በመዲናዋ በትንሳኤ ዋዜማና በዓል ምንም አይነት የእሳት አደጋ አልተከሰተም
(ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ በትንሳኤ ዋዜማ እና በዓል ምንም አይነት የእሳት አደጋ አለመከሰቱን ተገልጿል።
የአዲስ አበባ ከተማ እሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከልና መቆጣጣር ባለስልጣን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮፖሬት እንደገለፀው መዲናዋ ምን ዓይነት የእሳት አደጋ በሁለቱ ቀናት አልተመዘገበባትም።
ከተማዋ በአማካኝ በቀን ከሁለት ያላነሰ የእሳት አደጋ በማንኛውም ቀን ይመዘገብ እንደነበር ነው የባለስልጣን የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ንጋቱ ማሞ ያነሱት።
ስለሆነም ባለስልጣኑ አደጋዎች እንዳይከሰቱ በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን የግንዛቤ መስጫ ስራ በስፋት መስራቱን ገልፀዋል።
በዚህም በአዲስ አበባ በትንሳኤ ዋዜማ እና በዓል ምንም አይነት የእሳት አደጋ አለመከሰቱን የተናገሩት አቶ ንጋቱ፥ በዓሉ ምሽቱን ጨምሮ በድምቀት የሚከበርበት በመሆኑ አደጋው እንዳይከሰት የሚደረገው ጥንቃቄ መቀጠል ይገባዋል ብለዋል።
ድንገት አደጋ ቢከሰት በ939 ነጻ የስልክ መስመር በመደወል ለባለሰልጣኑ ማሳወቅ እንደሚገባም አቶ ንጋቱ አስገንዝበዋል።
በተያያዘ ዜና በአዲስ አበባ ያለው የትራፊክ እንቅስቃሴም ሰላማዊ መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቋል።
የኮሚሽኑ የህዝብ ግነኙነት ሃላፊ ኮማንደር ፋሲካው ፈንታ ለጣቢያችን እንደገለፁት፥ በበዓሉ ምንም ዓይነት የትራፊክ አደጋ አለመከሰቱ እና የወንጀል ድርጊትም ተፈጽሞ አልተመዘገበም ብለዋል።
ከበዓሉ አስቀድሞ ለህብረተሰቡ የትራፊክ አደጋ እንዳይከሰት ግንዛቤ እንዲኖረው በማድረግ የኮሚሽኑ የፖሊስ አባላት የሚያደረጉትን ቁጥጥር እንዲያጠናክሩ ተደረጓል ብለዋል።
ኮማንደር ፋሲካው፥ መዲናዋ አሁን ያላት ሰላማዊ እንቅሰቃሴ እንዲሳለጥ ለማድረግ የኮሚሽኑ ፖሊስ አባላት የሚያደረጉትን ክትትል እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
ምሽት ወደ ተለያዩ መዝናኛ ቦታዎች በተሸከርካሪ የሚንቀሳቀሱ ሰዎች የሚኖሩ በመሆኑ እግረኞችም ይሁን አሽከርካሪዎች ጥንቃቄ እንዲያደረጉ አሳስቧል።
አሽከርካሪዎችም የትራፊክ አደጋ እንዳይከሰት ጠጥቶ ከማሽከርከር ራሳቸውን በማራቅ አስተዋጽኦ እንዲያደሩም ጥሪ አስተላልፈዋል።