fbpx

ጠ/ሚ ዶክተር አብይ አህመድ ከኬንያው ፕሬዚዳንት ጋር እየተወያዩ ነው

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከኬንያው ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ጋር እየተወያዩ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬ ረፋድ ላይ በሃገሪቱ ብሄራዊ መንግስት በፕሬዚዳንት አሁሩ ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል።

በወታደራዊ ስነ ስርዓት በተደረገው አቀባበል ላይ 19 ጊዜ መድፍ ተተኩሷል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ እና ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ የሃገራቱን ግንኙነት ማጠናከር በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ እንደሚመክሩ ይጠበቃል።

የሁለትዮሽና ቀጠናዊ ጉዳዮችም የመሪዎቹ ዋነኛ የመወያያ ነጥቦች ይሆናሉ ተብሏል።

ሃገራቱ ያላቸውን ኢኮኖሚያዊ ግንኙነትን ማጠናከር እንዲሁም የግሉን ዘርፍ የንግድና ኢንቨስትመንት ተሳትፎ ማሳደግ የሚያስችል ውይይት ልዩ ትኩረት እንደሚሰጥበት

የፕሬዚዳንቱ ጽህፈት ቤት ቃል አቀባይ ማኖህ ሲፒሱ ተናግረዋል።

ሃገራቱ የደረሷቸው ስምምነቶችን ተፈጻሚነትና ሂደቱን ማፋጠን የሚያስችል ምክክርም በውይይቱ ወቅት ይነሳል ነው ያሉት ቃል አቀባዩ።

ኢትዮጵያና ኬንያ ጠንካራ ግንኙነት ያላቸው ሲሆን፥ በምስራቅ አፍሪካ ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈንና ሽብርተኝነትን ለመዋጋት በጋራ እየሰሩ ነው።

ከዚህ ባለፈም በሶማሊያ ሰላምን ለማስፈንና ለደቡብ ሱዳን ፖለቲካዊ ቀውስ መፍትሄ ለማምጣት በጋራ እየሰሩም ይገኛል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጉብኝት የሁለቱን ሃገራት የቆየ ወዳጅነት እንደሚያጠናክረው ይጠበቃል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ትናንት ጆሞ ኬንያታ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ በኬንያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሞኒካ ጁማ አቀባበል ተደርጎላቸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በጎረቤት ሀገራት እያደረጉ ባሉት ጉብኝት እስካሁን በጂቡቲ እና በሱዳን ስኬታማ ጉብኝቶችን ማድረጋቸው ይታወሳል።

በእነዚህ ሀገራት በነበራቸው ቆይታም ኢትዮጵያን ከየሀገራቱ ጋር በኢኮኖሚ የሚያስተሳስሩ እና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን የሚያጠናክሩ የተለያዩ ስምምነቶች መድረሳቸውም ይታወቃል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በጂቡቲ በነበራቸው ቆይታም ከሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ኢስማኤል ኦማርጊሌህ ጋር ተገናኝተው ተወያይተዋል።

በተጨማሪም በመሰረተ ልማት፣ በባቡር፣ በመንገድ፣ በኤሌክትሪክ እና በውሃ ዘርፍ ያለውን ትስስር የበለጠ ለማጠናከር መስማማታቸው ይታወሳል።

በተለይም ኢትዮጵያ የጂቡቲ ወደብ ዋነኛ ተጠቃሚ እንደመሆኗ የጂቡቲ ወደብን በጋራ ለማልማትና ለማስተዳደር ከስምምነት ተደርሷል።

በሱዳን ባደረጉት ይፋዊ የስራጉብኝትም ተጨማሪ ሶስት አዳዲስ መንገዶችን ለመገንባትና አዲስ አበባና ካርቱምን የሚያገናኝ የምስራቅ አፍሪካ ማዕከል የሆነ የባቡር መሥመር ለመዘርጋት ስምምነት ላይ ደርሰዋል።

በተመሳሳይ በድንበሮች አካባቢ ነጻ የንግድ ቀጠና ለመፍጠርና የሱዳን ወደብን በጋራ ለማልማትና ለማስተዳደር የተደረሰው ስምምነትም ሌላው የጉብኝቱ ስኬት መሆኑ ተጠቁሟል።

በታላቁ ህዳሴ ግድብ ላይም ሁለቱ ሃገራት ተመሳሳይ አቋም ያላቸውና ግድቡ በተለይም ለቀጠናው ሃገራት በሚሰጠው ጥቅም ላይ ትኩረት አድርገው መወያየታቸውም ታውቋል፡፡

ኤፍ.ቢ.ሲ

Share your thoughts on this post
%d bloggers like this:
Visit Us On TwitterVisit Us On YoutubeVisit Us On Instagram