fbpx
AMHARIC

ዶ/ር ፍቅሩ ማሩ የተካተቱበት የቂሊንጦ ቃጠሎ ተጠርጣሪዎች በፍርድ ቤት ላይ ተቃውሞአቸውን አሰሙ

በመቶ አለቃ ማስረሻ ሰጤ የክስ መዝገብ የቂሊንጦ እስረኛ ማቆያን በማቃጠል ተጠርጥረው ክስ የተመሠረተባቸው ዶ/ር ፍቅሩ ማሩን ጨምሮ 38 ተጠርጣሪዎች፣ ሰኞ መጋቢት 3 ቀን 2010 ዓ.ም. በፍርድ ቤት ተቃውሞአቸውን አሰሙ፡፡

ተከሳሾቹ ፍርድ ቤቱን የተቃወሙት በዕለቱ ተቀጥረው የነበረው፣ ዓቃቤ ሕግ በተከሳሾቹ ላይ አስምቶ ያጠናቀቀውን የሰዎች ምስክርነት ቃልና የሰነድ ማስረጃ አግባብ ካለው የሕግ ድንጋጌ ጋር መርምሮ ውሳኔ ለመስጠት ቢሆንም፣ እንዳልደረሰለት በመናገሩና ተጨማሪ አንድ ቀጠሮ እንደሚያስፈልገው በማስታወቁ ነው፡፡

ተከሳሾቹ እንዲናገሩ እንዲፈቀድላቸው ጠይቀው ሲፈቀድላቸው፣ በማረሚያ ቤት ውስጥ በደል እየተፈጸመባቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የታሰሩት ወንጀል ፈጽመው ሳይሆን ዘርን መሠረት በማድረግ መሆኑን፣ አንዳንዶቹ ‹‹ማግለያ›› እየተባለ በሚጠራው ዞን አምስት ውስጥ ታስረው እየተሰቃዩ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

አሸዋ እየበሉ በማረሚያ ቤቱ ኃላፊዎች እየተዛተባቸው መሆኑን ገልጸው፣ ፍርድ ቤቱ ይኼንን ችግራቸውን ተገንዝቦ አፋጣኝ ውሳኔ ሊሰጣቸው ሲገባ፣ በተደጋጋሚ መቅጠሩ ተገቢ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡

በተለያዩ ክሶች ተፈርዶባቸው ለአራትና ከዚያም በላይ ዓመታት ታስረው የቅጣት ጊዜያቸውን ማጠናቀቃቸውን የገለጹት ተከሳሾቹ፣ አሁን የተጠረጠሩት ምንም ባልሠሩት ጉዳይ በመሆኑ፣ የክስ መዝገቡ ተዘግቶላቸው ከቤተሰቦቸው እንዲቀላቀሉ ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል፡፡

አንዳንዶቹ ተጠርጣሪዎች የአዲስ አበባ ነዋሪዎች መሆናቸውን ለፍርድ ቤቱ ገልጸው፣ ከቂሊንጦ ቃጠሎ ጋር በተያያዘ ክስ የተመሠረተባቸው ምንም በማያውቁትና በዘራቸው ምክንያት መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ተመልሰው ወደ ማረሚያ ቤት መሄድ እንደማይፈልጉ ገልጸው፣ ፍርድ ቤቱ ፈርዶባቸው መሞትን እንደሚመርጡ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ከዚያ ማረሚያ ቤት አውጡን፣ የተያዝንበት ሁኔታ ጥሩ አይደለም፣ እየተዛተብን ነው፤›› በማለት ያሉበትን የአያያዝ ሁኔታ አስረድተዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ እንዲናገሩ የፈቀደላቸውን ተከሳሾች አስተያየት አዳምጦ ሲጨርስ እንዳስረዳው፣ ችግር እንዳለ እንደሚገነዘብ ነው፡፡ ነገር ግን መዝገቡ ውስብስብ ከመሆኑም በተጨማሪ፣ ባለፈው ወር ዓቃቤ ሕግ የተከሳሾችን ክስ በማቋረጡ መዝገቦችን በማስቀረብ ክስ የተቋረጠላቸውን ተከሳሾች ሲለይ መክረሙንና ጊዜ እንደወሰደበት አስረድቷል፡፡ በመሆኑም የማያዳግም ቀጠሮ በመስጠት ለሚያዝያ 16 ቀን 2010 ዓ.ም. ውሳኔ እንደሚሰጥ በመግለጽ ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

ምንጭ፡- ሪፖርተር

Share your thoughts on this post
%d bloggers like this:
Visit Us On TwitterVisit Us On YoutubeVisit Us On Instagram