fbpx

ጀምበር፡ ከሰው የተለየ ኃይል ያለው ኢትዮጵያዊው ወጣት

የ28 ዓመቱ ብስራት ደበበ የምህንድስና ምሩቅ ሲሆን ኮኔክትከት በተሰኘችው የአሜሪካ ግዛት ውስጥ ነዋሪ ነው። በአሁን ሰዓት ኤንጅን በሚያመርት ድርጅት ውስጥ ተቀጥሮ እየሠራ ይገኛል።

ብስራት ኢትዮጵያን ለቆ ሲውጣ የ14 ዓመት ወጣት ቢሆንም እስካሁን ባህሉ፣ ኃይማኖቱና የዕጣኑ ሽታ ከአዕምሮው እንዳልወጣ ይናገራል። እነሆ አሁን በአሜሪካ ባደገበትም ጊዜ የተዋወቀው የጥበብ ስልት ብስራት ላይ የተለየ ተፅዕኖ አሳድሮበታል።

ብስራት ተቀጥሮ ይስራ እንጂ ጎን ለጎን ‘ዕጣን ኮሚክስ’ የተሰኘውን ድርጅት ያቋቋመ ወጣት ነው። ዕጣን ኮሚክስ የኢትዮጵያንና የመላውን አፍሪካ ታሪክ በአግባቡ በመንገር ዕቅድ የተደራጀ ነው። በሕይወት ዘመኑ ስለ ኢትዮጵያና ስለ አፍሪካ ያጋጠሙት የተለያዩ መጥፎና የተጋነኑ አመለካከቶች ይህን ዓላማ ለማሳካት አስተዋፅዖ እንደነበራቸው ይናገራል።

ኮሚክስ ምንድን ነው?

ዕጣን ኮሚክስ፤ በተለይ በምዕራቡ ዓለም ኮሚክስ በመባል የሚታውቁትን የመጽሐፍት ዓይነቶችን የሚያሳትም ድርጅት ነው። ኮሚክስ በሚለው ቃል ይሰየም እንጂ ከሳቅም ሆነ ከቀልድ የራቀ ይዘት ያላቸው መጽሐፍት ናቸው የሚለን ብስራት በወጣትነቱ ከመጽሐፍት ቤትና ከጓደኞቹ እየተዋሰ ማንበብ ያስደስተው እንደነበር ያስታውሳል።

ኮሚክ ቡክስ የሚባሉት ሥዕላዊ ድጋፍ ያላቸው ታሪኮችን ያዘሉ መጽሐፍት እንደሆኑና ታሪኩን ቅደም ተከተል ባላቸው ሳጥኖች ውስጥ በማስቀመጥ ገጸ ባህሪያቱን በማስወራት የሚተርክ እንደሆነም ያስረዳል።

እንደ ማንኛውም የአሜሪካ ወጣት ሱፐርማን፣ ስፓይደርማንንና ብላክ ፓንተር የመሳሰሉትን ገጸ ባህሪያት እያነበበ ያደገው ብስራት፤ በኢትዮጵያ ባህልና እምነት ውስጥ ያለፈ ጀግና ገጸ ባህሪ አስፈላጊ ሆኖ ይሰማው ነበረ።

በምዕራቡ ዓለም ስለ ኢትዮጵያና ስለ እፍሪካ ይሰሙ የነበሩት ዜናዎች አብዛኛውን ጊዜ አሉታዊ ስለነበሩና መልካም ጎናቸው እምብዛም ባለመንፀባረቁ ነገሮችን ለመቀየር ይመኝ እንደነበር የሚናገረው ብስራት ”ትግሉ ሰፊና ብቻዬን መወጣት የምችለው እንዳልሆነ አውቅ ነበር” ይላል።

ለኮሚክ ቡክስ ፍቅር ያደረበት የ14 ዓመቱ ብስራት እንድ ቀን የእራሱን ታሪክ የሚነግርበትንና የሚስልበትን አጋጣሚ የመፍጠር ዓላማውን እንደያዘ በሕይወት ውጣ ውረድ እንደተጠመደ እዚያው በእሜሪካ አደገ።

ሕልሙን ለማሳካት ጊዜ የፈጀበት ብስራት፤ ሥራውን ለመጀመር ብርታት ያገኘው በአጋጣሚ ዜና ላይ የብሩክታዊት ጥጋቡን ‘ጥበብ ገርልስ’ የተሰኙትን የማስተማር ዓላማ የያዙትን ገጸ ባህሪያት ሲመለከት ነበር። ይህም የድሮውን ፍላጎቱን እንዲያገረሽ አድርጎ ተደብቆ የነበርውን ሕልሙን ቀሰቀሰ።

የዕጣን ኮሚክስ ቡድን (ከግራ ወደ ቀኝ) ብስራት ደበበ፣ ሬቤካ አሳ፣ ብራያን ኢቤህ፣ አካኒ አኮሬዴ እና ስታንሊ ኦቤንዴ
ETAN COMICS
የዕጣን ኮሚክስ ቡድን (ከግራ ወደ ቀኝ) ብስራት ደበበ፣ ሬቤካ አሳ፣ ብራያን ኢቤህ፣ አካኒ አኮሬዴ እና ስታንሊ ኦቤንዴ

ዕጣን ኮሚክስ

”ከአክስቴ ልጅ ጋር እየተጫወትን ሳለ እንደ ሃሳብ ዕጣን የሚለውን ስያሜ ስታቀርብልኝ ወደድኩት። ምክንያቱም ብዙውን ጊዜ ከቤተሰብና ከጓደኞቼ ጋር የማሳልፈውን መልካም ጊዜና ያስታውሰኛል” ይላል።

ዕጣን የሚለው ስያሜ ምንጊዜም አዎንታዊ የሆነን ስሜት የሚፈጥር ነው በማለት የሚናገረው ብስራት፤ ዕጣን ሲጨስ ዙሪያውንም ሆነ የሚደርስበት አካባቢ ሁሉ በማዕዛው ማወዱ አይቀርም። ልክ እንደዚያው ዕጣን ኮሚክስ ጥሩ ስሜትን የመፍጠርና በዓለም የመዳረስ ዓላማ ይዞ በመነሳቱ የስያሜው ተገቢነት አላጠራጠረውም።

ዕጣን ኮሚክስን ለማቋቋም ያነሳሳው በልጅነቱ ያነባቸው በነበሩት ኮሚክስ ውስጥ እራሱን ማግኘት ባለመቻሉ ነበር።

”በመጀመሪያ የኢትዮጵያን ባህል የያዙና የሚያንፀባርቁም ሆነ መቼታቸውን በሚታወቁ የኢትዮጵያ ውይም የአፍሪካ ሃገራት ላይ ያደረጉ የጀግና ገጸ ባህሪያት የሉም” የሚለው ብስራት በመቀጠል ”በተለይ ትክክለኛነትን፣ ፍትሐዊነትን፣ ተስፋንና ሰላምን የሚያንፀባርቅ ጀግና አይገኝም” በማለት ያስረዳል።

አፍሪካዊያን ስለ እራሳቸው ያላቸው አመለካከትና ለእራሳቸው ያላቸው ቦታ መጥፎ እንዳይሆንና እራሳቸውን በጥሩ ብርሃን መመልከት እንዲችሉ ይጠቅማል ብሎም ያምናል።

እነዚህን የመሳሰሉ ባህሪያት እሱን በሚመስሉ ገጸ ባህሪያት ላይ ማየቱ አስፈላጊ ነው የሚለው ብስራት ኢትዮጵያም ሆነ በሌሎች የእፍሪካ ሃገራት ውስጥ ላሉ ወጣቶች ይጠቅማል ባይ ነው።

ከልጅነታቸው ጀምሮ አዎንታዊ ሥራ የሚያከናውኑ ገጸ ባህሪያትን ቢመለከቱ ሊያበረታታቸውም ሆነ አስተሳሰባቸውን ሊቀይር ይችላል ይላል። ይህ አመለካከት ደግሞ በምዕራቡም ዓለም ሊስፋፋ እንደሚችል ተስፋ አለው።

”አፍሪካ ውስጥ በእርግጥ ብዙ ችግሮች አሉ ሆኖም ግን ብዙ ጥሩ ነገሮችም አሉ። በአፍሪካ የሚኖሩ ሰዎች በየቀኑ ጥንካሬ፣ ድፍረትና ተስፋ የሚጠይቁ ነገሮችን በማድረግ ኑሮን የሚገፉ ሞልተዋል” የሚለው ብስራት ሲቀጥል ”እነሱ ደግሞ በዓለም ሌሎች ክፍሎች ላይ ካሉ ስዎች ምንም እንደማይለዩ ማሳየት እፈልጋለሁ” ይለናል።

ብስራት ይህን የማረም ፍላጎቱን ከኮሚክ ቡክ ፍቅሩ ጋር በማዋሃድ ጀምበር የተሰኘውን ገጸ ባህሪ ሊፈጥር ችሏል።

ጀምበር
ETAN COMICS

 ኢትዮጵያዊው ጀግና ማን ነው?

የዕጣን ኮሚክስ ሃሳብ የመጣለት አንድ ዓመት ከግማሽ በፊት ቢሆንም እንኳን፤ ፍሬ ሊያፈራ የቻለው ለጊዜው የዕጣን ኮሚክስ አባላት ጥቂት በመሆናቸው እንደሆነ ያስረዳል። የሚያውቃቸውን ሰዎችና ጓደኞቹን አሰባስቦ የመጀምሪያውን የዕጣን ኮሚክስ እትም ‘ጀምበር’ ብሎ በመሰየም ለሕዝብ በእንግሊዝኛና በአማርኛ በድረ ገጽ በኩል፤ የዛሬ ሁለት ወር ደግሞ ለኢትዮጵያ ታትሞ ከጥቂት ሳምንታት በፊት ሊቀርብ ችሏል።

ጀምበርን በቀላሉ ለማስተዋወቅ ፤ ጀምበር እንደ ማንኛውም ኢትዮጵዮጵያዊ ወጣት ነው ማለት ይቻላል። ነገር ግን ከሌላው ሰው ለየት የሚያደርገው ልዩ ኃይል አለው። የጀግና ስሙ ጀምበር ቢሆንም እሱ ግን አማኑኤል ጥላሁን ይባላል።

የዩኒቨርሲቲ ምሩቅ ሲሆን የሥራ ዓለምን ለመቀላቀልና እራሱን ለመቻል እየጣረ ያለ ኢትዮጵያዊ ወጣት ነው። ጀምበር በአጋጣሚ የጥንት ጽሑፎችን ሲያገኝ ነው ልዩ ኃይል ተላብሶ ጀግና ሊሆን የቻለውና ሕይወቱ የሚቀየረው።

ብስራት እንደሚለው ”አማኑኤል ባለበት ሁኔታ ላይ ያሉ ብዙ ኢትዮጵያዊ ወጣቶች አሉ። እሱም ልክ እንደ እነርሱ የሕይወትን ትርጉም ፍለጋ ላይ ያለና ማሕበረሰቡ የሚጠብቅበትን ለማሟላት እየተሯሯጠ ያለ ወጣት ነው።”

በጀምበር እትም የጀግናውን ውጣ ውረዶች የምንከታተልበትና ለኢትዮጵያዊው ልዩ ኃይል መላበስ ምን ዓይነት ትርጉምና ስያሜ እንዳለው የምናይበት ነው።

የዕጣን ኮሚክስ የመጀምሪያው ገጸ ባህሪ ወንድ ይሁን እንጂ ለወደፊት ሴቶችና ሌሎች ገጸ ባህሪያት እንደሚመጡ ይናገራል። የዕጣን ኮሚክስ ዓላማ የጥንቱን ታሪክ ከአሁኑ ሁኔታ ጋር በማዋሃድ የሚያዝናኑና ከአህጉሪቱ ጋር የሚመሳሰሉ ታሪኮችን መንገር እንደሆነም ይገልጻል።

”ለምንተርከው ነገር ገደብ አላስቀመጥንለትም” የሚለው ብስራት፤ ሌሎች ሰዎች ቡድኑን ሲቀላቀሉ ደግሞ የእራሳቸውን የትረካ ስልትና እይታ ይዘው ስለሚመጡ የዕጣን ኮሚክስን ዓላማ በይበልጥ ወደፊት እንደሚያራምደው እምነት እንዳለው ይናገራል።

”የምፈልገው ዕጣን ኮሚክስ ደረጃውን የጠበቀ ሥዕልና ታሪክ ያዞ እንዲቀጥል ብቻ ነው” ሲልም ብስራት የወደፊት ፍላጎቱን ይገልፃል።

ኢትዮጵያዊው ብላክ ፓንተር

BBC Amharic

Share your thoughts on this post
%d bloggers like this:
Visit Us On TwitterVisit Us On YoutubeVisit Us On Instagram