አመራሮች፣ ፣ወጣቶችና የስፖርት ማህበረሰቡ አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።

በክብሮም ተስፋይ