fbpx

HT

ሐበሻ ታይምስ ሚዲያ

AMHARIC

ዳሸን ባንክ ለቢጂአይ ኢትዮጵያ የ650 ሚሊዮን ብር ብድር ለቀቀ

  • ብድሩ ለራያ ቢራ ግዥ እንደሚውል ታውቋል

ራያ ቢራን ለመግዛት የተስማማው ቢጂአይ ኢትዮጵያ፣ ከዳሸን ባንክ የ650 ሚሊዮን ብር ብድር እንደተፈቀደለት ታወቀ፡፡

ሪፖርተር ከዳሸን ባንክ ምንጮች እንዳረጋገጠው ከሆነ፣ የብድር ጥያቄው በባንኩ ጸድቆ ክፍያው ለሚፈጸምላቸው የራያ ቢራ ባለአክሲዮኖች እንዲከፋፈል ታስቦ መለቀቁንም ማረጋገጥ ተችሏል፡፡

ቢጂአይ ኢትዮጵያ በራያ ቢራ አክሲዮን ማኅበር ውስጥ ካሉት አክሲዮኖች ውጪ ያሉትን 68 በመቶ የአክሲዮኖች ድርሻዎች ለመግዛት የተስማማበት ዋጋ ከ2.5 ቢሊዮን ብር በላይ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ለእዚህ አክሲዮኖች ግዥ ከሚያውለው ገንዘብ ውስጥ የ750 ሚሊዮን ብር ብድር ከአዋሽ ባንክ ማግኘቱን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

ለአንድ ፕሮጀክት በግል ባንኮች የተሰጠ ከፍተኛ የብድር መጠን ሲሆን፣ ከዚህ ብድር በተጓዳኝ፣ ዳሸን ባንክም ለራያ ቢራ የአክሲዮን ግዥና ዝውውር ይውላል የተባለውን የ650 ሚሊዮን ብር ብድር በመፍቀዱ፣ ለአክሲዮን ግዥ ከሚውለው ከጠቅላላው ገንዘብ ውስጥ ሁለቱ ባንኮች ከግማሽ በላይ የሚሆነውን ገንዘብ በብድር መልቀቃቸውን አመላክቷል፡፡

ቢጂአይ ኢትዮጵያ በራያ ቢራ ካለው የ42 በመቶ ድርሻ ውጪ ያሉትን አክሲዮኖች ለመግዛት የተስማማበት ዋጋ፣ የአንድ ሺሕ ብር ዋጋ ያለውን የአክሲዮን ድርሻ ከሰባት ሺሕ ብር በላይ በመስጠት ነው፡፡

በአሁኑ ወቅት በተለይ በራያ ቢራ የአክሲዮን ማኅበር ውስጥ ከፍተኛ ድርሻ ያላቸው ግለሰቦችና ኩባንያዎች በዚሁ ስምምነት መሠረት የአክሲዮን ድርሻቸውን ወደ ቢጂአይ ኢትዮጵያ በማዛወር ክፍያው እየተፈጸመላቸው እንደሚገኝ ታውቋል፡፡

ከአክሲዮን ዝውውሩ ጋር ተያይዞ፣ እያንዳንዱ ባለአክሲዮን ለመንግሥት መክፈል ያለበት የ30 በመቶ ከካፒታል ግኝት በሚገኝ ገቢ ላይ ታስቦ የሚከፈለው ታክስ እያከራከረ ይገኛል፡፡

ቢጂአይ ኢትዮጵያ ከፍተኛ የቢራ ገበያ ድርሻ ከያዙ ኩባንያዎች አውራው ሲሆን፣ ከራያ ቢራ ውጪ ቢጂአይ ኢትዮጵያን የሚያስተተዳድረው ዓለም አቀፉ ካስትል ኩባንያም በኢትዮጵያ በቅርቡ ወደ ሥራ የገባውን የዘቢዳር ቢራ የ60 በመቶ የአክሲዮን ድርሻ ለመግዛት መስማማቱ ይታወሳል፡፡

ይህም የቢጂአይ ኢትዮጵያን የገበያ ድርሻ እስካሁን ካለውም በላይ ከፍተኛ እንደሚያደርገው ይጠበቃል፡፡ የዘቢዳር ቢራ የ60 በመቶ የአክሲዮን ሽያጭ በቀጥታ በቢጂአይ ኢትዮጵያ በኩል ያልፈተጸመ ሲሆን፣ ስምምነቱም በካስትልና በዘቢዳር ቢራ የ60 በመቶ ድርሻን በያዘው ዩኒብራ በተባለው የሆላንድ ኩባንያ የተያዘውን ነው፡፡

ይህንን ስምምነት አስመልክቶ በቢጂአይ በኩል የተሠራጨው መረጃ በካስትልና በዩኒብራ መካከል የተደረሰው ስምምነት የሚፀናው በንግድ ውድድርና ሸማቾች ጥበቃ ባለሥልጣን ነው፡፡

በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ወደ ቢጂአይ ይዘዋወራሉ ከተባሉት ሁለቱ ፋብሪካዎች ውስጥ ራያ ቢራ በየዓመቱ 700 ሺሕ ሒክቶ ሊትር ዘቢዳር ደግሞ 600 ሺሕ ሒክቶ ሊትር ነው፡፡ ራያ በታሪካዊቷ ማይጨው ከተማ የተገነባ ሲሆን፣ ዘቢዳር ደግሞ በደቡብ ኢትዮጵያ በጉራጌ ዞን ውስጥ በምትገኘው ጉብርየ ከተማ ውስጥ የተገነባ ነው፡፡

Share your thoughts on this post
%d bloggers like this:
Visit Us On TwitterVisit Us On YoutubeVisit Us On Instagram