fbpx
AMHARIC

ደራሲ ይስማከ ወርቁ ሙሉ ወጪ ተሸፍኖለት እንዲታከም የቀረበለትን ዕድል አልቀበልም አለ

ደራሲ ይስማከ ወርቁ ሙሉ ወጪ ተሸፍኖለት እንዲታከም የቀረበለትን ዕድል አልቀበልም አለ

– ጋዜጠኛ ብሩክ እንዳለ ከሳምንት በኃላ ለሕክምና ወደቱርክ ያመራል | ድሬቲዩብ

አፍሪሄልዝ ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግል ኩባንያ በቅርቡ የጤና ችግር ለገጠመው የኢትዮጽያ ቴሌቪዥን የቀድሞ ባልደረባ አቶ ብሩክ እንዳለ ሙሉ ወጪን በመሸፈን በአውሮፓ ቀዳሚ በሆነው የቱርክ ሆስፒታል ለማሳከም ዝግጅት መጨረሱን አስታወቀ፡፡

በተመሳሳይ ሁኔታ ሕክምናው ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቀውንና በትራፊክ አደጋ ጉዳጥ የደረሰበትን ደራሲ ይስማከ ወርቁ ለማሳከም የኩባያው ቦርድ ቢወስንም ደራሲው ፍቃደኛ ባለመሆኑ ምክንያት ሕክምናው መቅረቱን ይፋ አደረገ፡፡

የአፍሪ ሄልዝ ቲቪ መስራቶችና የቦርድ አመራሮች ዶ/ር ሜለን በቀለ፣ አቶ ባህሩ መንግስቱ፣ አቶ ኢሳያስ አበበ ለድሬቲዩብ በሰጡት መግለጫ አፍሪሄልዝ ከተቋቋመበት ዓላማ ጎን ለጎን ማህባራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት በማሰብ ጋዜጠኛ ብሩክ እንዳለ የገጠመውን የዲስክ መንሸራተት የጤና ችግር በአገር ውስጥ ማከም ባለመቻሉ ምክንያት ዕርዳታ እየተሰባሰበለት መሆኑን በመረዳታቸው የሚዲያ ሰዎች እየተጎዱ ሚዲያን ማስፋፋት አይቻልም በሚል መንፈስ ከፍተኛ ወጪ በመመደብ በውጪ አገር ሄደው እንዲታከሙ የኩባንያው ቦርድ መወሰኑን አስታውሰዋል፡፡ በዚሁ መሠረት በአውሮፓና በአዥያ በሕክምና አገልግሎት አሰጣጥ በአንደኛነት የሚጠቀሰውና በዓለም አቀፍ ደረጃ የሁለተኛ ደረጃ በያዘው የቱርክ አሲባደም (ACIBADEM) ሆስፒታል እንዲታከም ዝግጅቱ በመጠናቀቁ ከሳምንት በሀላ ወደዚያ እንደሚያመራ አስረድተዋል፡፡

በተመሳሳይ ሁኔታ ደራሲ ይሰማከ ወርቁ የመኪና አደጋ ካጋጠመው በሀላ በራስ ቅሉ አካባቢ በደረሰበት ጉዳት መናገር የማይችልበት ሁኔታ መፈጠሩንና ሕክምናው በውጭ አገር ለማካሄድ ኮምቴ መቋቋሙን ከመገናኛ ብዙሃን መስማታቸውን የቦርድ አባላቱ አስታውሰው በተመሳሳይ ሁኔታ ይስማከን ለመርዳት በማሰብ ሕክምና ለማመቻቸት መሞከራቸውን ገልጸዋል፡፡ ሕክምናው ከባድ በመሆኑ ሆስፒታል ማፈላለግ በራሱ ጊዜ የወሰደ ተግባር እንደነበር ጠቁመው በመጨረሻም በመገኘቱ ደራሲው አስፈላጊውን መረጃ እንዲሰጣቸውና የጉዞ ሰነዶች እንዲያሟላ ንግግር መጀመራቸውን ጠቁመዋል፡፡

ደራሲውን እና ደራሲውን ለማሳከም ፈንድ ለማሰባሰብ የተቋቋመ ኮምቴ አንዳንድ አባላት ጋር ተነጋግረው በሃሳቡ ተስማምተው በጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ ለመስጠት ቀጠሮ ከያዙ በሃላ በዚያ እለት እኛ በማናውቀው ሁኔታ ኮምቴው ገንዘብ ለማሰባሰብ እየተዘጋጁ መሆኑን ስንሰማ ይህ ማድረግ እንደማይቻል ስንናገር “እናንተ ተጋባዥ እንግዶች ናችሁ፣ በዚህ ጉዳይ አያገባችሁም” የሚል መልስ ተሰጠን ብለዋል፡፡ በዚህም ምክንያት በዕለቱ የተጠራው መግለጫ ለሌላ ጊዜ እንዲተላለፍ ማድረጋቸውን ጠቁመው ኮምቴው ግን በሌላ ጊዜ በራሱ ፕሮግራም መግለጫ መስጠቱን ተናግረዋል፡፡

የአፍሪ ሄልዝ የቦርድ አባላት በመጨረሻም አቶ ይስማከ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሃሳቡን ለውጦ የሕክምና ድጋፉን ለመጠቀም ከፈለገ በራቸው ክፍት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አፍሪሄልዝ በቅርቡ የቴሌቭዥንና የራዲዮ (93 ነጥብ 8) ራሱን የቻለ የ24 ሰዓታት ስርጭት ያለው የጤና ቻናል ከፍቶ ወደሥራ ለመግባት ዝግጅት ማጠናቀቁን፣ በተጨማሪም ኦንላይን ሚዲያ እና ኮል ሴንተር (8455) የጤና አገልግሎት ለመስጠት መዘጋጀቱን ዶ/ር ሜለን በቀለ የነርቭ ሕክምና ስፔሻሊስትና የኩባንያው ዋና ሥራ አስፈጻሚ ተናግረዋል፡፡

ደራሲ ይስማዕከ ወርቁ ከደረሰበት አደጋ ጋር ተያይዞ መናገር እንደማይችል በኢቢኤስ ቴሌቭዥንለሕዝብ ይፋ የተደረገ በመሆኑ ስለጉዳዩ የተዋቀረውን ኮምቴ የሚመራውን አርቲስት ሽመልስ አበራ በስልክ ለማነጋገር በተደጋጋሚ ሞክረን ስልኩ ዝግ በመሆኑ ሳይካልን ቀርቷል፡፡

አንድ ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተል የሚዲያ ባለሙያ በሰጠው አስተያየት አፍሪ ሄልዝ ኩባንያ በበጎ ፈቃድ ተነሳስቶ በራሱ ሙሉ ወጪ ይስማከን ለማሳከም ያደረገው ጥረት የሚደነቅና የሚመሰገን መሆኑን አስታውሶ ነገርግን ኮምቴው ገንዘብ ማሰባሰብ ላይ ትኩረት በማድረጉ ምክንያት ይህን ዕድል ሊጠቀምበት አለመፈለጉ እንዳሳዘነው አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡

DireTube

Share your thoughts on this post
%d bloggers like this:
Visit Us On TwitterVisit Us On YoutubeVisit Us On Instagram