fbpx

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከመከላከያ ሰራዊት ከፍተኛ ሃላፊዎቹ ጋር በሀገራዊና ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያዩ

የኢፌድሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ለመከላከያ ሰራዊት ሃላፊዎች በንድፈ ሃሳብ የታገዘ ገለጻና ከሃላፊዎቹ ጋር በሀገራዊና ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት አድርገዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ፥ የሀገሪቱን ብሄራዊ ጥቅሞችን ለማስከበር የፖለቲካ፣ ኢኮኖሚ፣ ቴክኖሎጂ፣ ዲፕሎማሲ እና ወታደራዊ አቅሞችን አቀናጅቶ ሀገራዊ ክብርና ልዕልናዋን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የመከላከያ ሰራዊት የማይተካ ሚና አለው ብለዋል።

ብሄራዊ ፍላጎትና ጥቅም በሌላ ቋንቋ የህዝብ ፍላጎትና ጥቅም ማለት በመሆኑ፥ የመከላከያ ሰራዊት ከህገ መንግስቱ የሚመነጩ ግልጽ ተልዕኮዎችን አንግቦ ለህዝብ ፍላጎት የሚገዛና ለህዝብ ጥቅም የሚሰራ መሆን እንዳለበትም ገልፀዋል።

የተለያዩ ሀገሮች የመንግሰት ምስረታ ታሪክ የሀገር ጥቅምና ፍላጎት የሚመነጨው ከተለያዩ የገዥ መደቦችና እምነት ተቋማት እንደሆነ ያሳያል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ዘመናዊው ብሄራዊ ጥቅምና ፍላጎት አረዳድ ግን ህዝብና ህዝብን ብቻ መሰረት ያደረገ ነው ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ፥ “የብሄራዊ አቅማችን ዋነኛ መገለጫ የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ግቦች ማሳካት እና የሀገራችን ህዝቦች ክብርና የሀገር ሉዓላዊነት ማስከበር ናቸው” ሲሉም አስረድተዋል።

ዘመናዊው ጦርነት ከመደበኛ የጦርነት አውድ የተለየ ቅርጽ እና መልክ አለው ያሉት ዶክተር አብይ፥ መንግስታትና መንግስታዊ ያልሆኑ የጦርነት ተዋናዮች የሚሳተፉበት፣ የግለሰቦች እና መንግስታዊ ያልሆኑ አካላትን የማድረግ አቅም ያመጠቀ የቴክኖሎጂ እድገት መኖር እና አለም-ቀፋዊነት ያመጣው የኢኮኖሚ፣ ፖለቲካ እና የባህል ትስስር ከፍተኛ የሆነበት ጊዜ ላይ እንገኛለን ሲሉም የዘመናዊ ጦርነት ምህዳሩን ባህሪያት አስረድተዋል።

የጦርነት ስልቱም አሸናፊ ሆኖ ለመገኘት ከሚደረግ ጥረት ይልቅ የተፃራሪ ኃይሎችን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ስርዓቶችን የሚያሳትፍ፣ የተፃራሪ ሀይልን ውሳኔ ሰጪ አካላት ስትራተጂ እቅድ እንዳይሳካ ወይም ውድ ዋጋ የሚያስከፍል ሆኖ እንዲታይ ማድረግን መሰረት ያደረገ የጦርነት ስልት ነው ብለዋል።

መደበኛ ጦርነቶች የሚያስከፍሉት ዋጋ እጅግ ከፍተኛ በመሆኑ መግስታት በቀጥታ ጦርነት ከመግባት ይልቅ የውክልና ጦርነትን መምረጥ የሚታይበት ምህዳር እንደሆነም ጠቁመዋል።

በተጨማሪም የምንገኝበት የአራተኛው ትውልድ ጦርነት አለም በነገሮች እና በኩነቶች መተሳሰር ምክንያት አንድ አካባቢ የሚከሰት ድርጊት አለማቀፋዊ በሆነ መልኩ ቀውስን የሚያስከትል እንደሆነ አንስተዋል።

በነገሮች እና በኩነቶች መተሳሰር እጅግ በጠነከረበት በዚህ ዘመን የሚያጋጥሙ ስጋቶችን መረባዊ የሆኑ በመሆናቸው፥ ስጋቶችን መመከት የሚቻለው በመረባዊ አደረጃጀት ነው ብለዋል።

ይህንን ወቅታዊና ነባራዊ ሁኔታ ከግምት ውስጥ በማስገባት መከላከያ ሰራዊቱ ራሱን በቀጣይ የለውጥ ምህዋር ውስጥ ማስገባት አለበት ሲሉ ተናግረዋል።

የሪፎርሙ መነሻ ሁኔታዎችም የሀገሪቱ የማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚ ሁኔታችና በአጠቃላይ የህዝብ ስሜት ነው ብለዋል።

ሀገራችን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ዙሪያ መለስ የፖለቲካ አለመረጋጋት ውስጥ በመቆየት ከፍተኛ አደጋ ያንዣበበት ሁኔታ ተፈጥሮ እንደነበር ያስታወሱት ዶክተር አብይ፥ ችግሩን የፈጠረው መንግስት ችግሩን መፍታት አይቻልም እስከመባል ቢደርስም ተግዳሮቱን ወደ እድል ቀይሮ ሀገራዊ የለውጥ እንቅስቃሴዎችን በአፋጣኝ መውሰድ በመጀመሩ የህዝቡን ተስፋ በድጋሚ በማግኘቱ ለውጡን ለማስፋትና ለማጥለቅ ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል ብለዋል።

በመሆኑም በመከላከያ ሀይል በኩል ያለው ዋነኛ ቁልፍ ሪፎርም ጉዳይ የሰራዊቱን “ፕሮፌሽናሊዝም” ማሳደግ እንደሆነ ጠቁመዋል።

ይህም ሲባል የሰራዊቱን ሙያዊ ብቃት፣ ሃላፊነት የመውስድና የተሟላ ሰብዕና የተላበሰ መሆን ይኖርበታል።

ይህ ሲሆን ሰራዊቱ በመርህ የሚገዛና ለወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ ተጽዕኖ በቀላሉ እጅ የማይሰጥ የህዝብን ፍላጎትና ጥቅም የሚያስከበር ያደርገዋል ብለዋል።

በቅርቡ በተደረገው የመንግስት ስልጣን ሽግግር ወቅትም ሰራዊቱ ያሳኘውን ሙያዊ ዲሲፕሊን ያደነቁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ይህ “ፕሮፌሽናሊዝም” መቀጠል አለበት ብለዋል።

የመከላከያን ወሳኝ አቅሞች ለማሰደግ በምድር ሀይልና በአየር ሀይል በአፍሪካ ቀደምት ሀገሮች ተርታ ያስቀመጠንን ሀይል ገንብተናል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የባህር ሀይል አቅምንም በቀጣይ ማሳደግ ይገባናል ነው ያሉት።

የኢፌድሪ ህገ መንግስት መከላከያ ሰራዊቱ የብሄር፣ ብሄረሰቦች ነጸብራቅ፣ ከፖለቲካ ወገንተኝነት መጽዳት፣ ለሲቪል አስተዳደርና ለህገ መንግስቱ ተገዥ መሆን፣ የሀገርን ሉዓላዊነት የማስከበር ተልዕኮ ያሰቀመጠ በመሆኑ፥ የሀገር መከላከያ ሰራዊት ህገ መንግስታዊ ባህሪውን ጠብቆ መዝለቅ አለበት ብለዋል።

የመከላከያ ሰራዊት ዋነኛ አላማ በሲቪል አስተዳደሩ የሚቀመጡ ሀገራዊ ስጋቶችና የደህንነት ስጋቶችን በተቀመጠለት ትርጓሜ መሰረት በላቀ ብቃት ግዳጁን የማስፈጸም፣ የህዝብን ፍላጎቶችና ጥቅሞች ማስከበር እና የሀገር ክብርና ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ እንደሆነም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልፀዋል።

ኤፍ.ቢ.ሲ

Share your thoughts on this post
%d bloggers like this:
Visit Us On TwitterVisit Us On YoutubeVisit Us On Instagram