fbpx

ይቅርታ ስላቅ እንዳይሆን

ይቅርታ ስላቅ እንዳይሆን | ኪዳኔ መካሻ (የህግ ባለሞያ )በድሬቲዩብ

የአብዲ አሌን ቃለምልልስ ሰማሁት። ባጠቃላይ አንድምታው አጥፍቻለሁ ይቅር በሉኝ ሌላውስ ይቅር ተባብሎ የለም ወይ እኔንስ ይቅር ብትሉኝ ምን አለበት፤ተፅእኖ ነበረብን ጣልቃ ሲገባብን የነበረው የቀድሞው የደህንነት ሀላፊ ጌታቸው አሰፋ ነበር የሚል ነው።

ያሳቀችኝ አባባሉ ደግሞ፦

‘ጌታቸው አብዲ ሙሰኛ ነው ይላል፤ እሱ ያሰራውን የደህንነት ቢሮ አይቼዋለሁ፤ በጣም ውድ ህንፃ ነው፤ በደሀ ሀገር እንደዛ አይነት ቢሮ ማሰራቱ እራሱ ሙሰኛ መሆኑን ያሳያል። ህዝብ አይቶት የማያውቀው ለምንድን ነው? አውሮፓም አሜሪካም እስያንም እናውቃለን እንደዛ አይደለም ሚሰራው’ የምትለው ነች። የኔስ ምኑ ይገርማል አይነት ናት።

አብዲ እኔ ባየሁት ቪድዮ ላይ ህግ የስልጣን ገደብ እና ተጠያቂነት እንዳለም ዘንግቶታል።

የክልሉን እና የፌደራሉን ስልጣኖች ሕገ መንግስቱ አስቀምጦታል። ስለዚህ ከተደረገም ጌታቸው እንዳሻው ሲያደርገው አብዲ መቃወም ነበረበት።

የሱማሌ ክልል ፕሬዝዳንት ሆኖ ተገቢውን ሀላፊነቱን ባለመወጣቱ ለደረሰ የሰብአዊ መብት ጥሰት፤ በክልሉ እስር ቤቶች ለተፈፀሙ ኢሰብአዊ አያያዝና ማሰቃየቶችን፤ እሱና አመራሮቹ ባለመቆጣጠራቸው፣ ተገቢውን ጥበቃ ባለመድረጋቸው በቀጥታም ወይም በተዘዋዋሪ ተጠያቂ ሊሆኑ ይችላሉ።

በቅርቡ በኦሮምያና በሱማሌ ክልል አዋሳኝ ወረዳዎች ውስጥ የሚኖሩ የኦሮሞዎች እና የኢትዮጽያ ሱማሌዎች ላይ ለደረሰው ዘርን መሰረት ያደረገ ጥቃት ላይስ የአብዲ አሌና የሌሎች አመራሮቹ ሚና ምን ነበር? በሁለቱም ክልልሎች ህዝቦች ላይ ጥቃቱ እንዳይሰነዘር ያደረጉትስ ጥበቃ ምን ነበር?

ይሄን እና ሌሎችንም ሀላፊነትን ባለመወጣት፣ ስልጣንን አላግባብ በመጠቀም የተሰሩ ጥፋቶችንም ነው አብዲ ‘ሰው ነን አጥፍተናል የማይሳሳት ሰው ካለ እሱ ሸይጣን ነው’ ይቅር እንባባል የሚለን?

ይቅርታ አላማው እኮ የህግ ተጠያቂነትን እና የሕግ የበላይነትን ማስቀረት አይደለም።

መግባባትን እና እርቅን ለማስፈን በነበሩ አለመግባባቶች ህግን እንደ መሳሪያ በመጠቀም ወይም ከዛ ጋር በተያያዘ መልኩ የተፈፀሙ እና ያለ በቂ ማስረጃ የተመሰረቱ ክሶችን የሚመለከት ነው።

በምንም መልኩ ግን ሊሳበቡ የማይችሉ በእስረኞች ላይም ሆነ በማንኛውም ሰው ላይ የተፈፀሙ ኢሰብአዊ ማሰቃየት አካል ማጉደል እና ግድያዎችን፤ዘር ፣ሀይማኖት አመለካከት ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶች ማፈናቀሎች እና ግድያዎች በይቅርታ ለማደባበስና እጃቸው በንፁሀን በደል ያደፉ ሰዎችን ለማስመለጥ አይደለም። ይህን ሕገመንግስታችንም አይፈቅደውም።

ስለዚህ እንደ አብዲ አሌ አይነቶቹ ኑዛዜ መሰል ንግግሮች ከጀርባቸው ብዙ ፍላጎት ቢኖርም፤ የይቅርታ እና የፍቅር የመተሳሰብ ለውጥ ጅምሮችን አላግባብ መጠቀሚያ ለማድረግ ያለሙ ይመስላሉ።

አንደምታቸውም በሕግ እንዳትጠይቁን ነው። ይህ ደሞ የህግ የበላይነትን እና ከሕግ ፊት ሁሉም እኩል ነው የሚለውን መርህ አደጋ ላይ ይጥላል።

የሱማሌ ክልል ህዝብም ሆነ የፌደራሉ መንግስት ግን ይቅርታውን ብቻ ሳይሆን በክልሉ አመራሮችም ሆነ በሌሎች አካላት የተፈፀሙ ድርጊቶችን ሁሉ መርምረው ተገቢውን ሕጋዊ ምላሽ መስጠት አለባቸው።

ይህ የአብዲ ኢሌ ንግግር እና ይቅርታ የክቡር ዶ/ክ ጥላሁን ገሰሰ ሙዚቃ አስታወሰኝ፦

“የልብን ሰርቶ ይቅርታ መጠየቅ
ብልጠት ነው
…አጉል መራቀቅ።”  DireTube

Share your thoughts on this post
%d bloggers like this:
Visit Us On TwitterVisit Us On YoutubeVisit Us On Instagram