fbpx
AFRICAAMHARICPOLITICS

ግብፅ ግድቡ ላይ ተፅእኖ ለመፍጠር ያገኘችውን ክፍተቶች ሁሉ መጠቀምን ተያይዛለች- ምሁራን

የግብፅ መሪዎች ዛቻ ተመልሷል፤ ስለ አባይ ውሃ የጋራ ተጠቃሚነት ከሁለት ዓመት በፊት የፈረሙት ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አል ሲ ሲ ስለ ብቻ ተጠቃሚነት ማቀንቀን ጀምረዋል።

የውሃ ምንጭ ለሆነች ሀገር ውሃን የከለከለ ስምምነት አሁንም በግብፅ ጠረጴዛ ላይ ነው ይላሉ ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ያነጋገራቸው ምሁራን።

በዓባይ ውሃ አጠቃቀም ዙሪያ ጥናት ያካሄዱት ምሁር አቶ ጌታቸው መኮንን፥ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1929 እና በ1959 የተፈረመው ስምምነት ግብፅ አንዲትም ጠብታ ለውሃው ሳታበረክት ከፍተኛውን ድርሻ ነው የሰጣት ይላሉ።

ተመራማሪው እንደሚናገሩት፥ ግብፅ የአባይ ውሃ የብቻዬ ነው የሚለው አቋሟ ተመልሶ መጥቷል።

ፕሬዚዳንት አብዱል ፈታህ ኤል ሲሲም ከሁለት ዓመት በፊት አትዮጵያን ሲጎበኙ አባይን በጋራ ስለ መጠቀም ቃል ገብተው እንደነበረ አይዘነጋም።

ባለፉት ሳምንታት ግን ግብፅ ታሪካዊ የውሃ ድርሻዋን አታስነካም ብለዋል።

ይህንን ባሉ በቀናት ውስጥ የግብፅ መገናኛ ብዙሃን ከሁለት ዓመት በፊት የነበረውን ፉከራ ማሰማት ጀምረዋል፤ የጦር ሀይልን እስከማሰማት የደረሰ ዛቻ ላይ ናቸው።

ግብፃውያን ከሩቅ ወታደራዊ ሀይልን በማሳየት ማስፈራራት፤ ውስጥ ውስጡን ደግሞ ለዘመናት የቆየ ድርጊታቸውን ስለመቀጠላቸው ምሁራን ያነሳሉ።

በዓባይ ውሃ አጠቃቀም ዙሪያ ጥናት ያካሄዱት አቶ ጌታቸው መኮንን ግብፅ የውሃ አጠቃቀም የበላይነትን ለማስጠበቅ ያልፈነቀለችው እና ያላደረገችው ነገር የለም ያሉ ሲሆን፥ በሀይልም በሌላ በኩልም ሙከራ አድርጋለች፤ ኢትዮጵያ ይህንን መክታለች ይላሉ።

ጋዜጠኛ ፋኑኤል ክንፉም፥ “መግፋት ስላልቻሉ እንጂ ጠንካራ ኢትዮጵያን ላለማየት የማያቋርጥ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ያላቸው ሰዎች ናቸው፤ አይበትኑንም የሚባለው ነገር አይደለም በሀገር ደረጃ በግለሰብ ደረጃ ቢበትኑን ደስታቸው ነው” ብለዋል።

ብሄርን ከብሄር ማጋጨትን እየተጠቀሙ ሀገርን መበተን ይችላሉ ለሚለው፤ መንገድ ከከፈትንላቸው በደንብ ሊበትኑ ይችላሉ ሲልም ተናግረዋል።

የግብፅ የዚህ ወቅት ድርጊት የኢትዮጵያን ውስጠ ሁኔታ በራስ መንገድ ከመገምገም የመነጨና እና ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ኢላማ ያደረገ ነው።

አቶ ጌታቸው መኮንን፥ “የኢትዮጵያ የውጭ ተጋላጭነት ጨምሯል፤ በሀገሪቱ ውስጥ ሰላም እና መረጋጋት የለም የሚል አስተሳሰብ ኑሯቸው ጊዜው አሁን ነው ብለው ያስባሉ” ሲሉ ተናግረዋል።

የህዳሴው ግድብ የሚሰራው እና የሚገነባው በሀገሪቱ ህዝብ እና መንግስት አቅም ስለሆነ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ማናቸውንም ነገር ማተራመስ እና ማጥፋት ግድቡ ላይ ቀጥተኛ ተፅእኖ እንዳለው ያምናሉ የሚሉት ደግሞ አቶ ፋኑኤል ክንፉ ናቸው።

ሁሉም ኢትዮጵያውያን በአብሮነት ግድቡን ለማጠናቀቅ ከጫፍ ሲደርሱ፤ ግብፆች የጥንካሬ ምንጩን መበተን ላይ ተጠምደዋል።

የቀጥተኛ ጦርነት ሁለተኛው ማለት የውክልና ጦርነት የሚሉት አቶ ፋኑኤል፥ “ግብፅ በታሪኳ እስካሁኗ ደቂቃ ድረስ በኢትዮጵያ ውስጥ በውክልና ጦርነት ውስጥ አለች” ይላሉ።

ግብፅ መገናኛ ብዙሃን አውታሮችን፣ የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ሀይሎችን፣ ለኢትዮጵያ በጎ አመለካከት የሌላቸው ሀይሎችን ግብፅ በማደራጀት ይፋዊ የሆነ እንቅስቃሴ እንዳደረገች የምናውቀው ነው የሚሉት ደግሞ ተመራማሪዎው አቶ ጌታቸው መኮንን ናቸው።

በአባይ የለማች ሀገር፣ በናይል ውሃ ከረሃብ ተከልለው ያሉ ግብፃውያን ውሃ እያላቸው ከተጠሙ ታላቅ ወንዝን ታቅፈው በረሃብ ሲያልቁ የነበሩ በጋራ ለመጠቀም በተነሱ ኢትዮጵያውያን መካከል ግጭትን ይዘራሉ።

ምሁራኑ እንደተናገሩት የውክልና ጦርነት በኢትዮጵያ ላይ ያወጀች ግብጽ፤ መገናኛ ብዙሃኖቿ እንደሚሉት የቀጥታ ጥቃትን ትፈፅም ይሆን?

የኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ መምህሩ አቶ ብርሃኑ በላቸው፥ ኢትዮጵያ በዓለምም በአፍሪካም ያላት ተሰሚነት እና ድርሻ ይታወቃል፤ ከዚህ በተጨማሪም በአሁኑ ሰዓት እንኳን በአካል በሳይበር ጥቃት እንዳይፈፀም የመረጃ መረብ ደህንነት ኤጀንሲ እየሰራ ነው ይላሉ።

ስለዚህ ግብፅ በኢትዮጵያ ላይ በማንኛውም መልኩ ጥቃት ለመሰንዘር ይከብዳታል ባይ ናቸው።

የህዳሴው ግድብ የገዢው ፓርቲ ግድብ አይደለም፤ ሀገሪቷ ውስጥ ያሉ ልሂቃን ስብስብ ፍላጎት ማስፈፀሚያም አይደለም የሚሉት አቶ ፋኑኤል፥ ስለዚህ ግድቡ የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ስለሆነ ጦርነቱ ከማን ጋ እንደሆነ በግልፅ ያውቁታል ብለዋል።

ጦርነቱ ከመንግስት ጋር ብቻ ሳይሆን ከእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ጋር ነው፤ ይሄ በጣም ትልቅ የሆነ እና አሸናፊ ሊሆን የማችይልበት እንደሆነ ይገመታል ሲሉም ገልፀዋል።

በዳዊት መስፍን

Share your thoughts on this post
%d bloggers like this:
Visit Us On TwitterVisit Us On YoutubeVisit Us On Instagram