fbpx

HT

ሐበሻ ታይምስ ሚዲያ

AMHARIC

ፌዴሬሽኑ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጥያቄ ያልተቀበለው ለምን ይሆን?

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ዘንድሮ በዳላስ ከተማ በሚካሄደው 35ኛው የባህል እና ስፖርት ፌስቲቫል ላይ እንዲገኙ ብሎም ንግግር እንዲያደርጉ የቀረበለትን ጥያቄ የኢትዮጵያዊያን የስፖርት ፌዴሬሽን በሰሜን አሜሪካ ሳይቀበለው ቀርቷል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቀጣይ በሚደረጉ ፌስቲቫሎች ላይ መገኘት እንደሚችሉ ግን ፍንጭ ሰጥቷል።

የፌዴሬሽኑ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ እያዩ ዘነበ ለቢቢሲ እንደተናገሩት እዚህ ውሳኔ ላይ ለመድረስ የአምስት ሰዓታት ውይይትና የሶስት ቀናት የሚስጢራዊ ድምጽ አሰጣጥን ተከትሎም፤ የቦርድ አባላት በሰጡት ድምፅ ብልጫ መሰረት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፌስቲቫሉ ላይ እንዳይገኙ ተወስኗል።

ከዚህ ውሳኔ ባሻገር ግን የፌዴሬሽኑ አብዛኞቹ የቦርድ አባላት ጥያቄው በመቅረቡ ክብር እንደተሰማቸው፣ ፌዴሬሽኑ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ለመጪው የኢትዮጵያ ትውልድ አብሮነት ሲል የሚያደርጉትን ሰላማዊ ንግግር እንደሚደግፍም አስታውቋል።

«ዶክተር አብይን እያበረከቱት ላለው ለውጥ እንደግፋቸዋለን፣» ያሉት ሃላፊው፣ ሆኖም የፌስቲቫሉ መርሃ -ግብር ተደራጅቶ ካለቀ በኋላ ጥያቄው በመቅረቡ ፣ ታዳሚዎችን ለማስተናገድ የተዘጋጀው ስፍራ አቅም ከማነስ ጋር የተገናኙ የ’ሎጀስቲክ’ ችግሮች እና ተጨማሪ ምክንያቶች ተደምረው ጥያቄው በቦርድ አባላት ዘንድ ውድቅ እንደተደረገ ተናግረዋል።

በተለይም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሊፈጥሩት የሚችለውን ትኩረት ተከትሎ ፌስቲቫሉ የሚደረግበት ስታዲየም የሚመጣውን ህዝብ ለማስተናገድ እንደሚቸግርም አስታውቀዋል።

በተጨማሪም ፌዴሬሽኑ በኦፊሴላዊ ድረ-ገፁ ላይ የእንግዶች እና ታዳሚዎችን ደህንነት ለመጠበቅ ተጨማሪ እርምጃዎችን ለመውሰድ ጊዜው አለመፍቀዱን በዋና ምክንያትነት አስቀምጧል።

የቦርድ አባላት እዚህ ውሳኔ ላይ ከመድረሳቸው በፊት -የጠቅላይ ሚኒስትሩ መምጣት ባለው ፋይዳ እና ጉዳት ላይ መወያየታቸውን ይናገራሉ።

የፎኔክስ አሪዞና ቡድን ተወካይ ረድኤት ባይለየኝ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፌስቲቫሉ ላይ እንዲገኙ ቢፈቀድ መልካም ነው ከሚሉ ወገኖች አንዱ ነበሩ።

“ከእሳቸው ጋር አንድ ተፎካካሪ ተገኝቶ ንግግር ቢያደርጉ በኢትዮጵያዊያን ዘንድ ትልቅ መነቃቃት ይፈጠራል።እንደኔው በተመሳሳይ ድምፅ የሰጡ ሰዎች የተገነዘብነው ኢትዮጵያ ውስጥ እየተሰማ ያለ ወደ ዲሞክራሲ የሚወስድ እንቅስቃሴ አለ።ይሄንን መድረክ በመጠቀም የምትቻለንን ጋት ለመጨመር ሚናም ለመጫወት ካለው ፋይዳ አንፃር ነበር ጉዳዩን ያየነው» ይላሉ።

የተሰጠውን ውሳኔ እንደሚያከብሩ የሚናገሩት አቶ ረድኤት ውሳኔው የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጥያቄ ሙሉ በሙሉ ውድቅ እንደማድረግ ሳይሆን በሌላ ጊዜ እንዲተለላፈ ቀጠሮ እንደሚቆጥሩት አጋርተውናል።

ቢቢሲ ያናገራቸው የቦርድ አባላት “ግልጽና መግባባት የሰፈነበት ነው” ያሉት ምርጫ ውጤት ይፋ ከተደረገ በኋላ ፤ ይህ ውሳኔ የብዙዎችን ስሜት መከፋፈሉ በተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያዎች እየተንፀባረቁ ነው።

ይሄ የተቀላቀለ ምላሽ የ የቦርድ አባላትን ልብ አሻክሮ -ለፌዴሬሽኑ ህልውና ስጋት ይሆን የሚሉ ጥያቄዎችንም አጭረዋል።

የኢትዮ ዳላስ ቡድን ተወካይ የሆኑት ዘውገ ቃኘው የፌዴሬሽኑ የቀደመ- ልምድ ባህል ለዚህ ስጋት መፍትሄ እንደ ሆነ ይናገራሉ።

ከሶስት አስርት ዓመታት በላይ ባስቆጠረው በዚህ ድርጅት ፈታኝ ነገሮች ተደቅነውበት እንደነበር አቶ ዘውገ ይናገራሉ።

«የአሁኑ ጉዳይ የተለየ ቢመስልም ድርጅቱ መሰል ችግሮችን በሚችለው እና አቅሙ በሚፈቀደ መልኩ ሲፈታ ግን የመጀመሪያው አይደለም» የሚሉት አቶ ዘውገ “እንደ አሁኑ በዲሞክራሲያዊ መንገድ ውይይት ተደርጎ በስርዓት የተሰጠ ውሳኔ በቦርዱ አባላት ዘንድ ምንም አይነት ችግር አያመጣም” ይላሉ።

የፌዴሬሽኑ ሊቀመንበር አቶ አብይ ኑርልኝ ከ30 በላይ የሆኑ ተሳታፊ ቡድኖች የቦርድ አባላት በሚሰጡት ድምጽ፣ በአብላጫ ድምጽ በጉዳዩ ላይ ውሳኔ እንደሚሰጥ ለቢቢሲ ከቀናት በፊት አስታውቀው ነበር። BBC Amharic

Share your thoughts on this post
%d bloggers like this:
Visit Us On TwitterVisit Us On YoutubeVisit Us On Instagram