fbpx

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ዛሬ በምክር ቤቱ ተገኝተው በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ የሰጡት ሙሉ ማብራሪያ

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ዛሬ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው በሀገሪቱ የማክሮ ኢኮኖሚ አፈፃፀም ዙሪያ እና ከምክር ቤቱ አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል።

ኢኮኖሚ

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው ባለፉት ሁለትና ሶስት ዓመታት በሃገሪቱ በተከሰቱ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ቀውሶች ምክንያት፥ በሃገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደሩን ተናግረዋል።

በዚህ ሳቢያም እድገቱ ወደ አንድ አሃዝ መውረዱን ጠቅሰዋል፤ ከግብርናው ጋር በተያያዘ በ2008 ዓ.ም በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ በተከሰተው ኤል ኒኖ የተስተዋለው የምርት መቀነስ በ2009 እና 2010 እያገገመ መምጣቱን ገልጸዋል።

አሁን ላይም ዘርፉን ከዝናብ ጥገኝነት በማላቀቅ ወደ መስኖ ለማሸጋገር እየተሰራ ነው ብለዋል።

በኢንዱስትሪው መስክ የማምረቻውን ዘርፍ ለማሳደግ በርካታ ስራዎች መሰራታቸውን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ዘርፉን በኢኮኖሚው መስክ ቀዳሚ ለማድረግ ከተያዘው እቅድ አንጻር ቀሪ ስራዎች መኖራቸውን ጠቁመዋል።

የወጪ ንግድ

ከወጪ ንግድ አፈጻጸም አንጻር በሰጡት ማብራሪያ ዘርፉ ለተከሰተው የውጭ ምንዛሪ እጥረት ዋና ምክንያት መሆኑን ጠቁመው፥ የወጪ ንግዱን ከማጠናከር ባለፈ ሌሎች የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ይደረጋሉ ብለዋል።

ከዚህ ባለፈም የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶችእ ላይ ማሻሻየዎችን ማድረግና ህገ ወጥ ንግዱን በመቆጣጠር ዘርፉን ለማሻሻል ጥረት ይደረጋልም ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አሁን ላይ ሃገሪቱ የተበደረችውን ብድር የመክፈል አቅም ማጣቷንም ነው በማብራሪያቸው ያነሱት።

በተያዘው በጀት ዓመት የመጀመሪያው መንፈቅም ለእዳ 688 ነጥብ 6 ሚሊየን ዶላር መፈጸሙን ጠቅሰው፥ ኢትዮጵያ ከፍተኛ እዳ ጫና ካለባቸው ሃገራት ተርታ መሰለፏን አስረድተዋል።

አሁን ላይ የሃገሪቱ እዳ 24 ነጥብ 7 ቢሊየን ዶላር መሆኑን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ከአጠቃላይ ብድሩ ውስጥ 56 ነጥብ 1 በመቶው በመንግስት ቀሪው ደግሞ በመንግስት የልማት ድርጅቶች አማካኝነት የተያዘ መሆኑን ገልጸዋል።

አሁን ላይ በመንግስት ያለውን ኢኮኖሚ ለማሻሻል የወጪ ቅነሳ፣ አዳዲስ ኢንቨስትመንቶችን ወደ ኢኮኖሚው ማስገባት እና ማክሮ ፋይናንሱ የሚመራበትን ህግ ማሻሻል አስፈላጊ መሆኑንም ነው ያነሱት።

በተጨማሪም በቴሌኮም ዘርፉ የሚስተዋለውን የጥራት፣ የተወዳዳሪነት እና የሃብት ብክነት ችግር ለመቅረፍም እንደሚያግዝ ገልጸዋል።

የፕራይቬታይዜሽን አፈፃፀም

የተጀመረው ትልልቅ ድርጅቶችና ፕሮጀክቶችን በፕራይቬታይዜሽን ለማስተላለፍ የተወሰነው ውሳኔም ይህን ኢኮኖሚያዊ ጫና ለመቀነስ የተወሰደ ነው።

በፕራይቬታይዜሽን ሂደቱ ዋናው ድርሻ በመንግስት እጅ እንደሚቆይ ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ከ30 እስከ 40 በመቶ በዘርፉ ከፍተኛ ልምድ ያላቸው እና ውጤታማ የሆኑ ኩባንያዎች ብቻ እንደሚይዙት እና 5 በመቶዎቹ ደግሞ በሚሊየን የሚቆጠሩ ሰዎች የሚሳተፉበት እንደሚሆን ነው ያነሱት።

የፖለቲካ ምህዳሩን ከማስፋት አንጻር

ዴሞክራሲውን ለማስፋት በርካታ እርምጃዎች እየተወሰዱ እንደሚገኙም አመልክተዋል።

የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት ለሁሉም የኢትዮጵያ ጉዳይ ያገባኛል ለሚሉ በራፉ ክፍት መደረጉን፣ አስረኞች እንዲፈቱ እና በይቅርታ እንዲለቀቁ መደረጉን አንስተዋል።

በውጭ የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎችም በሰላማዊ መንገድ በፖለቲካው ለመሳተፍ ወደ ሀገር ቤት እየገቡ መሆኑን በመግለፅ ሌሎች ዘመኑ በማይፈልገው ትግል ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ያሏቸው ቡድኖችም ለሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ወደ ሀገር ቤት እንዲገቡ ነው የጠየቁት።

የሀሳብ በነፃነትን ከማጎናፀፍ አንፃርም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ የመገናኛ ብዙሃን በነፃነት እንዲዘግቡ በመወሰኑ ለውጦች እየታዩ መምጣታቸውን ተናግረዋል። ሆኖም የሚዲያ ሙያተኞች ሊወስዱት በሚገባው ሀላፊነት ዙሪያ ግን በቀጣይ የሚሰራ ነው ብለዋል።

የኢትዮ – ኤርትራ፣ ከሰሞኑ የተከሰቱ ግጭቶችና ይቅርታና ምህረት የተደረገላቸው ታራሚዎች ጉዳይ

ከኢትዮ ኤርትራ ጋር በተያያዘ የተላለፈው ውሳኔ ከዚህ ቀደም በጉዳዩ ላይ የተወሰነን የማስፈጸም ጉዳይ እንጅ አዲስ ውሳኔ አይደለም ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት ባድመን በተመለከተ አዲስ ውሳኔ የለም ውሳኔው በፓርላማ በሙሉ ድምጽ የጸደቀና ስምምነቱ በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ተፈርሞ ለአፍሪካ ህብረት የተላከ ነው።

የተወሰነው ውሳኔም ሆነ ለኤርትራ የቀረበው የሰላም ጥሪም በአካባቢው ዘላቂ ሰላምና ልማት ለማምጣት የተደረገ መሆኑንም አውስተዋል።

ሁለቱ ሃገራት ባለፉት አመታት ለጦርነት በመዘጋጀት በርካታ ገንዘብ ማፍሰሳቸውን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በዚህ ሰበብ ለልማት የሚውል ገንዘብ ማባከን አይገባም ነው ያሉት።

በድንበር ጉዳይም ከየትኛውም ሃገር ጋር ግጭት ውስጥ መግባት አይገባም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ በድንበር አካባቢ የነበረውን ችግር በመቅረፍ በትብብር ዘላቂ ሰላም ማምጣት ይገባል ብለዋል።

ከስምምነቱ ጋር ተያይዞም አሁን ላይ ከሚነሳው ጥያቄ ይልቅ የሰላም ጥሪ ተግባራዊነቱ ለምን ዘገየ የሚል ጥያቄ መቅረብ ነበረበት ብለዋል ዶክተር አብይ።፡

አክለውም በኢህአዴግ የተላለፈውን ውሳኔ ከማስፈፀም ውጭ አዲስ የተጨመረ አዲስ ነገር እንደሌለም ነው ያስረዱት።

ከዚህ ባለፈ ግን የባድመ ጉዳይ ለፖለቲካ ፍጆታ መዋል አይገባውም ብለዋል በማብራሪያቸው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሃገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች የተነሳውን ግጭት በተመለከተም፥ ችግሩ ህዝብን ከህዝብ ጋር በማጋጨት የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት በሚሰሩ ሃይሎች ሴራ የተከሰተ ነው ብለዋል።

ህዝብ ከህዝብ ጋር ችግር የለበትም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ እነዚህ አካላት ከመሰል ድርጊታቸው ሊታቀቡ እንሚገባም አሳስበዋል።

ኢትዮጵያ ለኢትዮጵያውያን እንደምትበቃ ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ፥ አንዱን ብሄር ከሌላው በማጋጨት ሃገር መገንባት እንደማይቻል አስረድተዋል።

የዜጎችን ከቦታ ቦታ ተዘዋውሮ የመስራት መብት ከማስጠበቅ አንጻር የተሰሩ ስራዎች ውስንነት መኖሩንም ጠቁመው በቀጣይ ይህ ለመቅረፍ የሚያስችል ስራ እንደሚሰራ አስረድተዋል።

ከዚህ አንጻርም በሃገር ውስጥ ዜጎች በስጋት መተያየትንና መጠላላትን አስወግደው በጋራ መግባባት የተመሰረተ ውጤት እንዲያመጡ እየተሰራ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

ለትውልድ ፍቅርና ሰላምን ማውረስ ይገባልም ነው ያሉት፤ ኢትዮጵያውያን ለሰላም የሚከፈለውን መስዋዕትነት ሊከፍሉ እንደሚገባ በመግለጽ።

እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ አሁን ያለው የወሰን አስተዳደር ችግር እየፈጠረ በመሆኑ ዳግም በመመለስ ከችግሩ መውጫ መንገድ መቀየስ ያስፈልጋል።

በተለያየ ምክንያት ማረሚያ ቤት ቆይተው ከተፈቱ ታራሚዎች ጋር በተያያዘም፥ በምህረትና በይቅርታ በርካታ እስረኞች መፈታታቸውንና መቀመጫቸውን ከሃገር ውጭ ያደረጉ ተቀናቃኝ ፓርቲዎች ወደ ሃገር ውስጥ መግባታቸውን አስረድተዋል።

በሽብር ጭምር ተከሰው ከማረሚያ ቤት የተፈቱ ሰዎች ጉዳይ ኢህአዴግ ባስቀመጠው አቅጣጫ የተፈፀመ እንጅ ህግ የጣሰ አለመሆኑን አስታውሰዋል።

ፍትህን ለሁሉም በዴሞክራሲያዊ መንገድ መተግበር እንደሚያስፈልግ ጠቁመው፥ በይቅርታ ተፈችዎቹን በፖለቲካና በደም መለየት ስህተት መሆኑንም ነው ያስረዱት።

ከዚህ አንጻርም በሃገር ውስጥ በህግ ጥላ ስር ያሉ ታራሚዎችና ተጠርጣሪዎች ያለ ልዩነት መፈታታቸውን ነው የገለጹት።

ሙስና፦ ሙስና ዋነኛው የጭቆና መሳሪያ መሆኑን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ በሃገሪቱ ላይ ከፍተኛ ቀውስ እያስከተለ መሆኑን አንስተዋል።

ግለሰቦች በሙስና የፈለጉትን ነገር ስለሚፈጽሙም እንደ መንግስት ሆነው የመንግስትን ስራ መስራት እንደሚጀምሩም ጠቅሰዋል።

የሙስናን ምንጭ ሳይሆን ቅርንጫፉ ላይ በማተኮራችን ምክንያት ሙስና የሚያደርሰው ጉዳት አለመቆሙንም ገልጸዋል።

በሙስና ሀብት የዘረፉ ሰዎች በሃገሪቲ መኖራቸውን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ሁሉንም ማስገባት አልያም ደግሞ የተሟላ መረጃ እስከሚገኝ ማጣራትን እንደ አመራጭ መያዙን ጠቁመዋል።

ከዚህ ጋር በተገናኘም የውጭ መንግስታትም መረጃ እያቀበሉ እንደሚገኙ አስታውቀዋል።

Share your thoughts on this post
%d bloggers like this:
Visit Us On TwitterVisit Us On YoutubeVisit Us On Instagram