fbpx
AMHARIC

ደቡብ ሱዳን ኢትዮጵያን አልፈልግም አለች

የደቡብ ሱዳኑ ማስታወቂያ ሚኒስትር ኢትዮጵያ ለድርድር ቦታ አትሆነንም ማለታቸዉ ምናልባትም የኢጋድ ሚኒስትሮች ምክር ቤት ያሳለፈዉ ዉሳኔ የጁባን መንግሥት አስቆጥቶ ይሆናል። ዉይይቱ በቀጣይ ጅቡቲ ኬንያ አልያም ዩጋንዳ ላይ መካሄድ ይችላልም ብለዋል።

ኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ቀዉስ ዉስጥ በመሆንዋ ለደቡብ ሱዳን የሰላም ድርድር ሌላ ቦታ መፈለግ እንደሚገባ የደቡብ ሱዳን መንግሥት አስታወቀ። የደቡብ ሱዳን የማስታወቂያ ሚኒስትር በሳምንቱ መጀመርያ ለአንድ የሃገር ዉስጥ ራድዮ በሰጡት ቃለ ምልልስ፤ በኢትዮጵያ የቀጠለዉ ፖለቲካዊ ቀዉስ የሰላም ድርድሩን ሊያጨናግፍ አይገባም ብለዋል።

የደቡብ ሱዳኑ የማስታወቅያ ሚኒስቴር ሚሻኤል ማኩይ ሉት ባለፈዉ ሰኞ ለሃገር ዉስጥ መገናኛ ብዙሃን በሰጡት ቃለ ምልልስ ኢትዮጵያ ፖለቲካ ቀዉስ ውስጥ በመሆንዋ የደቡብ ሱዳን ተፋላሚ ኃይሎች መደራደርያ ሃገር እንዲቀየር መንግሥታቸዉ ሃሳብ ማቅረቡን አስታወቀዋል።

« የምንወያይበት ቦታ እንዲቀየር እንፈልጋለን። ምክንያቱም ድርድርና ዉይይታችን ኢትዮጵያ ዉስጥ ባለዉ ወቅታዊ ፖለቲካዊ ቀዉስ ምክንያት እንዲቋረጥ ባለመሻታችን ነዉ። ዉይይቱ በቀጣይ ጅቡቲ ኬንያ አልያም ዩጋንዳ ላይ መካሄድ ይችላል። ነገርግን በሶማልያ በሱዳን እና በደቡብ ሱዳን እንዲካሄድ አንሻም።»

ማኩይ ሉት የኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ በሂደት ላይ በሚገኘዉ በሃገራቸዉ የሰላም ድርድር ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳሳደረበት ተናግረዋል።

በምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ባለስልጣን/ኢጋድ/ አማካኝነት ባለፈዉ የካቲት ለሁለተኛ ዙር ድርድር የተቀመጡት የደቡብ ሱዳንን ፕሬዚዳንት ሳልቫኪር ቡድንና የተቀናቃኙ ቡድን ስምምነት ላይ ባለመድረሳቸዉ በሁለቱ ቡድኖች መካከል ሊካሄድ የነበረው ድርድር ለጊዜዉ መታገዱ ይታወቃል።  የደቡብ ሱዳን የፖለቲካ ጉዳዮች ተንታኝ ጋዜጠኛ ጀምስ ሽማኑኤላ ለደቡብ ሱዳን ድርድር ከኢትዮጵያ የተሻለ ቦታ የለም ይላል።

« ድርድሩ በኢትዮጵያ ተካሄደ ማለት ኢትዮጵያ የዉይይቱን ወጭ ትሸፍናለች ማለት አይደለም። በርግጥ ድርድሩ የሚካሄደዉ በምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት/ኢጋድ/ ተወካዮች አማካይነት ነዉ። በአጭሩ ኢትዮጵያ ዉይይቱን ለማካሄድ የተመረጠ እና ትክክለኛ ቦታ ነዉ።»

የደቡብ ሱዳኑ የማስታወቅያ ሚኒስትር የድርድሩ ቦታ ከኢትዮጵያ ይነሳ የሚል ሃሳብ የተሰማዉ  ኤርትራን ሳይጨምር ሰባት አባል ሃገራትን ያቀፈዉ የኢጋድ አባል ሃገራት ስብስብ በሚቀጥለዉ ሳምንት መጀመርያ በደቡብ ሱዳን የሚታየዉን የርስ በርስ ጦርነት ለማስቆም ድርድር ለመጀመር ዝግጅት እያደረገ መሆኑ በተሰማበት ወቅት ነው።  ኢትዮጵያ እንደ ሃገር አታደራድርም ያሉት  በኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት እና ስልታዊ ጥናት ተቋም የፖለቲካ ተንታኝ አቶ አበበ አይነቴ አዲስ የኢጋድ ሊቀመንበር እስኪገኝ ድርጅቱን ጠ/ሚ ኃይለማርያም ደስአለኝ በመምራት ይቀጥላሉ ብለዋል።

ላለፉት ሰባት ስምንት ዓመታት የኢጋድ ሊቀመንበርነቱ በኢትዮጵያ እጅ ፀሐፊነቱ ደግሞ በኬንያ እጅ መሆኑን የተናገሩት አቶ አበበ፤ የማስታወቂያ ሚኒስትሩ ይህን አስተያየት የሰጡት ምናልባት የኢጋድ ሚኒስትሮች ምክርቤት በደቡብ ሱዳንን ያሳለፈዉ ዉሳኔ ደቡብ ሱዳንን አስቆጥቶ ሊሆን ይችላል ሲሉ አስተያየታቸዉን ሰጥተዋል።

እንደ ደቡብ ሱዳን የፖለቲካ ጉዳዮች ተንታኝ እና ጋዜጠኛ ጀምስ ሽማኑኤላ አስተያየት ደግሞ አባባሉ የጁባ መንግሥት ድርድሩን ለማጨናገፍ የሚያደርገዉን መፍጨርጨር የሚያሳይ ነው።

« ምናልባት ጁባ የገባችበትን የፖለቲካ ዉጥንቅጥ በመጠቀም ድርድሩን ለማጨናገፍ ትፈልጋለች።  የጁባ ችግር የድርድር ሂደቱን መመረዝ መፈልግዋ ብቻ ነዉ። ምናልባትም ጥቅም ለማግኘት ፈልገዉ ይሆናል።»

የኢጋድ አባል ሃገራት ከራስ ጥቅም አንፃር እስከዛሬ የተለያየ አቋም ይዘዉ ቢቆዩም ባለፈዉ ታህሳስ ወር አዲስ አበባ ላይ በተካሄደዉ ስብሰባ በአቋም አንድ መሆናቸዉ ለሃገሪቱ መፍትሄ ለማምጣት ጥሩ ርምጃ ማሳየታቸዉ ተመልክቶአል።  DW

Share your thoughts on this post
%d bloggers like this:
Visit Us On TwitterVisit Us On YoutubeVisit Us On Instagram