fbpx

ጣሊያን 629 ስደተኞችን የያዘች ጀልባ ወደ ባህር ክልሏ እንዳትገባ ከለከለች

ጣሊያን 629 ስደተኞችን የያዘች ጀልባ ወደ ባህር ክልሏ እንዳትገባ ከለከለች።

ከሊቢያ የባህር ዳርቻዎች ከመስጠም አደጋ ተርፈው የመጡ ስደተኞችን የያዘችው ጀልባ ከጣሊያን የባህር ጠረፍ 35 ማይል ርቀት ለመቆም ተገዳለች።

የጣሊያን አዲሱ የሃገር ውስጥ ሚኒስትር ማቲዮ ሳልቪኒ፥ ስደተኞቹን የያዘችውን ጀልባ ከጣሊያን ይልቅ ማልታ ልትቀበል ይገባል ብለዋል።

ስደተኞቹ መንግስታዊ ባልሆነው የጀርመን በጎ አድራጎት ማህበር አባላት እና የጣሊያን የባህር ላይ የነብስ አድን ቡድን ባካሄዱት ስድስት የነብስ አድን ስራ ከሊቢያ የባህር ዳርቻዎች ወደ ስፍራው የመጡ ናቸው።

ከስደተኞቹ መካከል በርካታ ህጻናትና 7 ነብሰ ጡር ሴቶች መኖራቸውም ተገልጿል።

ስደተኞቹን የያዘችው ጀልባም በጣሊያንና ማልታ የባህር ዳርቻዎች መካከል ላይ ስትሆን፥ የባህር ላይ የነብስ አድን ሰራተኞችም የሁለቱን ሃገራት ባለስልጣናት መልስ እየጠበቁ መሆኑን ተናግረዋል።

በጣሊያን የሚገኘው የስደተኞች ጉዳይ ኤጀንሲ የሚመለከታቸው አካላት አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጡ ጠይቋል።

በነብስ አድን ስራው የታደጓቸው ሰዎች አብዛኛዎቹ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የነበሩ መሆናቸውን፥ የባህር ላይ የነብስ አድን ሰሬተኞቹ ገልጸዋል።

አሁን ላይ ስደተኞቹን ይዘው የት እንደሚያርፍ አለማወቃቸውም ችግር እንደፈጠረባቸው ነው የሚናገሩት።

በሜዲትራንያን ባህር ከአፍሪካ የሚነሱ ስደተኞች ዋነኛ መዳረሻ የሆነችው ጣሊያን፥ የመጣውን ስደተኛ ሁሉ የመቀበል ግዴታ የለብኝም በሚል የባህር ዳርቻወቿ ላይ ጥብቅ ቁጥጥር ማድረግ ጀምራለች።

ከዚህ ባለፈም በርካታ ስደተኞችን ከሃገሯ ለማስወጣት ሃገራት እንዲቀበሏትም እየጠየቀች ነው።

የሃገር ውስጥ ሚኒስትሩም ሃገራት በተደረሰው ስምምነት መሰረት ስደተኞችን የመቀበል ሃላፊነታቸውን እየተወጡ አይደለም በሚል ኮንንዋል።

ይህን ተከትሎም ሃገራቸው በባህር ላይ የነብስ አድን ስራ በመስራት ስደተኞቹን ወደ ጣሊያን በሚያጓጉዙ ተቋማትና ግለሰቦች ላይ ጠንካራ እርምጃ ትወስዳለች ብለዋል።

ስደተኞችን በማቆየትም ሆነ በባህር ላይ በሚደረገው የነብስ አድን ስራ ተሳትፎ ያላደረገችው የማልታ ውሳኔ የስደተኞቹን ቀጣይ እጣ ፈንታ አሳሳቢ አድርጎታል።

 

ምንጭ፦ ቢቢሲ እና አልጀዚራ

Share your thoughts on this post
%d bloggers like this:
Visit Us On TwitterVisit Us On YoutubeVisit Us On Instagram