fbpx

ጠ/ሚ ዶክተር አብይ የረመዳን ጾምን ምክንያት በማድረግ ለእስልምና እምነት ተከታዮች የመልካም ምኞት መልዕክት አስተላለፉ

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የረመዳን ጾምን ምክንያት በማድረግ ለመላው የእስልምና እምነት ተከታዮች የመልካም ምኞት መልዕክት አስተላለፉ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው የረመዳን ወር ከሰላም፣ ከፍቅር፣ ከመረዳዳት፣ ከአንድነት፣ ከእዝነት፣ ከመስጠት እና ከሌሎች በርካታ መንፈሳዊ ትሩፋቶች ጋር የተዛመደ ወር ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የተለየ ወር መሆኑን ጠቅሰዋል።

ከዚህ አንጻርም የረመዳን ወር ለህዝበ ሙስሊሙ በረከት ይዞ ይመጣልም ነው ያሉት።

“ወሩ የሰላም ወር በመሆኑም ህዝበ ሙስሊሙ ለሀገራችን ኢትዮጵያ ሰላም፣ እድገት፣ አንድነት እና ብልጽግና ተግቶ የሚጸልይበት” እንደሚሆንም እምነታቸውን ገልጸዋል።

ምዕመኑም በጾሙ ወቅት ራሱን በመመልከት ከራሱ ጋር በመታረቅ እና ከፈጣሪ ጋር በመገናኘት ለሀገርና ለህዝብ የሚበጅ ሀሳብ እና በተጨባጭም ወደ መሬት የሚወርድ ተግባር የሚከውንበትን እድል ያገኛልም ነው ያሉት።

በዚህ የጾም ወር “መላው ሀገራችን ሰላም እንዲሆን እና ህዝባችንም በሰላም ተዋዶ – በፍቅር ተዋህዶ የመኖር የዘመናት ታሪኩ ይዘልቅ ዘንድ እንደ ሁል ጊዜው በጸሎት – ዱዓችሁ እንድትማጸኑ ጥሪዬን አቀርባለሁ” ብለዋል በመልዕክታቸው።

“በመጨረሻም ታላቁ የጾም ወር ደግ ደጋችን በዝቶ ክፉ ክፉው የሚቀነስበት የሰላም፣ የአንድነት፣ የደስታ፣ የፍቅር፣ የሀሴት እንዲሆንላችሁ ልባዊ ምኞቴን እየገለጽኩ አሁንም በድጋሚ ረመዳን ከሪም ልላችሁ እወዳለሁ፤” በማለት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

1 ሺህ 439ኛው የረመዳን ጾም ነገ ይገባል።

ኤፍ ቢ ሲ

Share your thoughts on this post
%d bloggers like this:
Visit Us On TwitterVisit Us On YoutubeVisit Us On Instagram