በህገ ወጥ መንገድ በመተማ በኩል ሀገር ውስጥ ሲገቡ የነበሩ 58 ክላሽ እንኮቮች ተያዙ
በመተማ በኩል ህገ ወጥ መሳሪያዎች በተለያዩ ቀናት ወደ ሀገር ውስጥ ሊገቡ ሲሉ በቁጥጥር ስር ዋሉ።
በህገ ወጥ መንገድ ወደ ሀገር ውስጥ ሲገቡ የተያዙት የጦር መሳሪያዎች 58 ክላሽ እንኮቮች እና 4 ሺህ 354 ጥይቶች እንደሆኑ የምዕራብ ጎንደር ዞን የመተማ ወረዳ ፓሊስ ፅህፈት አስታውቋል።
ግንቦት 12 ቀን 2010 ዓ.ም ከሌሊቱ ስድስት ሰዓት በመተማ ወረዳ ደለሎ ቀበሌ 33 ክላሽ እንኮቭ ጠብመንጃ 3 ሺህ 970 ጥይቶች በቁጥጥር ስር ማዋል ተችሏል።
እንዲሁም ግንቦት 13 ቀን 2010 ዓ.ም በመተማ ዮሐንስ ከተማ በመንገድ ላይ በተደረገ ድንገተኛ ፍተሻ 25 ሽጉጦች ከ384 ጥይቶች በፀጥታ አካላትና በመከላከያ ሠራዊት አባላት ቅንጅታዊ ክትትል ለመያዝ መቻሉን የጽህፈት ቤቱ ኃላፊና የኮማንድ ፖስት አባል ኢንስፔክተር አብራራው የኋላ ተናግረዋል ።
መሳሪያዎቹና ጥይቶቹን በትራክተር ጭኖ ለማስገባት የሞከሩ ሁለት አዘዋዋሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው እየተጣራ መሆኑም ነው የተመለከተው።
ሌሎች በዚህ ወንጀል የተሳተፉ አካላትን ለመያዝ ከፍተኛ ክትትል እየተደረገ እንደሆነ ታውቋል።፡፡
የድንበር አካባቢ በመሆኑ ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር በከፍተኛ ሁኔታ እንዳለ የተገለፀ ሲሆን፥ ችግሩን ለመቅረፍ ህብረተሰቡን በመሳተፍ ጥብቅ የቁጥጥር እና የክትትል ሥራ እየተከናወነ መሆኑ ተነግሯል።
ምንጭ፦ ኢዜአ