fbpx

ጌዲዮና ጉጅ ሀገራቸው የት ነው?

ጌዲዮና ጉጅ ሀገራቸው የት ነው? | ሬሞንድ ሃይሉ

ሙህጅ እናትና የሁለት ዓመት ልጁን በህይወት ለማቆየት “ከሰማይ መናን” ይጠበቃል፡፡ ከስምንት ቤተሰቦቹ ጋር የተጠለለባት አነስተኛ ድንኳን ዝናብና ንፋስ መቋቋም ባትችልም ለእሱ ግን የከባዱ ክረምት ማሳለፊያ ብቸኛ አማራጩ ሁናለች፡፡

ከዓለም አቀፉ የስደተኞች ተቋማ (IOM) የጥናት ባለሙያዎች ቆታ ያደረገው ሙህጅ ስለነገ አይደለም ዛሬን የሚጥለው ከባድ ዝናብ በስደት ድንኳን ውስጥ የተጠለሉትን ቤተሰቦቹን ህይወት ሊነጥቀው እንደሚችል ያስባል፡፡ አረጋዊ እናቱና የሁለት አመት ልጁም የሚላስ የሚቀመስ አጥተው ፤በርሀብ ወደ ሞት ሲንደረደሩ ቁጭ ብሎ እያየ በአይኖቹ እንባ ያቀራል፡፡

የሙህጅ ታሪክ የብዙዎቹ የጌዲዮ ተፈናቃዮች የታሪክ ዕውነት ሊሆን እየተነደረደረ ነው፡፡ የእንግሊዙ ግብረ ሰናይ ድርጅት ኬር ኢንተርናሽናል ከዕይታ የተሰወረ ታላቅ ሰባዓዊ ቀውስ በሚለው የጌዲዮና የምዕራብ ጉጅ ግጭት የተነሳ አዕላፍ ኢትዮጵያውያን በሞትና በህይወት መካከል መሆቸውን በዚህ ሳምንት ባወጣው መግለጫው አትቷል፡፡ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በፍጥነት እጁቹን ካልዘረጋም ነገሮች ከዚህ በላይ አሳሳቢ እንደሚሆኑ ገልጾል፡፡

ዓለም አቀፉ የስደተኞች ተቋም በበኩሉ ዓለም የዘነጋችው ከባድ የሰባዓዊ ቀውስ ኢትዮጵያ ውስጥ ተከስቷል የሚል ዜናውን ትናንት ለዓለም አቀፉ ማህበረስብ አሳውቋል ፡፡ ለዚህም ሁሉም ሊረባረብ ይገባል ብሏል፡፡ ከቪ ኦ ኤ እሰከ ሽንዋ የዘለቀው የታላላቆቹ የመገናኛ ብዙሀኑ ወሬም ከአዲሱ ጠቅላይ ሚንሰትር ወደ ሰበአዊ ቀውሱ አጋድሏል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሰት ግን አሁንም ዝምታን ምርጫው አድርጓል፡፡ በሀገሪቱ ታሪክ ከፍተኛ የተባለውና በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን ያፈናቀለው በምዕራብ ጉጅና በጌዲዮ መካከል የተከሰተው አለመግባባት አሁንም በየቀኑ የበርካቶችን ህይወት እየቀጠፈ ነው፡፡ እንደ ዓለም አቀፉ ስደተተኞች ተቋም ሪፖርት ከሆነ ካለፈው ሚያዚያ አንሰቶ ከ822 ሺህ(?) በላይ የጊዲዎ ነዋሪዎችና 147 ሺህ በላይ ጉጅዎች ከቤት ንበረታቸው ተፈናቅለዋል፡፡

ህጻናትና አረጋውያን አሳሳቢ ደራጅ ላይ የሚገኙበት ይህ የሀገር ውስጥ ፍለሰት አሁንም በኢትዮጵያውያን በኩል ተገቢ ትኩረት አልተሰጠውም፡፡ የክልሉ መንግስት አፈ ጉባዔ በቅርቡ እንዳስታወቁት የደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልላዊ መንግስት ለተፈናቃዮቹ የሚችለውን እያደረገ ቢሆንም ነገሮች ከአቅም በላይ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ የፌደራሉ መንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናትም በቦታው ተገኝተው ጉብኝት ቢያደርጉም ዛሬም አዕላፍ በአሰቃቂ ሁኔታ ይሞታሉ፤ ይፈናቀላሉ፡፡

በዚህ ሁሉ መኃል ግን ስለ አንደነት የሚዘምረው የኢትዮጵያ ህዝብ ጌዲዮና ምዕራብ ጉጅን ዘንግቷቸዋል፡፡ ስለ አንድ ኢትዮጵያዊነት እያወራን በሞትና ሕይወት መካከል ያሉትን በርካተ ዜጎች እረስተናቸዋል፡፡ ከትናንቱ የተሻለ ኢትዮጵያዊነት እየታየ ነው ስንል መስፈርቱ ምንድን ነው? የጌዲዮ ሞት የጉጅ ስደት ለትግራይ፣ለአማራ፣ለአፋር፣ለጋንቤላ…….. ካላመመው አንድነቱ ምኑ ላይ ነው ?

በብሄር ዘውግ አንለያይም እያለን እየዘመርን የእኛ ብሄር ብቻ ሲነካ መጮኹን ከቀጠልን ከትናንቱ ይልቅ ነጋችን ያስፈራል ፡፡”አንድ ላይ ብንሆንም ተለያይተናል !” መንግሰትም መልካም ገጽታየን ያጎድፍብኛል ብሎ ነገሮችን ለመሸፋፈን መሞከሩ ታሪካዊ ስህተት ይሆናልና ቆም ብሎ ሊያስብበት ይገባል ፡፡ ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በይፋ ድገፍ እንዲደረግለት መጠየቅም ይኖርበታል ፡፡

ቀዳማዊ ኃይለስላሴ የወሎ ህዘብ የሚላስ የሚቀመስ አጥቶ እያለ ዓለም ቢሰማ ክብሬ ይነካል ስላሉ በመጨረሻ ባፈኑት ህዘብ ታፈነው ሞቱ፡፡ ይህ የታሪክ ዕውነት ሊያስተምረን ይገባል፡፡ ዛሬም መሸፋፈኑ ይብቃና የሚላስ የሚቀመስ ላጡት ኢትዮጵያውያን እንድረስላቸው፡፡ ስለነገ ሳይሆን ስለዛሬ ህይወታቸው ህልውና እርግጠኛ ያልሆኑትን አዕላፍ ኢትዮጵያውያን በተገቢው ሁኔታ የሚደገፉበት መንገድ ይመቻች፡፡

ለኢትዮጵያውያኑ ከዓለም አቀፍ ተቋማት ይልቅ ኢትዮጵያውያን እንቅርባቸዋለንና ስለችግራቸው በድፈረት እናውራ፡፡ በየትኛውም አካል ይሁን የዕርዳታ መንገድ ይዘጋጅና የሀገሬው ሰው የሚችለውን ያድርግ፡፡ ስንደመር በርሃብና በግጭት የሚቀነሱትን እናስብ!

DireTube

Share your thoughts on this post
%d bloggers like this:
Visit Us On TwitterVisit Us On YoutubeVisit Us On Instagram