fbpx

ዶ/ር ዐብይ አህመድና የፕሮቶኮል ጉዳይ

ዶ/ር ዐብይ አህመድና የፕሮቶኮል ጉዳይ | አበበ ሙሉ በድሬቲዩብ

ወደ ስልጣን ከመጡ ገና 100 ቀናት ብቻ የሆናቸው የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ባከናወኗቸው ተግባራት የብዙዎችን ትኩረት መሳብ ችለዋል። በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ በርካታ ንግግሮችን አድርገዋል፣ በተለያዩ ኩነቶች ላይ ታድመዋል፣ የስልጠናና የውይይት መድረኮችን መርተዋል፣ የአገር ውስጥና የውጭ አገር ጉብኝቶችን አከናውነዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያልተለመዱ ተግባራትን በማከናወናቸው ከፕሮቶኮል አንጻር ጥያቄ የሚያስነሱ ሆነዋል፡፡ ከእነዚህ ውስጥም በሳውዲ አረቢያው ልዑል የኢትዮጵያ ጉብኝት ወቅት መኪና እየነዱ የአዲስ አበባን ከተማ ማስጎብኘታቸው ተጠቃሽ ነው፡፡

ይህን ለመግቢያ ካነሳን ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና ፕሮቶኮልን የተመለከቱ ጉዳዮች በብዙዎች በትችት መልክ ጭምር የሚነሱ በመሆናቸው ጠቅላያችንን በፕሮቶኮል ሚዛን እየመዘንን ማየትና በእርግጥም የተጣሰ የፕሮቶኮል መርህ አለ ወይ የሚለውን መመልከት ተገቢ ይሆናል፡፡ ከዚያ በፊት ግን ፕሮቶኮል ምንድን ነው የሚለውን መመልከት ይገባል፡፡

ዶ/ር ዐብይ አህመድና የፕሮቶኮል ጉዳይ

ፕሮቶኮል ምንድን ነው ለምንስ ያስፈልጋል?

ፕሮቶኮል ወይም በአማርኛ አቻ ትርጉሙ ሥርዓተ-ደንብ በተለይም በአገራት መሪዎች ደረጃ ያለው እያንዳንዱ ነገር በዝርዝር መመሪያ ተቀምጦለት የሚመራና የሚከናወን ነው፡፡ አገራት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የፕሮቶኮል ጉዳይን የሚመራ ክፍል በማቋቋም ይመሩታል፡፡ በአገራችንም በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ስር በፕሮቶኮል ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ጄኔራል ይመራል፡፡

ፕሮቶኮል የግንኙነት መምሪያ መሳሪያ ነው የሚለው በዚህ ላለንበት ዘመን የሚሰራ ትርጉም ነው፡፡ ሄይግ (Hague) የሚገኘውና በፕሮቶኮል ላይ ስልጠና በመስጠት ታዋቂ የሆነው Protocol Bureau ፕሮቶኮል በአሁን ዘመን ያለው ሚና ግንኙነትን መምሪያ መሳሪያ መሆኑን እንደሚከተለው ያስቀምጣል፡፡

“In essence, protocol management has always been about optimising relationships by maximising personal attention and systemising logistics. Protocol management enables the staging of the personal encounter. In a world where personal attention has become scarce and technology a facilitator for rules and procedures, protocol management provides us with a unique vision in which personal time is the greatest good we can give to someone. It is the modern currency of relationships.”

በዚህ አገላለጽ መሰረት ፕሮቶኮል የግንኙነት መገበያያ ገንዘብ ነው፡፡ ሸቀጥን በገንዘብ የምንገዛ ከሆነ ግንኙነትን ደግሞ በፕሮቶኮል እንገበያለን፡፡ ቀይ ምንጣፍ አንጥፎ እንግዳን መቀበሉ፣ የአቀማመጥ ተዋረዱ፣ የእራት ግብዣው፣ የስጦታ ልውውጡ፣ እነዚህ ሁሉ ተግባራት የግንኙነት ማጠናከሪያ መንገዶች ናቸው። የፕሮቶኮል ዋናው ግቡም ይሄው ነው። ሰዎች ምቾት እንዲሰማቸው በማድረግ ትኩረታቸውን በመጡበት ጉዳይ ላይ እንዲያደርጉ ሁኔታዎችን ይፈጥራል። ነገር ግን ከፕሮቶኮል ጋር የሚነሱ በርካታ ጉዳዮችም አሉ፡፡ ፕሮቶኮልን ከጊዜና ሁኔታዎች ጋር አብሮ የማይሄድ ግትር ነው የሚሉትም አሉ።

ይህ ጽንሰ ሃሳብ ግን በ21ኛው ክፍለዘመን ብዙ ጥያቄዎች የሚነሱበት በመሆኑ ፕሮቶኮል ከጊዜው ጋር አብሮ የሚራመድና በዓላዊ የሚመስለውን (ceremonial) ገጽታውን እያጣና የበለጠ ለግንኙነትና መቀራረብ ዕድል እንዲፈጥር የማድረግ አዝማሚያዎችን እየያዘ ይገኛል። ለዚህም ማሳያ የሚሆኑ በርካታ ምሳሌዎችን መጥቀስ ይቻላል። G-7 ተብሎ በሚጠራው የበለጸጉ አገራት ጉባዔ ላይ የሚታደሙ መሪዎች ከተለመደው አለባበሳቸው ወጥተው በሸሚዝና ሱሪ እንዲሁም ቲሸርት መታየታቸው ለብዙዎች ያልተለመደ ጉዳይ ሆኗል፡፡ አንዳንዶችም የመሪዎችን ገጽታ ቀንሷል ሲሉ አለባበሱን አለመቀበላቸውን ለማሳየት ሞክረዋል፡፡ ይሄ በተከታታይ ጉባዔዎችም ቀጥሏል፡፡ አዘጋጆቹ ግን በመሪዎች ዘንድ ዘና ያለ ስሜት እንዲፈጠር በማድረግና ከተለመደው መደበኛ የግንኙነት ሁኔታ ወጣ በማለት የበለጠ ቅርርብ እንዲፈጠር ያደርጋል ይላሉ፡፡ ይህም አንዱ ፕሮቶኮል ከሁኔታዎችና ከጊዜ ጋር አብሮ እየተቀየረ የመሄድ አዝማሚያ ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድና ዝርዝር የፕሮቶኮል ጉዳዮች

 

  • ያደረጓቸው ንግግሮች ከፕሮቶኮል አንጻር ሲቃኙ

 

የመሪዎች ንግግር ብዙ ትንታኔ የሚሰጥበትና ከፕሮቶኮል አንጻር የሚቃኝ አንዱ ጉዳይ ነው፡፡ ያደጉት አገራት መሪዎች ንግግር ጸሃፊዎች ከፍተኛ ክፍያ የሚከፈላቸውና በትልቅ መዋቅር የተደራጁ ክፍሎችም ናቸው፡፡ መሪዎችም እንደ ተዋናይ ንግግራቸውን ተለማምደውና ተዘጋጅተው ለታዳሚው ለማቅረብ ትልቅ ዝግጅት ያደርጋሉ፡፡

ዶ/ር አብይ አህመድ ባደረጓቸው ንግግሮች ከሌሎች ባህሎችና ህዝቦች ጋር በቀላሉ ለመቀራረብ የሚያስችላቸውን ነጥብ ለማግኘት የማይቸገሩና የሁሉንም ባህል የሚያከብሩ መሆናቸውን አሳይተዋል፡፡ ለሶማሌ፣ ለትግራይ፣ ለጉራጌ፣ ለወላይታ፣ ለሲዳማ፣ ለጎንደርና ለአፋር ህዝብ ባደረጉት ንግግር ከህብረተሰቡ ጋር በቀላሉ የሚያቀራርባቸውን ነጥብ ለማግኘት አልተቸገሩም፡፡ የየአካባቢውን ተረትና ምሳሌ እያነሱ፣ ጀግኖችን እያወደሱ ከሰዎቹ እንደ አንዱ መሆናቸውን አሳይተዋል፡፡ በአካባቢው ቋንቋ ሰላምታ እያቀረቡ ሲያሻቸውም በቋንቋው እየተናገሩ በፕሮቶኮል የሚመከረውን ከአድማጭ ጋር የሚያገናኛቸውን ነጥብ ለይቶ በማግኘት ጆሮ መሳብ ችለዋል፡፡ በንግግራቸው የኢትዮጵያ ታሪክ ከአካባቢው ነባራዊ ሁኔታ ጋር ተቃኝቶ ቀርቦበታል፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ሁሉም ህዝብ ያደረገውን አስተዋጽኦና ደርሻ ተርከዋል፡፡

መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም.  ጠ/ሚ/ር ዶ/ር አብይ አህመድ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባደረጉትንግግር ስለኢትዮጵያዊነት እንዲህ አሉ፡፡

“ማንነታችን እንዳይለያይ ሆኖ የተሰናሰለ፣ እንዳንነጣጠል ሆኖ የተገመደ፣ የተዋደደ እና የተዋሀደ ነውአማራው በካራማራ ለሀገሩ ሉዓላዊነት ተሰውቶ የካራማራ አፈር ሆኖ ቀርቷል። ትግራዋይ በመተማከሀገሬ በፊት አንገቴን ውሰዱ ብሎ የመተማ አፈር ሆኗል። ኦሮሞው በአድዋ ተራሮች ላይ ስለሀገሩደረቱን ሰጥቶ የሀገሩን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ ከአድዋ አፈር ተቀላቅሏል። ሱማሌው፣ ሲዳማው፣ቤንሻንጉል፣ ወላይታ፣ ጋምቤላው፣ ጉራጌው፣ አፋሩ፣ ስልጤው፣ ከምባታው፣ ሀዲያው እና ሌሎቹምየኢትዮጵያ ህዝቦች ሁሉ በባድመ ከሀገሬ በፊት እኔን ብለው እንደወደቁ ከባድመ አፈር ጋርተዋህደዋል። አንድ ኢትዮጵያዊ አባት እንዳሉት እኛ ስንኖር ሰዎች፣ ስናልፍ አፈር፣ ስናልፍ ሀገርእንሆናለን። የየትኛውንም ኢትዮጵያዊ ክቡር ስጋና ደም በየትኛውም የኢትዮጵያ ክፍል ውስጥ አፈርሆኖ ታገኙታላችሁ። ኢትዮጵያውያን ስንኖር ኢትዮጵያዊ ስንሞት ደግሞ ኢትዮጵያ እንሆናለን፡፡ ኢትዮጵያ የሁላችን ሀገር፤ የሁላችን ቤት ናት!”

በዚህ ንግግራቸው ከብዙዎች ጋር እንደተግባቡበት በቀጣይ በታዩትና ከንግግራቸው ከተወሰዱ ነጥቦች ጥቅሶች መዘጋጀታቸው ማሳያ ናቸው፡፡ በዚሁ የበዓለ ሲመት ንግግራቸው ለእናታቸውና ለባለቤታቸው ባቀረቡት ምስጋና ሰውኛ ነውና ብዙዎች ተማርከዋል፡፡ ከብዙ ወላጆችና ቤተሰቦች ጋር ልብ ለልብ ተገናኝተዋል፡፡

በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ በነበራቸው የመጀመሪያ የሥራ ጉብኝት ከሱማሌ ህዝብ ጋር የሚግባቡበትን ጉዳይ ለማግኘት የንግግራቸው የመጀመሪያዎቹ ነጥቦች በቂ ነበሩ፡፡

“የኢትዮጵያ ሱማሌ ህዝብ እንደ ሁሉም የአገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በጫንቃው የተጫነበትን አስከፊ የድህነት ቀንበር ከላዩ አሽቀንጠሮ ለመጣል ከተቀሩት ኢትዮጵያውያን ወንድሞቹ ጋር በአብሮነትና በአጋርነት መሰለፍ ያለውን ፋይዳ በመገንዘብ ኢትዮጵያዊነትን በልቡ ይዞ በየጎራው በመሰለፍ ወራሪዎችን የተፋለመበት ገድል በሁሉም የአገራችን ህዝቦች ልብ ውስጥ የታተመ አኩሪ ገድል ነው፡፡”

በጎንደር በነበራቸው ጉብኝት ለተሰበሰበው ህዝብ በውብ ቋንቋ ጎንደርን እንደሚከተለው ገልጸዋታል፡፡

“የአብሮነትና የዘመናዊነት ተምሳሌት፣ የመካከለኛው ዘመን የሥልጣኔ መሰረትና የህዝባችን የከፍታ መሰላል፣ የባህልና ውብ እሴቶቻችን ማህተም፣ የዘመናዊቷ ኢትዮጵያ ጌጥና የትጉሃን ልጆች እናት፣ የኢትዮጵያችን የታሪክ አውድማና የኩሩ ህዝብ ምድር፣ የዛሬያችን መሰረት ትናንት በተጣለባት ድንቋ ከተማ ጎንደር ተገኝቼ መልዕክት ማስተላለፍ በመቻሌ የተሰማኝን ልባዊ ክብር ለመግለጽ እወዳለሁ፡፡”

በዚህ አገላለጻቸው ውስጥ ብዙ ዝርዝር ነጥቦች አሉ፡፡ ግቡ ግን ከአድማጫቸው ጋር በቀላሉ ለመናበብ ዕድል የሚሰጥ መሆኑ ነው፡፡

በአፋር በነበራቸው ቆይታ ይህን ተናገሩ፡፡

“…የሰው ዘር መገኛ እምብርት፣ የዓለም ከየት መጣን ጥያቄ ምላሽ፣ የተአምራዊ መልክዓ ምድር ሰገነት፣ የደግ ጀግናና ኩሩ ኢትዮጵያውያን ቤት፣ የአገር ወዳድ ህዝብ መሰረት በሆነችው የአፋር ምድር በመገኘቴ የተሰማኝን ልባዊ ደስታ ስገልጽላችሁ ከፍ ባለ ወገናዊ ኩራትና ጥልቅ በሆነ የእንኳን ተገናኘን ሃሴት ውስጥ ሆኜ ነው፡፡ የአፋር ህዝብ ተግዳሮትንና አስቸጋሪ የህይወት መልክን የሚሸሽ ህዝብ ሳይሆን አስቸጋሪውን ዕጣ ፈንታ በጥበብ በማከም ወደ በረከትነት የሚቀይር ውብ ህዝብ ነው፡፡  ”

“ለውጥን እንደግፍ ዲሞክራሲን እናበርታ!” በሚል መሪ ቃል ደግፏቸው መስቀል አደባባይ ለወጣው የአዲስ አበባና አካባቢው ነዋሪ እንዲህ ተናግረዋል፡፡

“…ገና ኃላፊነት ከተረከብን መንፈቅ ሳይሞላን፤ ፊት ለፊታችን እንደ ተራራ የተቆለለውን ግርዶሽ ሳንገፍ፣ ፊት ለፊታችሁ ቆመን ምስጋናን ለመቀበል የሚያስችል አቅም አላደረጀንም፡፡ ነገር ግን ጥላቻ አክስሮናል፣ አጉድሎናል፤ ፍቅር ግን ያተርፋል ያሻግራል ብላችሁ በተስፋ ተሞልታችሁ በምስጋና ጀምራችኋልና በፍቅርና በአንድነት ጀምሮ መጨረስ የተሳነው ስለሌለ የዛሬው የፍቅርና የምስጋና ቀን መድረስ ከሚገባን ማማ የሚያደርሰን የመጀመሪያው ጡብ መቀመጡን ያሳያል፡፡ የዛሬዋን ቀን እንድናይ የዛሬዋን ቀን ያላዩ፣ እንድንኖር ሲሉ የሞቱ፣ እንድንከበር ሲሉ የተዋረዱ፣ እንድንፈታ ሲሉ የታሰሩ፣ ለህይወታችን ህይወታቸውን የገበሩ ሰማዕታትን በዚህ በከበረ ቦታ ቆመን ልናመሰግናቸው ይገባናል፡፡ ያለእኛ ሊኖሩ ይችሉ ነበር፤ ያለ እነሱ እኛ መኖር አንችልም፡፡”

በአጠቃላይ እስከአሁን ባደረጓቸው ንግግሮች ለዳያስፓራው፣ ለተማሪው፣ ለሴቶች፣ ለወጣቶች፣ ለመምህራን፣ ለሰራተኛው፣ ለሃይማኖት አባቶች በአጠቃላይ ለሁሉም ህብረተሰብ ተናግረዋል፡፡ የሁሉንም አድማጭ ጆሮ ለመሳብ የሚያስችል ንግግር ማቅረባቸው እንደመሪ የመደመጥ ዕድላቸውን የጨመረ ጉዳይ ነው። ለሁሉም ስንቅ የሚሆን ነጥቦችን አንስተዋል የቤት ስራ ሰጥተዋል። በፍጹም ትህትና ማስጠንቀቂያዎችን አስተላልፈዋል፡፡

ከፕሮቶኮል አንጻር እንደመሪ ብቻ ሳይሆን እንደተናጋሪ ውጤታማ መሆናቸውን አሳይተዋል፡፡ በዚህ ረገድ የነበረኝ ምልከታ አዎንታዊ ብቻ ሳይሆን ለመሪ ንግግር አዋቂነት ግዴታ ጭምር መሆኑን ማሳያ ነው፡፡

  1. በአለባበስ

በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ጉዞሃቸው ወቅት የጋባዥ አገርን ወይም የሚጎበኙትን አካባቢ ባህልና አለባበስ በመከተል የታዳሚውን ባህልና ወግ አክብረዋል፡፡ በአዲስ አበባ በተደረገው የድጋፍ ሰልፍ ታዳሚው የለበሰውን ቲሸርት በተመሳሳይ በመልበስ የኩነቱ አንዱ ታዳሚ መሆናቸውን አሳይተዋል፡፡ እግረ መንገዳቸውንም በታተመው ጽሁፍ የራሳቸውን ስሜት የሚያንጸባርቅና የሚወክላቸውን መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ የአለባበስ ምርጫቸው ከሁነቶችና ከአካባቢው ጋር የሚሄድ በማድረግ ለአካባቢው ባህልና ወግ እውቅና ሰጥተዋል፡፡ ሌሎችን አክብረዋል፡፡

  1. ያልተለመዱ ተግባራቸው

ሰው ጥየቃ ሃኪም ቤት መገኘታቸው፣ በአስመራ ጉዞሃቸው ኩኪሥ ማስያዛቸው፣ ለሳውዲው ልዑል መኪና እየነዱ ያደረጉት አቀባበል፣ የደም ልገሳና ሌሎችም ጉዳዮች እንዲሁ በማህበራዊ ሚዲያ ከፕሮቶኮል አንጻር ተገቢ አይደሉም በሚል የተነሱ ጉዳዮች ናቸው፡፡ ምልከታዬ ከሌሎች ጋር በነበረኝ ውይይት እንዲሁም በማህበራዊ ድረ ገጾች ካደረኩት ዳሠሣ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከዚህ ቀደም ህዝቡ በመሪዎች ላይ የሚያነሳቸውን ቅሬታዎች የሚቀርፉና መሪም ሰው መሆኑን ያሳዩባቸውን በርካት ተግባራት በማከናወናቸው በበጎ የሚነሳ ተግባር አከናውነዋል፡፡ ዜጎች በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ መንገድ የሚደርስባቸውን ጉዳትና አደጋ ተከትሎ የመሪዎች ጉብኝት የተለመደ ነው። ጠቅላዩ በነዚህ ኩነቶች ታድመዋል። ለሳውዲው ልዑል መኪና እያሽከረከሩ ከተማውን የማስጎብኘታቸውም ጉዳይ ይህ የመሪ ፕሮቶኮል ነው የሚል ጥያቄ ካስነሱ ጉዳዮች ውስጥ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። የሳውዲ ልዑላን የሚያከብሩት እንግዳ ሲመጣ ራሳቸው እያሽከረከሩ ማስጎብኘትን እንደትልቅ ክብር ይወስዱታል። መቀራረባቸውን የሚያሳዩበት አንዱ መንገድም ነው። ሌሎች መሪዎችም ይህንኑ አድርገዋል። የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ በዩጋንዳ በነበራቸው ቆይታ ሙሴቤኒ ራሳቸው እያሽከረከሩ አስጎብኝተዋቸዋል። የተለመደ ብቻ ሳይሆን መሪዎች እግረ መንገዳቸውን ብዙ እንዲቀራረቡ ዕድል የሚፈጥር አጋጣሚ አድርገው ይወስዱታል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ማድረጋቸው የሚያስመሰግን እንጂ የሚያስወቅሥ ምንም ነገር የለበትም፡፡

በአስመራ ቆይታቸውም ኩኪስ ማስያዛቸው ክብርን የሚጎዳ ሳይሆን ለግንኙነት ሲባል የተደረገ ተግባር ነው። ድርጊቱ ሳይሆን ድርጊቱ የተከናወነበትን ዳራ ማየት አስፈላጊ ይሆናል። ለሁለት አስርተ ዓመታት በጠላትነት ሲተያዩ የቆዩ አገራት የመጀመሪያውን ገበታ አብሮ ቀርቦ እህል ለመቁረስ መድረስ ከሚፈጥረው ስሜት የሚመነጭና ተገቢ የሆነ ተግባር እንጂ የመሪ ሚናን የሚያሳንስ ሆኖ አላገኘሁትም፡፡ በመግቢያችን እንዳልነው ፕሮቶኮል ግንኙነትን የምንመራበት መሳሪያ መሆኑን ልብ ይሏል፡፡

የኤርትራ ልዑካን ጉዳይ አዲስ አበባ መምጣትና የጠቅላይ ሚኒስትሩ አቀባበል አንዱ ጉዳይ ሆኖ ቆይቷል። አስመራ ለአዲስ አበባ ጥሪ ምላሽ መሥጠቷን ተከትሎ በወልቂጤ የነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ በቴሌቪዥን በሰጡት ምላሽ የኤርትራ ልዑኡካንን ራሳቸው እንደሚቀበሉ መግለጻቸውን ተከትሎ ለልዕካኑ አቀባበል አድርገዋል። በዚህም ለግንኙነቱ የሰጡትን ቦታና ጥሪያቸው ተቀባይነት በማግኘቱ ለልዑካን ቡድኑ  የመሪ አቀባበል ማድረጋቸው በመግቢያችን ፕሮቶኮል በዚህ ዘመን የግንኙነት መምሪያ መሳሪያ ነው ላልነው ትርጉም ስምም የሆነ ተግባር ነው። ጠቅላዩ በአስመራ በብዙ እጥፍ ምላሹን አግኝተውታል። ከአቀባበል እስክ ሽኝት የነበረው የኤርትራ መሪዎች ተግባርም ከፕሮቶኮል በላይ ለግንኙነቱ ትልቅ ቦታ የሰጠ ነበር፡፡

DireTube

Share your thoughts on this post
%d bloggers like this:
Visit Us On TwitterVisit Us On YoutubeVisit Us On Instagram