ድብርት ከልብ ህመም ጋር ተያያዥነት ላላቸው በሽታዎች ያጋልጣል-ጥናት
ድብርት መደበኛ ያልሆነ የልብ ምትን ከፍ በማድረግ ለስትሮክ እና ለልብ ህመም እንደሚያጋልጥ አንድ ጥናት አመለከተ።
ጥናቱ ለድብርት የተጋለጡ ሰዎች 75 በመቶ ያህል መደበኛ ላልሆነ የልብ ምት ተጋላጭ ሆነው መገኘታቸው አረጋግጧል።
በዚህም ከዚህ ቀደም የነበሩ ጥናቶች የልብ በሽታን ከፍርሃት እና ጭንቀት ጋር ያያይዙት ነበር ያሉት ተመራማሪዎቹ፥ አሁን ግን ድብርትም ለልብ በሽታ እንደሚያጋልጥ በጥናቱ ማረጋገጣቸውን ገልፀዋል።
ይህም የልብ በሽታ እና የአዕምሮ ጤና ሁኔታ ከፍተኛ ቁርኝት እንዳላቸው ያረጋገጠ ጥናት ነው ተብሏል ።
የአሜሪካ የልብ ማህበር በሀገሪቱ 2 ነጥብ 7 ሚሊየን ሰዎች መደበኛ ያልሆነ የልብ ምት ችግር እንዳለባቸው አስታውቋል።
መደበኛ ያልሆነ የልብ ምት (atrial fibrillation) ማለት የልብ ሁለቱ የላይኛው ክፍሎች በተገቢው መንገድ መስራት ሳይችሉ እና ከታችኛው የልብ ክፍል ጋር ሳይገናኙ በሚቀሩበት ወቅት የሚፈጠር ችግር ነው።.
ይህም ችግሩ በወቅቱ ተገቢውን ህክምና ካለገኘ በልብ በሽታ ምክንያት ለሚከሰት ስትሮክ ብሎም ለሞት እንደሚያጋልጥ ተጠቁሟል።
በሰዎች ላይ ውጥረት ሲከሰት የሚፈጠሩት ፍርሃት እና ጭንቀት የሚፈጥሩት ሆርሞኖች በሂደት ለልብ በሽታ እንደሚያጋልጡም ባለሙያዎቹ ይናገራሉ።
አስር ዓመታት በወሰደው በዚህ ጥናት ከ6 ሺህ 600 በላይ ተሳታፈዎች ተካፍለዋል።
በዚህም ድብርት ከሌለባቸው ሰዎች አንፃር በድብርት የተጠቁት መደበኛ ላልሆነ የልብ ምት ተጋላጭ ሆነው መገኘታቸውን ጥናቱ አመልክቷል።
በጥናቱ ለልብ በሸታ የሚያጋልጡት ምክንያቶች ከመጠን በላይ ውፍረት፣ ደም ግፊት እና ማጨስ እንደመነሻ ተጠቁሟል።
ምንጭ፣ ዩ ፒ አይ