fbpx
AMHARIC

ማረሚያ ቤት የፍርድ ቤት ቅጣታቸውን የጨረሱ ፍርደኞችን ከተደጋጋሚ ትዕዛዝ በኋላ ፈታ

ታምሩ ጽጌ – ሪፖርተር

በተከሰሱበት ከገቢ ግብር ጋር በተያያዘ የወንጀል ድርጊትና የንግድ ፈቃድ ሳይኖራቸው ለኢትዮጵያውን ብቻ በተፈቀደ ሥራ ላይ ተሠማርቶ መገኘት ወንጀል የቅጣት ውሳኔ የተጣለባቸው አንድ ኢትዮጵያዊና ሁለት የሴሪላንካ ዜጎችን፣ ማረሚያ ቤት ከተደጋጋሚ የፍርድ ቤት ትዕዛዝ በኋላ ፈታ፡፡

መጋቢት 7 ቀን 2010 ዓ.ም. በአምስት ዓመታት ጽኑ የእስር ቅጣትና የተለያየ መጠን ያለው የገንዘብ ቅጣት የተጣለባቸው የአካፔ ኢምፔክስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ባለድርሻ አቶ አሸረፍ አወል፣ ሁለት የሲሪላንካ ዜጎች ሄትራጅግ ያጎንታ ሱሬንድሪናታና ፕናንዎታጅ አሲታ ሳራናት ናቸው፡፡ የተወሰነባቸውን የእስራት ቅጣት በአመክሮ (በማረሚያ ቤት የነበራቸው የባህሪና ጠቅላላ ሁኔታ ግምገማ ውጤት) ቅጣታቸውን መጨረሳቸውን ለፍርድ ቤት አመልክተዋል፡፡

በወቅቱ ሳይፈቱ የቀሩት ከሳሽ ዓቃቤ ሕግ በሥር ፍርድ ቤት የተሰጠውን ቅጣት በመቃወም ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ በማቅረቡ ሲሆን፣ ይግባኝ ሰሚው ችሎት ለግንቦት 1 ቀን 2010 ዓ.ም. ቀጠሮ በመስጠቱ ነው፡፡ ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤቱ የሰጠው ትዕዛዝ ፍርደኞቹ ማረሚያ ቤት የሚገኙ መሆኑን ጠቅሶ እንዲቀርቡ እንጂ፣ የእስር ትዕዛዝ ያልሰጠ መሆኑን ለፍርደኞቹ ሚያዝያ 1 ቀን 2010 ዓ.ም. በጻፈው ደብዳቤ አሳውቋል፡፡ ፍርደኞቹ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የጻፈላቸውን ደብዳቤ ይዘው ለሥር ፍርድ ቤት ሲያመለክቱ፣ ፍርድ ቤቱ የታራሚዎች ጥበቃና ደኅንነት አስተዳደር ዘርፍ አስተባባሪ ዋና ኦፊሰር አላምረው ተረፈን ጠርቶ አነጋግሯቸዋል፡፡

ፍርደኞቹ አመክሮ የሚያገኙበት ወይም የሚያስከለክል ችግር እንዳለባቸውና እንደሌለባቸው የተጠየቁት አስተባባሪው፣ የሚያስከለክል እንደሌለ ምላሽ ሰጥተው መፍታት ያልቻሉት ግን ፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፍርደኞቹ ግንቦት 1 ቀን 2010 ዓ.ም. እንዲቀርቡ ትዕዛዝ በመስጠቱ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ በሰጣቸው ምላሽ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ‹‹ይቅረቡ›› እንጂ፣ ‹‹እንዳይፈቱ፤›› የሚል ትዕዛዝ ስላልሰጠ፣ በዕለቱ ሚያዝያ 17 ቀን 2010 ዓ.ም. እንዲፈቱ ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር፡፡

ማረሚያ ቤቱ እስከ ሚያዝያ 19 ቀን 2010 ዓ.ም. ባለመፍታቱ የፍርደኞቹ ጠበቆች፣ ደንበኞቻችንን ማረሚያ ቤቱ ሊፈታልንና የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ ሊፈጽም ስላልቻለ፣ በኃላፊዎቹ ላይ ዕርምጃ ተወስዶ ዛሬውኑ እንዲፈቱ ትዕዛዝ ይስጥልን የሚል አቤቱታ ለፍርድ ቤቱ አቅርበዋል፡፡ ፍርድ ቤቱም ሌላ ትዕዛዝ የሰጠ ቢሆንም፣ ማረሚያ ቤቱ ግን አቶ አሸረፍ አወልን ሐሙስ ሚያዝያ 19 ቀን 2010 ዓ.ም. ከሰዓት በፊት ሊፈታቸው በመቻሉ ትዕዛዙ ቀሪ መሆኑ ታውቋል፡፡ ሁለቱ ሲሪላንካውያን ከአገር እንዳይወጡ ዕግድ የተጣለባቸው ከመሆኑ አንፃር ከእስር ቢፈቱ በምን ሁኔታ መቆየት እንደሚችሉ ከሕግ አንፃር መርምሮ ለመወሰን፣ ለሚያዝያ 23 ቀን 2010 ዓ.ም. የተሰጠው ቀጠሮ እንደተጠበቀ ቀጥሏል፡፡

የሥር ፍርድ ቤት አቶ አሸረፍ አወል አምስት ዓመታት ጽኑ እስራትና 80,000 ብር፣ ድርጅታቸው አካፔ ኢምፔክስ 15,000 ብር፣ ሁለቱ የውጭ ዜጎች እያንዳንዳቸው 100,000 ብርና አምስት ዓመታት ፅኑ እስራት እንዲቀጡ መወሰኑን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

Share your thoughts on this post
%d bloggers like this:
Visit Us On TwitterVisit Us On YoutubeVisit Us On Instagram