fbpx

የ1997 ነባር የ20 80 የጋራ መኖሪያ ቤት ተመዝጋቢዎች በሚቀጥለው ዓመት ሙሉ በሙሉ የቤት ባለቤት ይሆናሉ – የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት እና አስተዳደር ቢሮ

የ1997 ዓመተ ምህረት ነባር የ20 80 የጋራ መኖሪያ ቤት ተመዝጋቢዎችን በሚቀጥለዉ ዓመት ሙሉ ሙሉ የቤት ባለቤት ለማድረግ እየሰራ ስለመሆኑ የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት እና አስተዳደር ቢሮ ገለጸ።

ቢሮው የቀሩት ነባር ተመዝጋቢዎች 78 ሺህ መሆናቸውን ጠቁሞ አሁን ላይ ከ94 ሺህ በላይ ቤቶች በጥሩ የግንባታ አፈፃፀም ላይ እንደሚገኙ የገለጸ ሲሆን፥ ነባር ተመዝጋቢዎችም በ2011 ሙሉ በሙሉ የቤት ባለቤት ይሆናሉ ብሏል፡፡

የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት እና አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ አቶ ይድነቃቸዉ ዋለልኝ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ዛሬ ቆይታ አድርገዋል።

የከተማ አስተዳደሩ በ11ኛዉ የቤት እጣ አወጣጥ ስነ ስረዓት ላይ የባለ ሶስት መኝታ ቤት ተመዝጋቢዎቸን ሙሉ በሙሉ የቤት ባለቤት ማድረጉን ገልፆ እንደነበር ይታወሳል።

ሆኖም ነባር ባለ ሶስት መኝታ ቤት ተመዝጋቢዎች እጣ ወጥቶላቸዋል መባሉን ተከትሎ በርካታ ዜጎች ጥያቄ ሲያነሱ ቆይተዋል፡፡

አቶ ይድነቃቸው ታዲያ በወቅቱ ሙሉ በሙሉ ቤቶች የተላለፉት 29 ወር የቆጠቡት ብቻ ናቸዉ ያሉ ሲሆን፥ አሁን ግን የነባር ባለ ሶሰት መኝታ ቤት ተመዘጋቢዎችን ሙሉ በሙሉ ለመጨረስ በመታሰቡ ከ3 ወር ጀምሮ የቆጠቡ ሙሉ በሙሉ የቤት ባለቤት ለመሆን ችለዋል ብለዋል።

አቶ ይድነቃቸው የከተማዋን ነዋሪዎች የቤት ችግር ለመፍታት አስተዳደሩ ባለፉት ጊዜያት በ11 ዙሮች ከ176 ሺህ በላይ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን በመገንባት ለተጠቃሚዎች ማስተላለፉን አስታውሰዋል።

በቀጣይም ከ132 ሺህ በላይ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ በማገባደድ ላይ በመሆናቸው በቅርቡ ለእድለኞች ለማስረከብ በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።

በ2005 የተመዘገቡ የቤት ፈላጊዎችን ተጠቃሚ ለማድረግም የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ ነው ብለዋል፡፡

በእርግጥ ከቤት ፈላጊው አንፃር ያለው ቁጥር እና እየተገነባ ካለው ቤት አንፃር ተደራሽ ማድረጉ ከባድ ነው ያሉት የቢሮ ሃላፊው አዳዲስ ግንባታዎች እንደተጀመሩ ተናግረዋል።

በሌላ በኩልም መንግስት የኪራይ ቤቶች፣የማህበር ቤቶች እና ሌሎች አማራጮችን እያቀረበ በመሆኑ የመዲናዋን ቤት ፈላጊዎችን ለማርካት አጋዥ ይሆናሉ ብለዋል።

በ2005 በባለ ሶሰት መኝታ የተመዘገቡ የቤት ፈላጊዎች ደግሞ ከለሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ በእጣ እንደሚካተቱ ገልጸዋል።

አቶ ይድነቃቸወር የከተማ አስተዳደሩ በርካታ ቤቶችን ከስራ ተቋራጮች መረከቡን በመግለጽ የቤቶች አፈጻፀም መልካም የሚባል መሆኑንም ተናግረዋል።

ነገር ግን የመሰረተ ልማት ስራዎች ስላልተሟሉላቸው ለህብረተሰቡ ማስተላለፍ አልተቻለም ብለዋል።

የከተማ አስተዳደሩ የመዲናዋን ነዋሪዎች ቤት ፍላጎት ለማርካት በርካታ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን ተናግረው ህብረተሰቡ የሚጠበቅበትን ቁጠባ እንዲያካሂድም ጥሪ አካሂደዋል፡፡

አቶ ይድነቃቸዉ በአጠቃላይ ከቤት ፈላጊዉ ከ20 ቢሊየን ብር በላይ መቆጠቡን ተናግረዋል።

እስካሁንም በ20 80 ቤቶች ፕሮግራም ከ600 ሺህ በላይ ቤት ፈላጊዎች ቁጠባቸዉን እያካሄዱ ሲሆን፥ ከነዚህ ውስጥም ከ100 ሺህ በላይ የሚሆኑት መቶ በመቶ የቆጠቡ መሆናቸውን ነው ኃለፊው ለፋና ብሮድ ካስቲንግ ኮርፖሬት የተናገሩት።

 

 

በተመስገን እንዳለ

Share your thoughts on this post
%d bloggers like this:
Visit Us On TwitterVisit Us On YoutubeVisit Us On Instagram