fbpx

ግብጽ 7 ሚሊየን የሃገሪቱን ፓውንድ ለቆጠቡ የውጭ ሃገር ሰዎች ዜግነት ልትሰጥ ነው

የግብጽ ፓርላማ የውጭ ሃገር ዜጎች የግብጽን ዜግነት እንዲያገኙ አዲስና አነጋጋሪ የሆነ ረቂቅ የውሳኔ ሀሳብን አፅድቋል።

ፓርላማው ያፀደቀው ረቂቅ የውሳኔ ሃሳብ በሃገሪቱ 5 አመት ኖረው 7 ሚሊየን የግብጽ ፓውንድ የቆጠቡ የውጭ ሃገር ዜግነት ያላቸው ግለሰቦች የግብጽን ዜግነት እንዲያገኙ የሚያደርግ ይሆናል ነው የተባለው።

በዚህም አንድ ግለሰብ በግብጽ ለአምስት ተከታታይ አመታት የኖረና የተባለውን ገንዘብ በግብጽ በሚገኙ ባንኮች ውስጥ ያስቀመጠ ወይም የቆጠበ ከሆነ ማመልከቻ አስገብቶ የሃገሪቱን ዜግነት ማግኘት ይችላል ተብሏል።

ግለሰቡ በግብጽ ለተከታታይ አምስት አመታት በግብጽ መኖሪያውን አድርጎ ገንዘቡ ካለው ዜግነት የሚሰጠው ሲሆን፥ ፖለቲካዊ ተሳትፎን የሚያስገኙ ሌሎች መብቶችን ለማግኘት ግን ተጨማሪ አመታት መጠበቅ ይኖርበታል።

ለምሳሌ ግለሰቡ/ግለሰቧ በግብጽ በሚደረግ ምርጫ በመራጭነትም ሆነ በተፎካካሪነት መሳተፍ ቢፈልግ ተጨማሪ አምስት አመታትን መጠበቅ እንደሚኖርበት በረቂቅ የውሳኔ ሀሳቡ ላይ ቀርቧል።

አሁን ፓርላማው ያፀደቀው ረቂቅ የውሳኔ ሀሳብ ህግ ሆኖ እንዲወጣ በፓርላማው ተጨማሪ ውይይት ተደርጎበት በድጋሚ መፅደቅና በመጨረሻም የፕሬዚዳንቱን ይሁንታ ማግኘት ይኖርበታል።

በፈረንጆቹ 2011 በሃገሪቱ ከተሰከተው አለመረጋጋትና ብጥብጥ በኋላ መቀመጫቸውን ግብጽ ያደረጉ የውጭ ሃገር ኩባንያዎችና ባለሃብቶች ሃገሪቱን ለቀው ወጥተዋል።
ይህ መሆኑ ደግሞ የሃገሪቱን ኢንቨስትመንትና ኢኮኖሚ ክፉኛ ጎድቶታል ነው የተባለው።

የአሁኑ ውሳኔም የሃገሪቱ መንግስት ኢንቨስትመንቱን በተለይም የውጭ ባለሃብቶችን ተሳትፎ በማጠናከር ኢኮኖሚውን ለማሻሻል የሚያደርገው እንቅስቃሴ አንድ አካል መሆኑ እየተነገረ ነው።

በርካታ ግብጻውያን ግን ዜግነት እንዴት ይሸጣል በማለት የውሳኔ ሃሳቡን ኮንነውታል፤ ከዚያ ይልቅ ባለሃብቶችን መሳብ የሚያስችል ቀላል አሰራር ሊኖር ይገባልም እያሉ ነው።

በረቂቅ የውሳኔ ሃሳቡ ልጅና ባለቤት በግብጽ እስካልኖሩ ድረስ የግብጽን ዜግነት ማግኘት አይችሉም።

 

ምንጭ፦ ሬውተርስ እና አልጀዚራ

Share your thoughts on this post
%d bloggers like this:
Visit Us On TwitterVisit Us On YoutubeVisit Us On Instagram