fbpx
AMHARIC

በሩጫዋ ተመስጣ በስህተት ወደ አሜሪካ ድንበር የገባችው ወጣት ለእስር ተዳርጋለች

የ19 አመቷ ፈረንሳዊት ወጣት ያጋጠማት ነገር አስገራሚም አዝናኝም ነበር።

ወጣቷ ወላጅ እናቷን ለመጠየቅ ወደ ካናዳ ካመራች በኋላ የገጠማት ነገር አስገራሚ ሆኖ አልፏል።

ነገሩ እንዲህ ወጣቷ እናቷን ለመጠየቅ ባመራችበት አካባቢ በአንዱ ቀን ሶምሶማ እያደረገች ለመንቀሳቀስ ታስብና የሶምሶማ ሩጫዋን ትጀምራለች።

እርሷ ሶምሶማ ሩጫውን የምታደርግበት ቦታ ደግሞ ካናዳ ከአሜሪካ ጋር የምታወሰንበትና ድንበር አካባቢ የሚገኘው ብሪቲሽ ኮሎምቢያ አካባቢ ነበር።

እናም ወጣቷ በዚህ ስፍራ ያሰበችውን የሶምሶማ ሩጫ እያደረገች ብዙ ከተጓዘች በኋላ፥ በሁለት ግለሰቦች እንድትቆም ይነገራትና ትቆማለች።

በወቅቱ ሩጫዋን እንድታቆም ያደረጓት ደግሞ ሁለት የአሜሪካ የድንበር ተቆጣጣሪ ቡድን ባለሙያዎች ነበሩ።

ወጣቷ ፈረንሳዊ በሩጫዋ ተመስጣ ሳታስበው ከካናዳ ወደ አሜሪካ ድንበር ዘልቃ ገብታ ነበር።

የድንበር ተቆጣጣሪ ባለሙያዎች ካስቆሟት በኋላ የአሜሪካን ድንበር በህገ ወጥ መንገድ ጥሳ እንደገባች ይነግሯታል።

እርሷ ግን ሁኔታው አጋጣሚ እንጅ ታስቦበት የሆነ አይደለም በማለት ለማስረዳት ትሞክራለች፤ በወቅቱ ደግሞ ምንም አይነት መታወቂያም ሆነ ማንነቷን የሚገልጽ ነገር አልያዘችም ነበር።

ጠባቂዎቹም ወጣቷን አስፈላጊውን ፍተሻ ካደረጉ በኋላ በቁጥጥር ስር እንድትውል ትደረጋለች።

ወጣቷ ግን ሳላውቅ በፈጸምኩት ነገር በዚህ መልኩ ልቀጣ አይገባም ብትልም ሰሚ አላገኘችም።

ከተያዘችበት አካባቢ 225 ኪሎ ሜትር ርቀት በመውሰድም ድንበር በህገ ወጥ መንገድ ጥሳ ገብታለች በሚል 2 ሳምንታትን በእስር እንዳታሳልፍ ያደርጓታል።

በተፈጠረው ሁኔታ ማልቀሷን የተናገረችው ወጣት ምልክት በሌለበት ሁኔታ ድንበር አልፈሻል በሚል 2 ሳምንት ማረሚያ ቤት መቆየቷ አግባብ እንዳልነበር ትናገራለች።

ወላጅ እናቷ ልጃቸው እንደተያዘች ሲያውቁ አስፈላጊውን ዶክመንት አቅርበው የነበረ ቢሆንም፥ በሩጫዋ ተመስጣ ድንበር የተሻገረችው ልጃቸውን 2 ሳምንት ማረሚያ ቤት ከመቆየት ግን አልታደጓትም።

በመጨረሻም ወጣቷ በሩጫ ተመስጦ ለፈጸመችው ድንበር ጥሶ ማለፍ የ2 ሳምንት የማረሚያ ቤት ቆይታዋን አጠናቃ ከወላጅ እናቷ ጋር ተቀላቅላለች።

የሃገሪቱ ድንበር ጠባቂ ቡድን ተወካዮች ግን ማንኛውም ሰው የአሜሪካን ድንበር አውቆም ይሁን ሳያውቅ አልፎ ቢገባ ከመሰል ቅጣት አያልፍ ብለዋል።

ወጣቷም ተመስጣ ባደረገችው ሩጫ ሳቢያ ድንበር ጥሳ በመግባት ባሳለፈችው የ2 ሳምንት የማረሚያ ቤት ቆይታዋ ትምህርት ማግኘቷን ተናግራለች።

 

 

ምንጭ፦ ኦዲቲ ሴንትራል

Share your thoughts on this post
%d bloggers like this:
Visit Us On TwitterVisit Us On YoutubeVisit Us On Instagram