fbpx
AMHARIC

ፉከራ ይቀንስ፣ ወዮልህ/ወዮልሽ ይቀንስ – ኤፍሬም እንዳለ

ፉከራ ይቀንስ፣ ወዮልህ/ወዮልሽ ይቀንስ
(ኤፍሬም እንዳለ)

“ጤና ይስጥልኝ፣ ኤፍ.ኤም. ነው?”
“አዎ፣”
“በተነሳው ጉዳይ ላይ አስተያየት ለመስጠት ነበር፡፡”
“እሺ ጌታዬ፣ እርሶን ማን እንበል…”
“ግዴለም ስሜ ይቆይልኝ…”

‘ስሜ ይቆይልኝ’ የምትል አባባል አለች… ሁለት ቃላት፣ ብዙ ትርጉም፡፡ ሰዎች በትንሹም ነገር ቢሆን ሃሳባቸውን ለመስጠት ምን ያህል እንደሚሳቀቁ ነው፡፡

እና ገና ለገና ይተረጉምባኛል እየተባለ እኮ ሀሳባችንን አምቅን እነኖራለን…

አንደ ሰሞን ሁለት ጣት ነጥሎ ማሳየት መከራ ሆኖ ነበር፡፡ የሁለት ጣት የ‘ቪ’ ምልክት የነበረ፣ ያለና የሚኖር ነው፡፡ ግን ደግሞ ነገሩ ምልክቱን የሚያሳየው ሰው እንዳሰበው ሳይሆን ተመልካቹ እንደሚተረጉመው ሆነና ታክሲ ስናስቆም ሦስት ጣት እያሳየን “ሁለት ሰው መገናኛ፣” ስንል ከርመናል፡፡ ይሄን ያህል መሳቀቅ ይገባን ነበር እንዴ! እንደዚህ ገሚሶቻችን በተለያዩ መንገዶች አስፈራሪ፣ ለሌሎቻችን ደግሞ ፈሪ የምሆንበት ግንኙነት እስክመቼ ነው የሚቀጥለው!

ፉከራ ይቀንስ! ‘ወዮልህ/ወዮልሽ’ ይቀንስ!

ባለፈው ዘመን የሆነ ነው፡፡ አንድ መሥሪያ ቤት ሰውየው የደሞዝ ጥያቄ ሲያቀርቡ ሁልጊዜም ተመሳሳይ መልስ ይሰጣቸው ነበር፡፡ “ደሞዝ ከተጨመረልኝ እኮ ብዙ ጊዜ ሆነ” ሲሉ … “ኢትዮዽያ እየደማች እንዴት አንተ ደሞዝ ይጨመርልኝ ትላለህ!” ይባላሉ፡፡ ደግመው ሲሄዱ መልሱ ያው ነው፡፡ በሌላ በኩል ግን ለሌሎች ደሞዝ ይጨመርላቸዋል፡፡

በመጨረሻ እንዲሁ ጠይቀው ተመሳሳይ መልስ ሲሰጣቸው ምን ቢሉ ጥሩ ነው…

“ኢትዮዽያ የምትደማው ለእኔ ደሞዝ ጭማሪ ጊዜ ነው እንዴ!” አሉ፡ በዛ አባባላቸው ትንሽ ግርግር ቢጤ ገጥሟቸው ነበር፡፡ እንደውም አንድ ሰሞን እንድ ተቃውሞ ቢሯቸው በር ላይ የአህያ ስዕል ለጥፈው ነበር፡፡ በዛም የተነሳ “አርፈህ ተቀመጥ!” አይነት ነገር ደርሶባቸዋል ይባላል፡፡

ሰውየው የደሞዝ ጥያቄ ያቀረቡት መብታቸው ስለሆነ ነው፡፡ ከሌላው ሠራተኛ የተለየ አስተያየት ይደረግልኝ አላሉም፡፡ “ለሌላው የተደረገው ለእኔም ይደረግልኝ፣” ነው ያሉት፡፡ ግን ጥያቄያቸው ከአገር ህልውና ጋር እየተያያዘባቸው፣ በተለምዶ እንደሚባለው፣ ‘አመዳቸው ቡን’ እንዲል ሲደረግ ነበር፡፡

ዘንድሮም በትንሽ ትልቁ የሰዎችን ‘አመድ ቡን’ ለማድረግ ሲሞከር እናያለን፡፡ ሰዎች መብታቸውን ስለጠየቁ፣ “በዜግነቴ አገልግሎት ይስጠኝ” ስላሉ ‘አመድ ቡን’ የሚያደርጕ ነገሮች ይወረወሩባቸዋል፡፡

በተለይም በአስተዳደር እርከኑ ወደታች ሲወረድ የ“አርፈህ ተቀመጥ” ቀጥተኛም ሆነ ተዘዋዋሪ ማስፈራራቱ ይብሳል፡፡ ሰሞኑን ከስልጣን መሰላሉ ላይኛው አካባቢ የተለያዩ ነገሮች እየሰማን ነው፡፡ “እውነትም የሚተገበር ከሆነ ሸጋ ነው፣” እያልን እየሰማን፣ እያየንም ነው… ባቡሩ የከሰል ባቡር ይሁን፣ የነዳጅ ባቡር ይሁን፣ የአሌትሪክ ባቡር ይሁን እስኪለይልን እየጠበቅን፡፡ ገና ለዓመታት ሰምተን የማናውቃቸው ነገሮች ስንሰማ ተስፋችን ‘ጠበል ጠዲቁ’ ሁላችን ዘንድ ይደርሳል የሚል ነው፡፡

በዚህ ሁሉ መሀል ግን… ወረድ እየተባለ ሲኬድ የሚገጥሙ ነገሮች በዚህ ከቀጠሉ “ድሮም ቢሆን እንደማይሆን አውቀነው ነበር፣” ወደሚባል ደረጃ እየገፉን ነው፡፡ መንገዱ ተቆፋፍሮ ሰዉ መግቢያ መውጫ ሲያጣና “ኸረ የምንተላለፍበት እንኳን አዘጋጁልን!” ሲባል…

“እናንተ ልማቱን አትደግፉም ማለት ነው፣” አይነት የቃላት ሚሳይል ይለቀቃል፡፡ ይሄ ነገር መብቃት የለበትም እንዴ! ሰዉ በየአገልግሎት መስጫው ሃሳቡን ሲገልጽ “ጃስ!” አይነት ማስፈራራት መቆም የለበትም እንዴ!

ፉከራ ይቀንስ! ‘ወዮልህ/ወዮልሽ’ ይቀንስ!

በነገራችን ላይ በየአስተዳደር ቢሮው የሚቀመጡ ሰዎች ማወቅ ያለባቸው ተቀጣሪ ደሞዝተኞች መሆናቸውን ነው፡፡ አለቀ፣ ይሄ ምንም ምእራፍ ሁለት፣ ሲዝን ሰባት ምናምን ነገር የሚያስፈልገው አይደለም፡፡ አሳሳቢው ነገር…የሌኒንና የማርክስ የሙሉ ውክልና ሰነድ ያላቸው ይመስል ነገሮችን ሁሉ ፖለቲካዊ ቀለም መቀባት የሚወዱ እንዳሉ ነው፡፡ የእንትን ክፍለ ከተማን ሥራ አስፈጻሚ ተገልጋዩ የሚያወቀው እንደ ሥራ አስፈጻሚ ነው፡፡

ከእሱም የሚጠብቀው የተጣለበትን ሃላፊነት በብቃት እንዲወጣ ነው፡፡ ይኸው ነው! ‘ኔኦ ሌበራል’ የሚባለው ነገር ይሁን፡ ‘ዘውድ ናፋቂ’ ይሁን ሥራውን እስከሠራ ድረስ የራሱ ጉዳይ ነው፡፡ ምናምንዴድ ይሁን፣ ምናምን ህብረት ይሁን፣ ምናምን ግንባር ይሁን ሥራውን እስከሠራ ድረስ የራሱ ጉዳይ ነው፡፡ እናም ባለስልጣኑ ከተገልጋዮቹ ጋር ያለው ግንኙነት በሥራ አስፈጻሚነት በተቀጠረበት የሥራ ዘርፍ ነው፡፡

ችግሩ የሚመጣው ሰዎች ከሙያዊ ግዴታቸው ይልቅ ፖለቲካዊ ሰባኪነታቸው ሲብስ ነው፡ ደግሞም እኮ “የአሳምነኝ ላሳምንህ” ሀሳቦች የሚነሸራሸሩበት ፖለቲካ ሳይሆን እነደ ረጅም ማስፈራያ ዱላ መሆኑ ነው፡፡ “መመላሻ አጣን፣” “ለጆቻችንን ትምህርት ቤት መውሰጃ አጣን፡” “ታማሚዎችን የምናመላልስበት መንገድ አጣን” “ጊዜያዊም ቢሆን መረማመጃ አዘጋጁልን፣” ማለት ከልማት ከቅብጥርስዮ ጋር ምን አገናኘው!

ፉከራ ይቀንስ! ‘ወዮልህ/ወዮልሽ’ ይቀንስ!

ወደፊት የምንራመድ ከሆነ፣ ድህነትን ተንደርድረንም፣ ሮጠንም ለማምለጥ የምንሞክር ከሆነ፣ የተሰበረውን፣ የተሰባበረውን ደረጃ በደረጃም ቢሆን ለመጠገን የምንሞክር ከሆነ፣ በየመሀሉ የሚለያዩንን አጥሮች ለማፈረስ የምንሞክር ከሆነ… ከአሁኑ የሆነ ልጓም ሊበጅላቸው የሚገቡ ልማዶች አሉ፡፡ ‘የፔትሮዶላር ቅጥረኞች፣’ ሲባል ተኑሮ፣ ‘ጸረ አብዮተኞች፣’ ሲባል ተኑሮ፣ ‘የቀድሞ ስርአት ናፋቂ፣’ ሲባል ተኑሮ… አሁን ደግሞ “ልማትን የማይፈልጉ” አይነት ማስፈራራት ነገሩን ሁሉ “ውሀ ቢወቅጡት ቦጭ” ያደርገዋል፡፡ አሠራሮችን ዘመናዊ ለማድረግ እየተሞከረ እንዳለው ሁሉ አስተሳሰብም አብሮ ካልዘመነ የትም አይደረስም፡፡

በዛ ሰሞን በአንድ የከተማችን ክፍል የሆነ ነው አሉ፡፡ አንድ የግል ኩባንያ የከተማ አውቶብስ ሾፌር ተሳፋሪዎች ናቸው በተባሉ ሰዎች ተደብድቧል ይባላል፡፡ ምክንያቱ ምን እንደሆነ ግልጽ አይደለም፡ እንደውም ኩባንያው ወደዛው አካባቢ መሄድ አቋርጦ ነበር ተብሏል፡፡
ሆኖም ምክንያቱም ምን ይሁን ምን ድበደባ ደረጃ ይደረሳል እንዴ! ጥቃት ሰንዛሪዎቹ እንደዛ እንዲያደርጉ የልብ ልብ የሰጣቸው ምንድነው! ወዴት እየተሄደ ነው? ህግ ያለበት ሀገር ነው እንል የለም እንዴ!

በነገራችን ላይ የአለቆች፣ የቦርድ አባላት ስበሰባ ከሥራ ሰዓት ውጪ ነው ተብሏል፡፡ አሪፍ ነው፡፡ ይህም እንግዲህ የሥራ ሰዓትን ለመቆጠብ መሆኑ ነው፡፡ በየመሥሪያ ቤቱ በየቀኑ የሚደረገው አንድ ለአምስት የሚሉት ስበሰባስ! በዚህስ የሚባክነው የሥራ ሰዓት አይደለም እንዴ!፣

እና ሰው መብቱን ሲጠይቅ፣ የተንጋደደው ቀና ይበልልን ሲል፣ የተሸነቆረው እንዲደፈን ስለጠየቁ ማንም የሚመለከተው ከሆነ ተገቢውን ምላሽና ማብራሪያ መስጠት ነው እንጂ “እናንተ ልማት ልታደናቅፉ ነው፣” የማለት መብት የለውም፡፡ ለነገሩማ… ይቺን አይነት ማስፈራሪያ ሰዎች የራሳችንን ድክመት ለመሸፈን የምንጠቀምበት ሆኗል፡፡ ደግሞም ታሪክ በመጥፎ ሁኔታ ደጋግሞ ስላስተማረን…ላይኛው ጫፍ ካሉት ጋር መላተም፣ መጋጨት ወየንም በክፉ ዓይን መታየት አንፈልግም፡፡

ውጤቱን እናውቀዋለንና! ሰለዚህ “ልማቱን አትደግፍም ማለት ነው፣” ስንባል… “እንዲህ የማለት መብትማ የለህም፣” ከማለት ይልቅ “ሰዎቹ ሳይመርዙኝ በፊት ቢቀርብኝ ይሻላል ብለን ወደ ጉድጓዳችን እንገባለን፡፡
ፉከራ ይቀንስ! ‘ወዮልህ/ወዮልሽ’ ይቀንስ!

በአንድ አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች የቆሻሻ ክምችት ያስቸግራቸውና ወደሚመለከተው ባለስልጣን ይሄዳሉ፡፡ “ኸረ የቆሻሻና የፍሳሹ ነገር እኛና ልጆቻችንን ከፍተኛ ችግር ውስጥ እየከተተብን ነው፡ አንድ ነገር ይደረግልን፣” ይላሉ፡፡ በዚህ ጊዜ የተሰጣቸው መልስ “መንደሩ ፈራሽ ስለሆነ እናንተው እዛው ተሳሰቡ፣” ተባሉ የሚባል ነገር አለ፡፡ “ማምሻም እድሜ ነው፣” ይባል የለ እንዴ! ላይ አካባቢ ለጊዜው ማፍረስ የሚባል ነገር እንደቆመ በሚነገርበት ጊዜ፣ ይፈርሳሉ በተባሉ መንደሮች ሁሉ የኮብልስቶን ንጣፍ ይገባል ተብሎ በተቆፋፈሩበት “ለሚፈረስ መንደር” ብሎ ነገር ምንድነው!

‘ይፈርሳሉ’ ተብለው ነዋሪው ሰነድ ተሸክሞ ከአንዴም ሁለቴ ላይ ታች ከተንከራተተ በኋላ አሁን ለጊዜው መፍረስ እንደማይኖር ከተነገረ በኋላ፡ በአነዳንድ ቦታዎች የታችኛው የሃላፊነት እርከን የተሸነቆረና የሚያፈስ ጣራን ለመጠገን እንኳን እያሰቸገረ ነው ተብሏል፡፡ የትብብር ጥያቄ ሲቀርብ… “መንደሩ ፈራሽ ስለሆነ ምንም ነገር ማድረግ አይቻልም፣” አይነት ነገር አለ ይባላል.. ሌላ አካባቢ ደግሞ አየደለም የተሸነቆረ ጣራ መድፈን ነዋሪው ቤቱ ላይ ያስፈልጋል የሚለውን እድሳት እንዲያደርግ ይፈድለታል፡፡ ለምንድው ተመሳሳይ አሠራር የማይኖረው!

ፉከራ ይቀንስ! ‘ወዮልህ/ወዮልሽ’ ይቀንስ!

ላይ አካባቢ አልፎ፣ አልፎ በጎ ነገሮች ቤተሌቪዥኑ እናያለን፣ በየሬድዮው እንሰማለን፡፡ እሰየው ነው፡፡ ታች ሲወርድ ግን፣ ህብረተሰቡ በቀጥታ ወደሚገናኝባቸው ተቋማት ሲመጣ ግን ያ ተስፋ አቧራ ይሆናል፡፡ ቅሬታ ያቀረበ፣ ‘የመብቴ ይጠበቅ’ ጥያቄ በማቅረባቸው “እርሶ ልማቱን አይደግፉም እንዴ!” የሚባለት እናት ምን ሊሰማቸው ነው፡፡

በወዲያኛው ዘመን በአንድ ወቅት “ተፈጥሮን በቁጥጥር ስር እናውላለን፣” የሚለውን መፈክር አራት ኪሎ በትልቁ ተሰቅሎ ሲያይ “ድንቄም” ብሎ ያጉረመረመ ሰው ‘ሹክ’ ተብሎበት ምርምራ ተደርጎበታል፡፡

በአንድ ወቅት አንድ ወዳጃችን ስለሆነ ትያትር ጋዜጣ ላይ አስተያየት ይሰጣል፡፡ እናም አስተያየቱ በትያተሩ ደካማ ጎኖች ላይ ነበር፡፡ እና የቲያተሩ ተሰብስበው ቢሮ መጡለት፡፡ ነገሩ “አሳምነን፣ እናሳምንህ” አይነት ውይይት ሳይሆን…“አንተ ማነሀና ነው የእኛን ሥራ የምትተቸው!” አይነት ነገር ነበር…የቲያትር ልማት አደናቃፊ እንደማለት ነገር፡፡

እናም፣ ለምንድው ሰዉ አገልግሎት ምስጫ መብቱን ለመጠየቅ ሲሄድ “ምን ይሉኝ ይሆን!” “በምን ይተረጉሙብኝ ይሆን!” ብሎ በስጋት የሚሳቀቀው! ለምንድነው ሰዉ “በዝርዝር ካስረዳሁ በሌላ ሊተረጉሙብኝ ይችላሉ፣” አይነት ፍርሀት እንዲያድርበት የሚደረገው!…
ፉከራ ይቀንስ! ‘ወዮልህ/ወዮልሽ’ ይቀንስ!

“የዘንድሮን ዝምብ ማን ያምናል፣ ተልካ ሊሆን ይችላል፣” ልንል ምንም አይቀረን፡፡ አስተያየት በሰጠን ቁጥር “ልማቱ አይዋጥልህም፣” የምንባልበት…“መብታችን ይከበር፣” ስንል “የድሮ ስርአት ናፋቂ፣” የምንባልበት…ብዙ ሰው ላጨበጨበለት ነገር የግል የተለየ አስተያየታችንን ስንሰጥ “ጥቅሙ የተነካበት፣” “የአገሩን እድገት የማይፈልግ…”

የምንባልበት፣ በጎ ያልናቸውን ሃሳቦችና ተግባራት በምንደግፍበት ጊዜ “አጨብጫቢ፣ አለቅላቂ” ምናምን የምንባልበት መቆም አለበት፡፡ አለበለዛ እንዴት ነው ወደፊት መሄድ የሚቻለው! እንዴት ነው የኮሚነስት ማኒፌስቶ፣ የምናምን ማኒፌስቶ ግልብ እውቀት እንዳጦዘው ካድሬ ሁሉንም ነገር በደጋፊና በተቃዋሚ ዓይን የሚያዩ አገልግሎት ሰጪዎች የፖለቲካ እምነቱን ለሌላው ይተዉና ሙያዊ ሥራቸውን ብቻ ይሥሩልን፡፡

ሰወየው ውሀ ሲወስድው “እኔም ወደቆላ እወርዳለሁ፣” ብዬ ነበር አለ እንደሚባለው ነው፡፡ እኛም ውሀ እየወሰደን እያለ የምንጠላጠልበት የዳርቻ ዛፍ ወይ ቁጥቋጦ እንደመፈለግ “እኔም ቆላ እወርዳለሁ ብዬ ነበር፣” ማለት ትክክል አይደለም፡፡

እንዲህ አይነት ማስደንገጫዎች በጭላንጭል ልናይ እየሞከርን ያለነው ተስፋ የሚያዳክሙ፣ ለዓመታት ከብደው የቆዩት ደመናዎች ምናልባት የሚሳሱበት ጊዜ ደርሶ ይሆናል እያልን ያለነው የህልምና ምኞት ቅልቅል ጭራሽ ድርግም የሚያደርጉብን ናቸው፡፡

ፉከራ ይቀንስ! ‘ወዮልህ/ወዮልሽ’ ይቀንስ!

መብራት ‘ወደውጪ ይላካል’ በሚባልበት ጊዜ “ታዲያ ለምንድነው እኛ በቀን መአት ጊዜ የሚቋረጥብን? ቅድሚያ ለእኛ አይደለም እንዴ!” ማለት ምናልባትም… “አገሪቱ የውጪ ምንዛሪ ለማግኘት የምታደርገውን ጥረት አትደግፍም ማለት ነው፣” የሚል ረጅም የቃላት ዱላ የሚወዘውዝ ሌኒን ሊቀናበት የሚችል ካድሬ ሊኖር ይችላል፡፡

ለምንድነው እኔ ዜጋው በቀን ስንትና ስንት ጊዜ መብራት እየጠፋ፣ ኑሯችን እንደገና ወደ ድንጋይ ዘመን እየተንሸራተተ እየመሰለ “መብራት በተደጋጋሚ ለምን ይቋረጥብናል፣” ማለቱ ጸረ—ልማትነት የሚሆነው በምን አይነት ሂሳብ ነው!

እውነት ለማናገር…ጸረ—ልማትነት የሰዎችን ሃሳብ አዳምጦ ተገቢውን ምላሽ መስጠት ነው ወይስ ስልጣን አለኝ ብሎ፣ ወንበር አለኝ ብሎ፣ ከስሜ ፊት የማእረግ ስም አለኝ ብሎ የሰዉን የመብት ጥያቄ ማፈን ነው!

Share your thoughts on this post
%d bloggers like this:
Visit Us On TwitterVisit Us On YoutubeVisit Us On Instagram