fbpx
AMHARIC

ሽንኩርቱን ውሃ በላው፤ ለአርሶ አደሩ ማን ይድረስለት?

ሽንኩርቱን ውሃ በላው፤ ለአርሶ አደሩ ማን ይድረስለት?
(ይሁኔ አየለ)

ሽንኩት በሁሉም ቦታ ሚገባ የምግብ ማጣፈጫ ቅመምምና አትክልት ነው፡፡ ለዚህም ይመስላል የሽንኩርት ዋጋ በተለይ ለከተማ ነዋሪው የራስ ምታት የሚሆነው፡፡ በዓወዳመት ወቅት የሽንኩርት ዋጋ ከበግ፣ ከዶሮና ከበሬ ጋር አብራ ትነሳለች፡፡ በሀገራችን፣ በብዛት ጥቅም ላይ ከሚውሉ ቅመሞች ሽንኩርትና በርበሬ ቅድሚያውን ይወስዳሉ፡፡ ምን አለፋችሁ፣ ሽንኩርት የምግባችን ዋና አካል ነው፡፡ ለዚህም፣ የሽንኩርት አመራረትና አምራቹ ሊደገፍና ሊበረታታ ይገባዋል፡፡ ሽንኩርት ጤና አደላዳይ ምግብ ነው፡፡ የሽንኩርትና የጤናን ዝምድና በሌላ ቀን እመጣበታለሁ፡፡ ዛሬ ግን በሽንኩርት ምርት ላይ ስለደረሰ ውድመት መረጃ አቀብላችኋለሁ፡፡

የአዋሽን ተፋሰስ ይዞ ዝዋይ ዙሪያ ሽንኩርትና ሌሎች በተለይ ቲማቲም፣ እንጆሪ፣ ፓፓያ፣ ሜሎንና አባባ ብብዛት የሚመረትበት አካባቢ ስለመሆኑ ከአዲስ አባባ ወደ ሀዋሳ ጉዞ ያደረገ ሰው ሁሉ ምስክር ይሆናል፡፡ በዚህ መንገድ ጉዞ ሲደረግ ዋናው አስደሳች ትይንት ይህ የአትክልት መሸጫና ማማረቻ ቦታ ይመስለኛል፡፡
የእሁድ ለት (10/07/2010 ዓ.ም) ጉዞዬ ግን በሀዘን የተደመደመ ነበር፣ ብዙ የሽንኩርት ማሳ በውሃ ተጥለቅልቆ ብዙ የሽንኩርት ምርት ወድሞ ያየሁበት ቀን ነበር፡፡
በምስራቅ ሸዋ ዞን፣ ቦራ ወረዳ ያሉ ሽንኩርት አምራች ገበሬዎች ማሳቸውን ውሃ ሞልቶታል፤ ሀይቅ ሰርቷል ማለት ይቻላል፡፡ የማሳው ባለቤቶች፣ ብዙ ሰው አሰማርተው ከውሃው ውስጥ ሽንኩርቱን እያስወጡ ዋናው መንገድ ዳር ይከምራሉ፡፡

ሁኔታው የተለመደ ስላልሆነ ከመኪናችን ወርደን “ምን ተፈጠረ?፣ ውሃው ከየት መጣ?” እያልን ሰራተኞችን ጠየቅን፡፡ እነሱም “ባለቤቱን ጠይቁ” አሉን፡፡ ባለቤቱ ወደ እኛ መጣ፡፡ “ምንድን ነው ነገሩ?” ብለን ጠየቅን፡፡ “ያልታሰበ ጎርፍ አጥለቀለቀን” አለን፡፡ “ለመንግስት አካላት ሪፖርት አድረጋችኋል?” ብለን ደግመን ጠየቅን፡፡ “አድርገናል፡፡ ቢሆንም፣ መጥቶ ያየን የለም” አለ፡፡ “ይህ ክስተት ዘንድሮ ብቻ ነው ወይስ ከዚህ ቀደም ተከስቶ ያውቃል?” ብለን ጠየቅን፡፡ እሱም፣ “በእኔ ማሳ ላይ እንደዚህ ያለ ነገር ሲከሰት ሶስተኛ ጊዜው ነው” አለን፡፡ “መንግስት ይህንም ያውቃል ወይ?” ብለን ጠየቅነው፡፡ “አዎ፣ ያውቃል፤ ምንም ችግር የለም የጎርፍ መከላከያ ይሰራለካችኋል፣ ማምረቱን እንዳታቋርጡ ብለውን ነበር” አለን፡፡
“ኪሳራህ ምን ያህል ሆናል?” ብለን ጠየቅነው፡፡ “አሁን መገመት አልችልም፤ አሁን እያወጣነው ያለውን ነጋዴዎች ካልተረከቡን፣ የአሁኑን (ከውሃ ውስጥ ማውጣቱን ማለቱ ነው) ሰራተኛ ጉልበትም የምንሸፍነው ገና ከኪሴ አውጥቼ ነው” አለን፡፡
አብሮኝ የነበረ ጓደኛየ ስልኩን አውጥቶ ወደ አንድ የብዙሀን መገናኛ የስራ ባልደረባ ደወለ፡፡ ከወዲያኛው ጫፍ በተሰጠው መልስ ደስተኛ ያልሆነው ጓደኛየ ተክዞ ስልኩን ሲዘጋ፤ “ምን አለህ?” አልሁት፡፡ “እሱ እኮ የተለመደ ክስተት ነው፣ አዲስ ነገር አይደለም” አለኝ ብሎ መለሰልኝ፡፡
በእኔም አእምሮ ውስጥ “ሀገሬ ሆይ፣ መቼ ይሆን ወደ አርሶ አደር ልጆችሽ ፊትሽን የምታዞሪው፣ መቼ ይሆን እነሱ የሚደመጡትና የሚረዱት፣ መቼ ይሆን በእነሱ ስም ማጭበርበር የሚቆመው?” የሚል ጥያቄ አቃጨለ፡፡
ብዙዎቻችን ሶፋ ላይ ቁጭ ብለን በሽንኩርት የጣፈጠ ዶሮ ወጥ እናጣጥማለን፡፡ ሽንኩርት እንዴት ተመርታ ለአቅመ ወጥ እንደምትደርስ ግን የምናውቅ አይመስለኛም፡፡ ሽንኩርትን ለማምረት እንደ ጀልባ በውሃ ውስጥ መነከርን ትጠይቀለች(ያውም ቆርጥሞ ከሚበላ ውርጭ ጋር)፤ ወገብ እስኪሰበር አጎንበሶ ቀኑን ሙሉ መኮትኮትን ይጨምራል፣ ሽንኩርት የምትመረተው ከአፈር ጋር በመታገል ነው፡፡ ከሽንኩርት ጥፍጥና ውስጥ አላግባብ የፈሰሰ የአርሶ አደር ላብ አለበት፡፡
እስኪ ተማርን ለምንል ሰዎች አንድ ጥያቄ ላቅርብ፣ ሁሌም ወደ አፋችን ለምንልካት ጉራሽ የእኔ አስተዋጽኦ ምን ያህል ነው?” የሚል፡፡ እኔ በበኩሌ፣ ምንም (ባዶ) ሆኖ አግኝቸዋለሁ፡፡ እድሜ ለተሸከሙኝ የኢትዮጵያ አርሶ አደሮች፡፡

ታዲያ ምን ይደረግ?
በእኔ በኩል፤
1. አርሶ አደሮች የመድህን ዋስትና ሊገባላቸው ይገባል፤
2. እንደዚህ ያለ ውድመት ሲደርስባቸው፣ መንግስት ኪሳራቸውን አስቦ እስከማበረታቻው ሊደጉማቸው ይገባል፣
3. ማሳዎቻቸው እንደዚህ ካለ የተፈጥሮ አደጋ ሊጠበቁና ቅድሚያ ጥንቃቄ ሊደረግላቸው ይገባል
4. ለምርታቸው ተመጣጣኝ ዋጋ ሊከፈላቸው ይገባል፤ ለምሳሌ አሁን ያለው የሽንኩርት ዋጋ አበረታች አይደለም፣ አርሶ አደሮች እስካልተደጎሙ ድረስ
5. እናንተ ጨምሩበት….

Share your thoughts on this post
%d bloggers like this:
Visit Us On TwitterVisit Us On YoutubeVisit Us On Instagram