fbpx
AMHARIC

በተለያዩ የደቡብ ሱዳን የፖለቲካ ሃይሎች መካከል በአዲስ አበባ ሲካሄድ የነበረው ስብሰባ ተጠናቀቀ

በተለያዩ የደቡብ ሱዳን የፖለቲካ ሃይሎች መካከል አዲስ አበባ ውስጥ ለስድስት ቀናት ያክል ሲካሄድ የነበረው ስብሰባ ተጠናቋል።

የኢጋድ ምክር ቤት ሊቀመንበር እና የኢፌዲሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ በስብሰባው መጠናቀቂያ ላይ፥ ኢጋድ በስብሰባው ላይ ያቀረበው የሰላም ሃሳብ በደቡብ ሱዳን ሰላም መስፈን አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።

ለሰላም ሃሳቡ ሂደት ድጋፍ ላደረጉት ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ ለአፍሪካ ህብረት፣ ለአውሮፓ ህብረት፣ ለቻይና፣ ለጃፓን እንዲሁም አሜሪካ፣ ኖርዌይና እንግሊዝ አባል ለሆኑበት ትሮይካ ምስጋናቸውን አቅርብዋል።

በፖለቲካ ሃይሎች መካከል ውይይቱ ቢካሄድም እምርታዊ ለውጥ እንዳላስመዘገበ ጠቅሰው፥ ለውይይቱ አስተዋጽኦ ላበረከቱት የደቡብ ሱዳን ቤተ ክርስቲያናት ምክር ቤትን፣ የሴቶች እና የወጣቶች ቡድኖችን፣ እንዲሁም የስቪል ማህብረሰብ አባላትን አመስግነዋል።

በደቡብ ሱዳን የኢጋድ ልዩ ልዑክ አምባሳደር ኢስማኤል ዋይስ፣ ውይይቱ በተካሄዱባቸው ቀናት የሰላም ሂደቱን በማመቻቸት ረገድ የደቡብ ሱዳን ቤተ-ክርስቲያናት ምክር ቤት ያደረጉትን አስተዋጽኦ አድንቀዋል።

በደቡብ ሱዳን የጋራ ክትትልና ግምገማ ኮሚሽን ረዳት ተጠሪ አምባሳደር ብርሃኑ ከበደ የድርጅቱን ሊቀመንበር ወክለው ባደረጉት ንግግር፥ ኢጋድ ያቀረበው የሰላም ሃሳብ ለደቡብ ሱዳን ወሳኝ መሆኑን በመጠቆም፣ ፓርቲዎቹ ለደቡብ ሱዳን ዘላቂ ሰላም ሲሉ ችግሮቻቸውን እንዲፈቱ ጥሪ አቅርበዋል።

በቅርቡ የኢጋድ የሚኒስትሮች ካውንስል ስብሰባ ይካሄዳል ተብሎ ይጠበቃል የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ፅህፈት ቤት አስታውቋል።

Share your thoughts on this post
%d bloggers like this:
Visit Us On TwitterVisit Us On YoutubeVisit Us On Instagram